Saturday, 08 November 2014 11:16

የጉራጌ አገር ጉዞዬ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(3 votes)

      “አሜሪካ የሚኖሩ የዘሙቴ ማህበር አባላት ‘በዘንድሮው ጉዞ’ ቀንተናል ይላሉ” ብሎ ወዳጄ አጫወተኝ… ዳኜ፣ ድርሻዬ (የካርታው መሀንዲስ)፣ እንዳለ (ቂሾ) ይባላሉ፡፡ የዓመት ሰው ብሏቸው ቢመጡ ደስታዬ ነው፡፡
ዘሙቴ ውስጥ፤ ገና ካፋፍ ላይ ሆነን፣ የአቶ አበበ ወ/ማርያም ቤት ከሩቅ የተንጣለለ ግቢውን በስፋት ዘርግቶ ይታየናል፡፡ ትልቁ ልጃቸውን ግርማን ስለዘሙቴ ቤታቸው ነገረ-ሥራ ጠየኩት፡፡
”ግርማ አበበ ወ/ማርያም ደንቢሶ እባላለሁ” ብሎ ጀመረ፡፡ “ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ በ1952 ነው የተወለድኩት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የተወለድኩት፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ቀበሌ 26፡፡ ይችን ሀገር የማውቃት የአባቴ አጎት ሞተው ለለቅሶ መጥቼ ነው - በ1980ዎች፤ 20 ዓመት አካባቢ፡፡ ከዚያ በኋላ መጥቼ አባቴ ይህን ቤት በ1964 ዓ.ም ሣር የነበረውን ቆርቆሮ ቤት አርጎ ሠራ፡፡ እሱ የተወለደው እዚህ ነው፡፡
“አባቴ እዚህ ነው ከናቴ ጋር ከሚስቴ ጋር እዚህ እኖራለሁ” ብሎ መኖር የጀመረው፡፡ እዛው አዲስ ከተማ ሆኖ መርካቶ ሱቅ ነበረው፡፡ ክፍለ ሀገርም ይነግድ ነበር፡፡ እዚህ እንደማንኛውም ሰው ነበር የሚኖረው፡፡ እንሰት ይፍቅ ነበር፤ ጎበዝ ገበሬ ነበር ይባላል፡፡
ከዚያም ቤቱን እየተመላለሰ ያይ ነበር፡፡ “ምን ይሻላል ቤት እንስራ?”  ስንለው “የለም እኔ ሰርቻለሁ” አለን - እዚህ ያንን ቤት ሰርቶ ስለነበር፡፡ በጣም ጎበዝና ታታሪ ገበሬ ነበር አባታችን! ዘመዶቹን ይወድ ነበር፡፡ ያለውን ሁሉ ለዘመዶቹ ይሰጥ ነበር፡፡ የሚያገቡም ሰዎች ካሉ ልብስ ገዝቶ፣ ከብት ገዝቶ ይሰጣል፡፡ እዚህም ሲመጡ ተቀብሎ፤ ሥራ ለሚፈልጉ ስራ ሰጥቶ፣ መማር ለሚፈልጉ ት/ቤት አስገብቶ ያስተምር ነበር፡፡ ደርግ መጣና መሬትና ቤት ወሰደበት፡፡ ታመመ፡፡ ቤት መዋል ጀመረ፡፡ በጣም ይበሳጭ ነበር፡፡ የሚያከራየውም ቤት ነበረው፡፡ ሱቁንም ወሰዱበት፡፡ ከዛ ተበሳጨ፡፡ ታመመ በቃ፡፡ ቤት ዋለ፡፡ እኛም አይዞህ እያልን ትምህርታችንን እያቋረጥን ወደ ሥራ ገባን! 4 ወንዶችና 2 ሴቶች ነን፡፡ አንዷ ሴት በህመም ሞተች፡፡ አባቴ በ1920 ተወልዶ በ1995 ዓ.