Print this page
Saturday, 08 November 2014 11:11

‘የቻይና ሆድ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(21 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው… አለ አይደል…ፊቱ የሚያስፈራ…፣ “አጠገቡ ምግብ አይበላም…” የሚባል አይነት ነው፡፡ እናማ አንዱን እንዲህ ይለዋል…
“ለመሞት ተዘጋጅ፡፡”
“ለምን?”
“እኔን የሚመስል ሰው ካገኘሁ ከዚህ ዓለም አሰናብተዋለሁ ብዬ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፡፡”
“አንተን እመስላለሁ እንዴ?”
“ቁርጥ እኔን ነው የምትመስለው፡፡”
“እንግዳው ከዚች ዓለም አሰናብተኝ፡፡”
እንዲህ ከመባል ይሰውራችሁማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ ምነዋ የራሳችንን መልክና ቁመና የምንጠላ ሰዎች በዛንሳ!
ሰውየው ሞቅ ብሎት ቤቱ ይገባል፡ ግድግዳው አጠገብ ተጠግቶ አፍጦ ሲያይ ይቆያል፡፡ ከዛም ለሚስቱ… “ይሄ ግድግዳው ላይ ፎቶው የተሰቀለው አስጠሊታ ሰው ማነው?” ይላታል፡፡ ሚስትም…“ፎቶ አይደለም፡፡ በመስታወት የራስህን መልክ እያየህ ነው…” ብላው አረፈች፡፡ ሌላ ልጨምርላችሁ…ሰውየው ጓደኛው ላይ ‘ሙድ ለመያዝ’ …“አንድ ጊዜ ልክ እንዳንተ ችምችም ያለ ጢም ነበረኝ፣፡ እንዴት አስጠሊታ እንደመሰልኩ ሳይ ግን ሙሉ ለሙሉ ተላጨሁት፡፡”
ጓድኝየው ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው…“እኔም አንድ ጊዜ ያንተን የሚመስል ፊት ነበረኝ፣ ግን እንዴት አስጠሊታ እንደመሰልኩ ሳይ ጊዜ ፊቴን ለመሸፈን ጢሜን አሳደግሁት፣” ብሎት እርፍ፡፡
እናማ…‘ሙድ የሚያዝበትን’ ሰው መምረጥ አሪፍ ነው፡፡
ስሙኝማ… ዛሬ ከረባት ሆዱ ላይ ‘ጣል’ አድርጎ ሲንጎማለል እይታችሁት በማግስቱ ደግሞ ሆድ የሚባል ነገር ያጣችሁበት ሰው ገጥሟችሁ አያውቅም! ነገርዬው እንዴት መሰላችሁ…ሠርግ ላይ ወይም ሌላ ሰው ለሰው የሚተያይበት ስፍራ ሲሆን ከረባቷ ትደረግና ሆድ ላይ ደገፍ ትላለች፡፡ (“‘ቦርጭ’ ለከረባት ነው ይባል የለ! የምንታውቀው ሰው ሆድ በአጭር ጊዜ ተጠቅለሎ፣ ተጠቅለሎ ያያቸ አንዲትሴተ ምነ አለች አሉ መሳለችሁ…እኔ ሳውቀው እኮ አንድ ሆድ ብቻ የበረው ጊዜ ነው አለች አሉ፡፡)
ታዲያላችሁ…በማግስቱ ከረባት ማድረግ በማያስፈልግበት ጊዜ ሆዷም ከከረባቱ ጋር አብራ ‘ትወልቃለች’! ልክ ነዋ…ነገርዬው ምን መሰላችሁ… ሰዎች ጥብብ ያለች ካናቴራ ይለብሳሉ፡፡ ይሄኔ ሆድ እንደ አቅሚቲ ‘ትቆዘራለች’፡፡ በዚህ ጊዜ ‘ቦርጭ’ መሰለች አይደል! (አሁን፣ አሁን ደግሞ ከመጥበቧ የተነሳ ‘ደም ስር ልትዘጋ የምትችል’ የመሰለች ካናቴራ ለብሰው ‘ደረት የሚገለብጡ’ ጎረምሶች ገጥመዋችሁ አያውቅም!)
