Print this page
Saturday, 08 November 2014 11:19

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፍተሻ ላቦራቶሪ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

                  ለፈረንሳይ ቡና ያቀርብ የነበረ አንድ ቡና ላኪ ድርጅት “እናዝናለን፣ ያቀረብከው ቡና የአገሪቱን የጥራት ደረጃ መመዘኛ ስለማያሟላ ልንቀበልህ አንችልም” ተብሎ፣ ቡናውን ይዞ መመለሱን አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ በምታቀርባቸው የተለያዩ የግብርና ምርት ውጤቶችም ላይ ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚከሰቱ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
ለአንድ ነጋዴ ወይም የቢዝነስ ሰው፣ ለውጭ ገበያ የላከው ምርት “የእኛን አገር የጥራት ደረጃ (ስታንዳርድ) አያሟላም” ተብሎ ውድቅ ሲደረግበት ከሚደርስበት ኪሳራና ውርደት፣ እፍረትና ቅሌት፣ … የበለጠ አደጋ ያለ አይመስለኝም፡፡
ለምርት ግዢ፣ ለዝግጅት፣ ለትራስፖርት፣ ለሰራተኞች ደሞዝ፣ ለመንግስት የሚከፈል ግዴታ፣ … አጠቃላይ ወጪውን ከመክሰሩም በላይ ከንግድ ሸሪኩ ጋር ከተስማማበት የጥራት ደረጃ በታች በማቅረቡ እምነት የሚጣልበት ስላልሆነ ውላቸው ይፈርሳል፡፡ የችግሩ ምክንያት የግብርና ምርት ውጤቱ ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት የተቀባዩን አገር ስታንዳርድ ወይም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ “ያሟላል” ወይም “አያሟላም” የሚል ተቋም ወይም ላቦራቶሪ በአገር ውስጥ ባለመኖሩ ነበር፡፡
አሁን ይህን ችግር የሚቀርፍ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የመመርመሪያ (የፍተሻ) ላቦራቶሪ በአገር ውስጥ ተቋቁሟል፡፡ ብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ ሰርቪስ ኃ.የተ.የግ.ማ ይባላል፡፡ ላቦራቶሪው “በለጠና ቤተሰቡ” የተባለ አገር በቀል ድርጅት 51 በመቶ፣ ኢኒክስ ዴቨሎፕመንት (Onyx Development) በተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ 49 በመቶ ድርሻ በመያዝ፣ በ80 ሚሊዮን ብር በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት በክብር እንግድነት ተገኝተው ላቦራቶሪውን  የመረቁት በምክትል ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል ናቸው፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር አገሪቷ፣ ሁለተኛውን ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ብቃት ያላቸውን ላቦራቶሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በምትፈልግበት ወቅት፣ “ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ”  በመቋቋሙ፣ የምግብ ደህንነትን፣ ጥራትና የኑትሪሽን ይዞታቸውን በማረጋገጥ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ የምግብ ንግድ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል፡፡
ብሔራዊ የምግብ ኑትሪሽን ፕሮግራምን፣ የምግብ ዋስትና፣ የኤክስፖርት፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የዕድገት ስትራቴጂዎችን እንዲሁም የጥራት መሰረተ ልማትና ከሁሉም በላይ ሁለተኛውን ምዕራፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እውን ለማድረግ የብሌስ ላቦራቶሪ ተልዕኮና ራዕይ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ መንግስት፣ ላብራቶሪውን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም አለው ብለዋል፤ ዶ/ር ደብረጽዮን፡፡
በብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ ሰርቪስ የቴክኒክና የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ሙላት አበጋዝ፤ የብሌስ ላቦራቶሪ ለአገሪቷ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ በምግብ ደህንነት ጉድለት የሚመጡ ችግሮችን በላቦራቶሪ በመፈተሸ ለህብረተሰቡና ለአምራቾች፣ ለመስሪያ ቤቶችና ለመንግሥት ማሳወቅ ነው ብለዋል፡፡
ብሌስ፣ ይህን ተግባር እውን ለማድረግ የፍተሻ ላቦራቶሪ ማደራጀቱን የጠቀሱት ዶ/ር ሙላት፣ በተወሰኑ ፍተሻዎች ላይ ማለትም የካንሰር መንስኤ እንደሆነ የሚነገረውን በጥራጥሬ ምርቶች ውስጥ የሚገኘውን አፍላቶክሲን እንዲሁም ለካንሰር በሽታ ምክንያት ይሆናል የተባለውን በቡናው ውስጥ የሚገኝ አክራቶክሲን የተባለ ኬሚካል በመለየትና የማይክሮ ባዮሎጂ ምርመራዎች በማድረግ ከአይኤስኦ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