ም ሞተ፡፡ እናታችንም በ99 ዓ.ም ሞተች፡፡ እሷ እንኳ እነኚህን ቤቶች ሁሉ አይታለች የተሰሩትን፡፡ እኔንም የዳረችኝ እዚሁ ቤት ነው፡፡
“አባቴን ምን እናርግልህ? አልነው”
“አግቡ! በተለይ አንተ አግባ!” አለኝ፡፡
“እሺ ብዬ፤ እሱ እንደፈለገው በባህላዊ መንገድ እዚሁ ዘሙቴ ላገባ ወሰንኩ፡፡
እሺ ብዬው፤ ልጅ እንግዲህ ያባቱን ቃል በመሙላት ላይ ታች ይላል አደለ?... በማህል ታመመ፡፡
የኔንም ሰርግ ሳያይ እሱ አረፈ! በ95፡፡ እኔ በ97 አገባሁ፡፡ እዚህ ቤት፡፡
ይሄንን ቤት ያሰራነው እኔ፣ ኪዳኔ … እናታችንም ነበረች፡፡ እናታችን ቆማ ነው ያሰራችው፡፡ ሀሳብ እያቀረበች እንዲህ ይሁን እያለች … ፊቱ ወዲህ ይሁን እያለች፡፡ ጓዳ ይኑረው እያለች ነው ያሰራችው፡፡ በራሷ ፕላን! በጣም ጭምት ነች፡፡ ያዲሳባ ልጅ ነች፡፡ ወላጆቿ ደብረ ዘይት ሆነው ከአዲስ አበባ ደብረ ዘይት ሄዶ አምጥቶ ነው አዲሳባ ያገባት፡፡ በ1933 ጣሊያን ሲወጣ ነው የተወለደችው፡፡ ከሱ ጋር የተጋባችው በ1950 ነው፡፡ እኔን በ1952 ወለደች፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ! ቀጥሎ አስቴር አበበ፣ የሷ ታናሽ ያረፈችው ናት፡፡ ከዛ ኪዳኔ ነው፡፡ ከዛ ወርቁ ይሄይስ መጨረሻ ዮዲት ናት! እንግሊዝ ናቸው ሁለቱ፡፡ ትዳር አላቸው ልጅ ወልደዋል፡፡
እናታችን እኛን ለማሳደግ ያላረገችው ነገር የለም፡፡ ትነግድ ነበር ከተማ መርካቶ፡፡ አንድ ወቅት አባታችን ታሞ እሷ ነበረች የምታኖረን፡፡ ሥራ እንድንለምድ አረገች፡፡ በኋላ እሷን ንግዱን እንድትተው አደረግናት፡፡ አባታችንን አንቱ ነው የምትለው፡፡ አባታችሁ እንዲህ ይሉ ነበር “እንዲህ አረጉኝ! እኔ ለማንም ክፉ አላረኩም! “ክፉ እንደሰራ ሰው ቤቱ ጠፋ” እያለ ይጨነቅ ነበር! ግዴሎትም ይሰራል ብላ፤ ቃሉ ተጠብቆ እንዲሰራ ያረገች እሷ ነች! በ99 ዓ.ም እኛ አገር ቤት ገብተን፣ ለመስቀል፣ እሷን እዛ ቻዎ ብለናት ሁሉን ነገር ሸክፋ አዘጋጅታልን፤ ሁሉን ይዘን ገብተን፤ በድንገት ሞተች ተብሎ ሰው ተላከብን፡፡ ተነስተን ሄድን መስከረም 14 ደብረሊባኖስ ተቀበረች፡፡ በ1999 ዓ.ም፡፡