እናላችሁ…የዚች አይነት ስትፈለግ ብልጭ የምትል፣ ስትፈለግ ደግሞ ‘የምትሰወር’ ሆድ ምን ትባላለች መሰላችሁ… ‘የቻይና ሆድ’! አሪፍ አይደለች!
እናላቸሁ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ‘የቻይና ሆድ’ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ያያችሁት መልካም የሚመስል ነገር በማግስቱ አይደገምም፡፡ አንድ ሰሞን እገራቸው እስኪቀጥን እየተሯርጡ የሚያገለግሏችሁ የሆነ ድርጅት ሠራተኞች በአራተኛው ቀን…የዲያብሎስ ዕቁብተኞች ሆነው ቁጭ ይሉላችኋል፡፡ መሯሯጡ ‘የቻይና ሆድ’ አይነት ነገር ነዋ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የአንዳንድ ዘፈኖቻችን ስንኞች ይለወጡልን፡፡ ለምሳሌ…
አሁን የእኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ
ጉች፣ ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ፣
የሚለው ስንኝ ይለወጥልንማ፡፡ አሀ፣ ልክ ነዋ!…ዘንድሮ ጉች፣ ጉች ያለ ጡት ‘ከመርካቶ ይሸመታላ!’ “አየሀት ያቺን ሴትዮ፣ እንደ አሜሪካን ፓትርዮት ሚሳይል ነው እኮ የደገነቻቸው…” የሚባለላቸው ነገረዬዎች የእውነትም እንደ ሚሳይሎቹ ‘የተተክሉ’ ሊሆኑ ይችላሉ! እናማ… የዚህ አይነት ጉች፣ ጉቾች ምን ይባሉ መሰላችሁ…‘የቻይና ሆድ’!
ለምሳሌ… አለ አይደል… “እንደው ፈጣሪ ሙሉ ቀን እነሱን ሲያሰማምር የዋለ ነው እኮ የሚመስለው…” የሚባልላቸው የአንዷን እንትናዬ የዓይን ሽፋሎች ታያላችሁ፡፡ እናማ…የእኔ ቢጤ ሞኝ… አለ አይደል… “የዓይኖቿ ሽፋሎች ልቤን አርገብገበው…” ምናምን ብሎ አዝማሪ ቤት ስንኝ ሲያስቋጥር ያመሻል፡፡ ‘የቻይና ሆድ’ መሆናቸውን አላወቀማ!…ሽፋል ‘ከመርካቶ ይሸመታላ!’
“አቤት ዳሌና መቀመጫ! ዚታዎ ከእነሪሞርኪዮ ነው የሚስለው፡፡ ሰው እንዲህ ተስተካከሎ ይወለዳል!”  ወይንም… እንደ ሆሊዉድ አክተሮች በሁለት ጎኗ ትላልቅ የማካሮቭ ሽጉጦች የታጠቀች ነው እኮ የሚመስለው…!” ብሎ ነገር አይሠራም፡፡ ዚታዎ ከእነሪሞርኪዮ የሚባል ዳሌና ‘አክሰሰሪዎቹ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ‘ከመርካቶ ይሽመታሉዋ!’
እናላችሁ…የሆነ የውሀ ዋና ቦታ ወይም ‘እዛ ቦታ’ ጂንስ ምናምን ሆዬ ውልቅ ሲል “ዚታዎ ከእነሪሞርኪዮም” አብሮ ውልቅ! ‘የቻይና ሆድ’ ነዋ!
እንትና…እስቲ ፒያሳ ምናምን ብቅ በልና ‘ስማርት ፎን’ የሚባለው የእንትናዬዎች ቁመና ምን አይነቱ እንደሆነ ጠቁመኝማ፡፡ ‘ስማርት ፎን’ አሪፍ ስም ነዋ…
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የስማርት ፎን ምናምን ነገር ካነሳን አይቀር የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… በዘንድሮው ቴክኖሎጂ…ሞባይላችን ጠፍቶ እንኳን የምንናገረውን ነገር መስማት ይችላል የሚሉት እውነት ነው እንዴ! ማወቅ አለብና! ቴክኖሎጂው ሳይገባንስ!
ዘንድሮ እንደሁ…አለ አይደል…
ባልሽ ፊልድ ሊሄድ ስንቁ ሲሰናዳ
እኔ ጓሮ ሆኜ በሳቅ ለፈነዳ፣
አይነት ነገር ኋላ ቀር ሆኗላ! ዕድሜ ለሞባይል… “ሰውዬሽ ሲወጣ ምልክት አድርጊልኝ…” ማለት ይበቃላ! እናማ… በየቀኑ በሞባይል ስልክ መናገር የምንችላቸውና የማንችላቸው ነገሮች ተለይተው ማኑዋል ነገር ይዘጋጅልንማ! አለበለዛ… “ባልሽ ፊልድ ሊሄድ…” ምናምን ወደ ማለቱ እንመልሳለን፡፡
እናላችሁ…ምን ለማለት ፈለገ ነው  አይነት ነገር ነው፡፡ (ስሙኝማ…በቀደም በአንድ የኤፍ.ኤም. ሬድዮ ፕሮግራም ላይ ሥራ ሲለቅ “የመሥሪያ ቤቱን ዌብሳይት አስረክብ…” ስለተባለው ሰው ሰምተን ስንስቅ ከረምን ነው የምላችሁ፡፡ ስንቱን ጉድ ነው የምንሰማው!)
ሰውየው የ‘ገርል ፈሬንዱ’ን ፎቶ ለጓደኛው ያሳየዋል፡፡ እናማ…ጎራዳ የምንላት አይነት ነች፡፡ ታዲያላችሁ…ምን ይልላችኋል… “ገርሌን አየሀት፣ ልክ እኮ ከመንግሥተ ሰማያት ተወርውራ እቅፌ ውስጥ የወደቀች ነው የምትመስለው…” ይለዋል፡፡ ጓደኛ ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “አዎ ፊቷ ቀድሞ መሬት ላይ ያረፈ ነው የሚመስለው፣፡” ከእንዲህ አይነት ጓደኛ ይሰውራችሁ፡፡
ሰውየው የ‘ገርል ፍሬንዱ’ን ፎቶ ለጓደኛው ያሳየዋል፡፡ እናማ…ጎራዳ የምንላት አይነት ነች፡፡ ታዲያላችሁ…ምን ይልላችኋል… “ገርሌን አየሀት፣ ልክ እኮ ከመንግሥተ ሰማያት ተወርውራ እቅፌ ውስጥ የወደቀች ነው የምትመስለስው…” ይለዋል፡፡ ጓደኛ ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “አዎ ፊቷ ቀድሞ መሬት ላይ ያረፈ ነው የሚመስለው፣፡” ከእንዲህ አይነት ጓደኛ ይሰውራችሁ፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ነገር ብዙ ነገራችን ‘የቻይና ሆድ’ ሆኗል፡፡ ሰዉ ሁሉ እውነተኛ ራሱ ይሁን፣ የቻይና ሆድ ግራ የሚያጋባ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡  
አንድ ሰሞን ቢ.ፒ.አር. ምናምን የሚባል ነገር ተነሳና መሥሪያ ቤቶች… “ሀያ ቀን ይፈጅ የነበረውን በሀያ ደቂቃ ብቻ…” ምናምን እያሉ አገር ምድሩ “በሥራ ፍቅር” ትንፋሽ አጥሮት ነበር፡፡ ጥቂት ወራት እንዲህ ከሆነ በኋላ ነገሮች ወደነበሩበት ተመለሱ፡፡ መጀመሪያም ቢሆን ሩጫው ‘የቻይና ሆድ’ ነገር ነበራ!
ከ‘ቻይና ሆድ’ አስተሳሰብ የምንላቀቅበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 8513 times