ማይክሮ ባዮሎጂ ሲባል የምግብ ወለድ በሽታ የሚሆኑትን ባክቴሪያዎች መለየት የሚያስችል አቅም አጎልብቷል ማለት ነው፡፡ የምግብ ደህንነትን በመለየት የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የመጀመሪያው ሥራችን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአገራችን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት (ማልኑትሪሽን) አለ፡፡ ላቦራቶሪው ይህን የምግብ እጥረት መፈተሽ የሚያስችል አቅም አለው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚቀርቡልንን ምግቦች የፕሮቲን፣ የስብ (ፋት)፣ የካርቦሃይድሬትና የኢነርጂ፣ … ይዘት ወይም መጠን መፈተሸ እንችላለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ወደፊት ደግሞ ከአውሮፓ የገዛናቸው መሳሪዎች ተተክለው ስራ ሲጀምሩ ቫይታሚን፣ አሚኖ አሲድ፣ ፋቲ አሲድ፣ ስኳር፣ … በተባሉ ዘርፎች ሰፊ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ይህም ፋብሪካዎች፤ ህብረተሰቡ የተመጣጠነ የምግብ ይዘት እንዲያገኝ የሚያስችል ምግብ እንዲያመርቱ ያግዛቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሶስተኛው የላቦራቶሪው ተግባር የኤክስፖርቱን ዘርፍ ማገዝ ነው ያሉት ዶ/ር ሙላት፤ አገራችን ወደ ውጭ የምትልካቸው በርካታ ምርቶች አሉ፡፡ እዚህ ምርቶች በላቦራቶሪ ደረጃ ተፈትሸው ይዘታቸው ካልታወቀ በስተቀር፣ የውጭ ገበያ አግኝቶ ለመወዳደር አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ከ30 በላይ ኢንዱስትሪዎች፣ አምራቾችና የተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሲልኩ የምግብ ደህንነት ህክምና፣ ጥራትና ቀመሩን በመስጠት ከፍተኛ እገዛና እየሰጠን ነው፡፡
ሌላው ደግሞ የተደራጀ የሥልጠና ማዕከል አዘጋጅተናል፡፡ ወደፊት፣ ለተጠቃሚው፣ ለኢንዱስትሪው፣ ለአምራቾችና ለመንግስት መ/ቤቶች፣ … ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በተጨማሪም የምርምርና የልማት ማበልፀጊያ ማዕከል አለን፡፡ በዚህ ዘርፍ ከራሳችን በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከምርምር ማዕከላት ጋር ለመተባበርና እሴት በሚጨምሩ ነገሮች  ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ዝግጅታችንን አጠናቀናል በማለት ላቦራቶሪው የሚሰራቸውን ዋና ዋና ተግባሮች አስረድተዋል፤ ዶ/ር ሙላት አበጋዝ፡፡
ላቦራቶሪው የተሟላና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ነው ስንል፣ በመፈተሻ መሳሪያዎች ብቻ ሳይሆን በባለሙያዎችም ጭምር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የምንወዳደረው ብዙ ልምድና እውቀት ካላቸው ዓለም አቀፍ ላቦራቶሪዎች ጋር ነው፡፡ የእኛን የፍተሻ ውጤት የተጠራጠረ አካል፣ በሌላ ላቦራቶሪ አስመርምሮ ውጤቱ እኛ ከሰጠነው ጋር ተመሳሳይ ካልሆነ አደጋ አለው፡፡ ስለዚህ ባለሙያዎቻችን በሙሉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ከመሆናቸውም በላይ ልዩ የላቦራቶሪ ፍተሻ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፤ ወደፊትም ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የእውቀት ማሻሻያ የሥራ ላይ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡
ላቦራቶሪው እስካሁን ድረስ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የግብርናና የምግብ ምርቶችን ናሙና ለመፈተሽ ወደተለያዩ አገሮች በሚደረግ ጉዞ የሚባክነውን ጊዜ ያስቀራል፡፡ ወጪን ይቀንሳል ያሉት የላቦራቶሪው ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሕሊና በለጠ፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የግብርናና የምግብ ምርቶችን ደህንነትና ጥራት ለማረጋገጥ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ሕሊና፣ አስተማማኝና ጥራት ያለው የፍተሻ፣ ምርምርና ስርፀት፣ የስልጠናና የኮንፈረንስ አገልግሎት በመስጠት፣ በግብርና ምርት ዘርፎች በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አምራች አርሶ አደሩን፣ የምግብ ነክ ፋብሪካ ባለሀብቱን፣ የምግብ ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪውን፣ ነጋዴውና ህብረተሰቡን ማስተባበር ዋናው ዓላማቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመልማት ላይ ባሉ አገሮች በተመጣጠነ ጤናማ ምግብ እጥረት በርካታ ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው ይሞታሉ ያሉት ስራ አስኪያጇ፤ በኢትዮጵያም በዚሁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት 67 በመቶ ህዝብ ለአቀንጭራ የተጋለጠ ሊሆን፣ አኀዙ በአሁኑ ወቅት በህፃናት ወደ 44 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአካልና በበሽታ መልኩ 54 በመቶ ህፃናት ለአኒሚያ ወይም በተለምዶ ደም ማነስ እየተባለ ለሚጠራው በሽታ የተጋለጡ እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ ሕሊና፤ በእውቀት፣ በአዕምሮ ብስለትና በምርታማነት ዝቅተኛ እንድንሆን አድርጎናል በማለት አስረድተዋል፡፡
ሀገራችን ይህንን ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ ችግር ለመቅረፍ ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም የእርሻና የምግብ ውጤቶች ምርትና ኤክስፖርት ንግድ ሁለተኛውን ዙር የዕድገት ፕላን ያዘጋጀች በመሆኑ ብሌስ ይህንን ራዕይ ለማሳካት፣ በግብርና፣ በምግብ ውጤቶች፣ በውሃና አፈር፣ በምግብ ደህንነትና ጥራት፣ በእንስሳትና ዕፅዋት ጤንነት፣ በምግብ ምርት ቴክኖሎጂ፣ በላቦራቶሪ ፍተሻ፣ በስነ-ምግብ ቀመር… አያያዝና አጠቃቀም… ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል አቅም ማዳበሩን ስገልጽ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል፡፡   

Read 1562 times