በዓመት ሶስቴ ያህል ወደ ዘሙቴ እንመጣለን፡፡ ባለቤቴ 4ቴም 5ቴም ትመጣለች፡፡ ለመቆጣጠር፡፡ አንዳንዴ ሁላችን ተሰብስበን እንመጣለን፡፡ ለምሳሌ  በ2006 ወደ 4 ጊዜ መጥተናል፡፡ ማህበሩም ይመጣል፡፡ ማሪያምን እያስቀደሰ ይሄዳል፡፡በሰርጌ ሰሞን በ97 15 ቀን ቆየን! በ1997 ሰዉ ሲተራመስ እኔ እዚህ ነበርኩ፡፡ ሰርጌ ሚያዚያ 30 ነበር ይገርምሃል! ከአንድ ሳምንት በፊት ቀድመን ገብተናል እዚህ፡፡ 15 ቀን ቆይተን ነው ወደ ከተማ የሄድነው፡፡ ምንም የአዲሳባን ግርግር አላየንም፡፡”
የግርማና የባለቤቱ ፎቶግራፍ ግድግዳው ላይ ይታያል፡፡ እሱን እያሳየኝ “የመጀመሪያው ዕለት በባህላዊ መንገድ፣ በሁለተኛው ቀን ደግሞ በዘመናዊ፣ በዚህ አይነት አለባበስ ተጋባን፡፡ ሰኞ እለት፡፡ ባህላዊ ማለት ነጭ በነጭ ተደርጎ እጀ ጠባብ ተለብሶ፤ በፈረስ ሆነን፡፡ የእሷ አባቷ ቤት እዛ ነው፡፡ ከእኛ ጋር ዳገት አትወርድም፡፡ ገብሬል ነው ቤቷ፡፡ ባለቤቴ ዘሙቴ ናት! እዛ ነው ያገኘሁዋት፡፡ እኔ ምንድን ነው አስብ የነበረው ከተማ በፍቅር-ጓደኝነት ኖሬ ትዳር መመስረት ነበር- እንደከተሜ! አባቴ ካለኝ በኋላ ግን የትዳርን ምርጫ ለእግዚአብሔር ነው የሰጠሁት! እንደባህላችን ሽማግሌ ጠራሁ፡፡ ትዳር እፈልጋለሁ…  ሀብታም አልልም፣ ደሀ አልልም ቆንጆ ፉንጋ አልልም የጥሩ ቤተሰብ ልጅ ብቻ ፈልጉልኝ አልኳቸው… ተገኝቷል ተባለ - ልይም አላልኩም! በእውነት እግዚአብሔር ነው የሰጠኝ - መቼ እንዳየሁዋት ታውቃለህ? ሰኞ ማታ!” “ዕውነትክን ነው?” አልኩት ተገርሜ፡፡ “እግዚአብሔርን! እኔ እንግዲህ የከተማ ልጅ ነኝ! ነገር ግን አባቴ አከረረውና አግባ ስላለኝ በቃ! እሱ የታየው ነገር አለ ማለት ነው! እና ይሄንን ነገር እግዚአብሔርን ነው የለመንኩት፡፡ ያልኩትም አልቀረ በጣም ታዛዥ ቆንጆ ልጅ ሰጠኝ፡፡ ትዳሬ ቆንጆ ነው፡፡ እንደውም እቤቴ ስገባ እናቴ ያለች ያለች ነው የሚመስለኝ! (በዚህ ዘመን አይታሰብም) እኔ ሚስት አልመረጥኩም! አሁን ሁለት ልጆች አሉኝ - የ8 እና የ 7 ዓመት፡፡
ያሬድ ሚዜዬ ነው፡፡  መረቀልኝ ሚዜዬ ነው! ወንድሙም ሚዜዬ ነው፡፡ (እነዚህ የማህበሩ አባላት ናቸው እንግዲህ)
97ን ሸውዳችሁ እዚህ አሸሸ ገዳሜ አላችሁ አይደል ስለው ያሬድን፡-
“ቶራ ቦራ እኮ ነው ይሄ!” አለኝ፡፡ ተሳሳቅን!
