Saturday, 08 November 2014 10:58

በ60ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ

Written by 
Rate this item
(9 votes)
  •    የ7.3 ቢሊዮን ዩሮ ተጨዋቾች፤ ከ2.09 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወጭ ፤ እስከ 57.4 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት
  • 5 ክለቦች ታጭተዋል ፤ ሪያል ማድሪድ፣ ባየር ሙኒክ፣ ባርሴሎና፣ ቼልሲና ማን. ሲቲ
  • ፕሪሚዬር ሊግ ፤ ከቦንደስ ሊጋና ላሊጋ ይተናነቃል         
  • የ2014-15 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሰሞኑን በአራተኛ ዙር የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ቀጥሏል፡፡ በምድብ ማጣሪያው ቀሪ የሁለት ዙር ጨዋታዎች ቢኖሩም 5 ክለቦች ሪያል ማድሪድ፤ ቦርስያ ዶርቱመንድ፤ ፒኤስጂ፤ ባርሴሎና እና ፖርቶ ወደ ጥሎ ማለፍ መሸጋገራቸውን አረጋግጠዋል፡፡

አትሌቲኮ ማድሪድ፤ አያክስን ጨምሮ አምስት ክለቦች ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ በየውድድር ዘመኑ እስከ 30 ቢሊዮን ይንቀሳቀስበታል፡፡ በተለይ ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በትርፋማነቱ የሚስተካከለው የለም፡፡ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ የቀረበ መረጃ እንደሚያመለክተው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ በየውድድር ዘመኑ ከቅድመ ማጣሪያ አንስቶ እስከ ዋንጫ ጨዋታ እንዲሁም የውስጥ የሊግ ውድድሮችን ጨምሮ 853 ተጨዋቾችን የያዙ 155 ክለቦችን በማሳተፍ ይካሄዳል፡፡ በዝውውር ገበያው የዋጋ ግምታቸው እስከ 7.3 ቢሊዮን ዩሮ የሚተመኑ ተጨዋቾች በየክለቡ ተሰልፈው የሚፋለሙበት መድረክ ነው፡፡ ለዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ በአምስቱ የአውሮፓ ሊጎች የሚወዳደሩት ክለቦች ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸው የተረጋገጠው በተጨዋቾች የዝውውር ገበያው 2.09 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወጭ ማድረጋቸው ነው፡፡ ከተጠቀሰው የዝውውር ገበያ ወጭ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 45 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

25 በመቶውን የስፔን 10 በመቶውን የጀርመን ክለቦች አውጥተዋል፡፡ የጣሊያን እና የፈረንሳይ ሊጎች ዝቅተኛውን የወጭ ድርሻ አስመዝግበዋል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በ2014 /15 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና ዩሮፓ ሊግ ውድድሮች ለሽልማትና ሌሎች ገቢዎች ድርሻ 1.34 ቢሊዮን ዩሮ መቅረቡን አስታውቋል፡፡ ካለፈው የውድድር ዘመን በ30 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ የእግር ኳስ ማህበሩ እንዳመለከተው ሌሎች የገቢ ድርሻዎችን ሳይጨምር 60ኛዋን ዋንጫ ለማንሳት የሚበቃው ክለብ እስከ 57.4 ሚሊዮን ዩሮ የሽልማት ገንዘብ ይከፈለዋል፡፡ በምድብ ማጣርያው ላይ የሚገኙት 32 ክለቦች ደግሞ ቢያንስ 8.6 ሚሊዮን ዩሮ የገቢ ድርሻ አላቸው፡፡ በእያንዳንዱ የምድብ ጨዋታ በሚመዘገብ ውጤት መሰረትም የሽልማት ገንዘብ ይከፈላል፡፡ ለድል 1 ሚሊዮን ዩሮ እና ለአቻ ውጤቶች ደግሞ 500ሺ ዩሮ ይታሰባል፡፡ የምድብ ማጣርያውን አልፈው ጥሎ ማለፍ የሚገቡ 16 ክለቦች 3.5 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ሲኖራቸው፤ የሩብ ፍፃሜ 8 ክለቦች እያንዳንዳቸው 3.9 ሚሊዮን ዩሮ፤ የግማሽ ፍፃሜ አራት ክለቦች እያንዳንዳቸው 4.9 ሚሊዮን ዩሮ ፤ በዋንጫ ጨዋታ ተሰልፎ ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኘው ክለብ 6.5 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ዋንጫውን የሚያሸንፈው ክለብ 10.5 ሚሊዮን ዩሮ ከሽልማት ገንዘብ ብቻ ይከፈላቸዋል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለነበሩ 32 ክለቦች የተከፋፈለውገቢ 904.6 ሚሊዮን ዩሮ ነበር፡፡ 57.4 ሚሊዮን ዩሮ በማግኘት 10ኛውን የሻምፒዮንስ ሊግ ያስመዘገበው ሪያል ማድሪድ መርቷል፡፡ በሩብ ፍፃሜ የተሰናበተው ፓሪስ ሴንትዥርመን በ54.4፤ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቶ የጨረሰው አትሌቲኮ ማድሪድ በ50፤ ዘንድሮ የማይሳተፈው እና አምና በሩብ ፍፃሜ የተሰናበተው ማንችስትር ዩናይትድ በ44.8፤ ለግማሽ ፍፃሜ የደረሱት ባየር ሙኒክ በ44.6 እንዲሁም ቼልሲ በ43.4 ሚሊዮን ዩሮ የገቢ ድርሻ ተከታታይ ደረጃ ነበራቸው፡፡ ፕሪሚዬር ሊግ በጥሎ ማለፍ ከቦንደስ ሊጋና ላሊጋ ጋር ይተናነቃል በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፉ የሚሸጋገሩበት ክለቦች ዘንድሮም ከ5ቱ ታላላቅ ