Saturday, 08 November 2014 11:49

ሉሲ የተገኘችበት 40ኛ ዓመት በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ይከበራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በሰው ልጆች አመጣጥ ጥናት መስክ ውስጥ አለማቀፍ ቁልፍ ግኝት እንደሆነች የሚነገርላት ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሬተ-አካል በአፋር ክልል ሃዳር የተባለ አካባቢ በቁፋሮ የተገኘበት 40ኛ ዓመት በያዝነው ወር በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ እንደሚከበር ሳይንስ ኒውስ ድረገጽ ዘገበ፡፡
ዶናልድ ጆንሰን እና ቶም ግሬይ በተባሉ አንትሮፖሎጂስቶች እ.ኤ.አ በ1974 የተገኘችውና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አመታት በፊት በሁለት እግሮቿ ትራመድ  የነበረችው ሉሲ፤ የሰው ልጆችን አመጣጥ በተመለከተ ቀደም ብሎ የነበረውን አስተሳሰብ የቀየረችና ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያረጋገጠች ታላቅ ግኝት መሆኗን ዘገባው አስታውቋል፡፡
ሉሲ ከመገኘቷ በፊት “የሰው ልጆች መገኛ አውሮፓ ነው አፍሪካ?” የሚል ክርክር እንደነበር ያስታወሱት የግኝቱ ባለቤትና በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጆች መገኛዎች ኢንስቲቲዩት መስራችና ዳይሬክተር ዶናልድ ጆንሰን፤ የእሷ መገኘት በመስኩ የነበረውን አመለካከት በወሳኝነት እንደቀየረው ለዘ ታይምስ ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
ሉሲ በአንትሮፖሎጂ የጥናት መስክ ቁልፍ ሚና እንዳላት የገለፁት ዶናልድ፤ የሰው ልጆች አመጣጥ ታሪክን የቀየረችው ሉሲ የተገኘችበት 40ኛ ዓመት በዚህ ወር በዩኒቨርሲቲው በሚካሄዱ ውይይቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡

Read 4111 times