ቅድመ-አያታችን ደምቢሶ ናቸው ቦታውን የያዙት፡፡ የአባታቸው አገር ዋጮ አካባቢ ነበር፡፡ የቄስ ግብዝና ግማሽ ጋሻ መሬት ተሰጥቷቸው እዚሁ እያገለገሉ ትዳር ያዙ፡፡ ልጆች ወለዱ፡፡ ለያንዳንዳቸው ከፋፍለው ሰጡ፡፡ ይሄ ያያታችን ድርሻ ነው - አያታችን ላባታችን ሰጡ፡፡ እነገድር ገበሬ ማህበር ስር ነው ዘሙቴ ያለው! ወረዳው ቡኢ ነው፡፡ ችግር ካለ ከገበሬ ማህበሩ፣ ከፍ ካለ ቡኢ እንሄዳለን፡፡ ሶዶ ነው ህዝቡ!
እንግዲህ ያን ግቢ ያለምክንያት አልጠቀስኩትም፡፡ የተቀደሰ ግቢ ነው፡፡ የዘሙቴ ማርያምን በዓል ልናከብር የመጣነውና ያረፍነው የአቶ አበበ ወልደማርያም የተንጣለለ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ቀይ ቆርቆሮው የታየን ገና ከላይ ከጋራው ስንንደረደር ነው፡፡ ዐርበ -ሰፊ ተደርጎ በዘመናዊ ሞድ የተሰራ ሰፊ ቤትና በጉራጌ ባህላዊ አሰራር የተሰራው ሌላው ማረፊያችን ጎን ለጎን ናቸው፡፡ የፍራሽ መአት ዙሪያውን ተሰድሯል፡፡ መልበሻ ክፍል መሳይ ጓዳም አለ፡፡ እዚያ ሻንጣችንን አከማቸን - ልብሳችንን ቀየርን፡፡ ማሪያም ዕሮብ ነው የምትውለው፤ ዛሬ ማክሰኞ ነው፡፡ መስከረም 20፡፡ አረፍ አልን፡፡ ቡና ተፈላ! እንግዲህ ድግሱ ጀመረ!
ያ “ይጠጣል እንጂ አይበላም” የተባለው ክትፎ በአይኔ ላይ ይዞር ጀመር፡፡ ጣባ ጣባችንን ያዝን፡- ዐይቤው፣ ጎመኔው፣ ሌላው ቅጥፍ-ጎመን በአውሮፕላን እንደተሰራ የከተማ ካርታ በድንበር በድንበር ተለይቶ፣ ግን ኩታ ገጠም ሆኖ፤ በገዛ ጣባው ከች አለ፡፡
ክትፎው በራሱ ጊዜ ቆይቶ መጣ፡፡ አፕሬቲቭ ይመስል ዐይቤና ቆጮ መጀመሪያ መጥቷል!
ከዚያ ማወራረጃ የእህል አረቄ ቀጠለ፡፡ ሌላ ዘመናዊ ከባድ ከባድ ማወራረጃም ተንቆረቆረ/ፈሰሰ፡፡ ያለፈው የመስቀሉ መንፈስ እዚህ ዘሙቴ ገና እየተሟሟቀ ነው!   
እነሆ፤ ማስቀደስ፣ ክትፎ መጠጣትና መዝናናት የራሱ መንፈስ አለው! የበዓል ውሎ ሥርዓት መርሆው ይሄ ነው!!
የዘሙቴ ማርያም ዓመታዊ ክብረበዓል ደስ ይላል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ቀሳውስት እየቀደሱ ነው፡፡ ታቦት ሊወጣ ጥቂት ሰዓት ቀርቶታል፡፡ ዙሪያውን በአረንጓዴ ተራራ ተከባ በዛፎች ታጅባ የምትገኘው ጎጆ ቅርፅ ያለባት ባለቆርቆሮ ማርያም ቤተክርስቲያን ልትነግሥ እያኮበኮበች ናት፡፡ ሰው ከርቀት አቅጣጫ በመምጣት ላይ ነው፡፡ እኛ በእንሰት ማህል በቀጫጭን መንገዶች ነው ቁልቁል የመጣነው፡፡ ዓይን የሚያለመልመውን ዛፍ እያየን ለምልመናል፡፡ ይህን ግጥም የፃፈኝ ይሄ የዐይን ትፍሥህት ነው፡፡
“ልብ ሁሉ ለምለም ነው፣ ጉራጌው ፍቅር
ከቅዳሴው ጋራ መንፈሱ ጭምር
ዕምነቱ ኬላ ነው፣ ማተቡ ድንበር፤
ከመሬቱ ደሞ አረንጓዴ ጤፍ
ደሞ ከዚያ በላይ አረንጓዴ ጋራ
ሰማያዊ ሰማይ ከጋራው በላይ
አምላክ አትግደለኝ ዘሙቴን ሳላይ” የሚያሰኝ ነው በሙሉ ቀን መለሰ ቅኝት፡፡ ገበሬዎች ሞባይል ሲሞክሩ አያለሁ፡፡ ሥልጣኔያቸው ደስ አለኝ፡፡ በተክሲያኑ ግቢ ውስጥ አራት አምስት ቤቶች አሉ፡፡ አንድ ረዘም ያለ ቤት ሰምበቴ ቤት ይመስላል ምግብ ያበሳስላሉ - ምናልባት ለበኋላ ጠበል     ፀዲቅ ይሆናል፡፡ ሰፊ ክብ ግቢ ነው፡፡ አስቀዳሹ ምዕመን ቀድሞ ገብቷል፡፡ ውጪ ትንሽ ሰው ነው ያለው፡፡ የጄነሬተር ድምፅ አለ፡፡  በክር አውታር የተንጠለጠሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የጌጥ አርማዎች በሦስት አውታሮች ይታያሉ፡፡
ዘማሪያን ወጡ፡፡ ሰው ከየት መጣ ሳይባል ግቢውን ሞላው፡፡ ነጫጭ ልብስና ልብሰ ተክህኖ ፈካ፡፡ ዣንጥላው፣ ከበሮው፣ ባንዴ  እርግብግብታ ፈጠረ፡፡
“እኔስ ማርያምን እወዳታለሁ
እመቤቴ እላታለሁ!”
ዘሙቴ ማርያም አቤት ማማሯ
የዘሙቴ ሆነናል… አሁን አምረናል …” ታቦቱ ወጣ፡፡ ታቦቱ የቤተ ክርስቲያኑን አጥር ሊዞር ነው፡፡ ይኸው ታቦቱን እየተከተልኩ ነው፡፡ ጧፍ በየእጁ ላይ ይንበለበላል፡፡ ችቦ ይተኮሳል! እጅግ ደማቅ መልክ ነው ያለው፡፡ ከታቦቱ ጀርባ የጉራጌ ባህላዊ እጀባ አለ፡፡ ድንጋያማ ቁልቁለት አለ፡፡ ለኔ ነው እንጂ አገሬውማ የለመደው ነው፡፡ ቃጭል፣ ሆታ፣ በቀለም የደመቀ ታቦት!  “ኤቦ” ይላል ያገሬው እጀባ ዜማ! ይሄኔ ባለቤቴና ሌሎች ወዳጆቻችን ከአዲሳባ መጡ፡፡ ደርሰውበታል ታቦቱን፡፡ ቅዳሴ ገቡ፡፡
 “ባለቤቱ ስትመጣ ዕውነተኛ ሳቅ ሳቀ” ብሎ ያሬድ የተባለ ወዳጃችን ቀለደብኝ፡፡ ሴቶች የበዙበት መዘምራን… የባህል ዜማና አገሬው… በአረንጓዴ የተከበበ ባለፀዳለ-ሞገስ ታቦት! እንግዲህ ዑደተ-ታቦቱ ሂደቱን ጨረሰ - ነገሠ! በመጨረሻ እርዳታ ያደረጉ ሰዎች ዝርዝር ተነበበ፡፡ ይገርማል፤ ሰው እጣን እዚያው ገዝቶ እዚያው ይለግሳል፡፡ ዕምነት ማለት ይሄ ነው! ዕሮብ ስለሆነ ቅዳሴ ተገባ! እኔ ወደማረፊችን ሄድኩ፡፡
ይቀጥላል

Read 4114 times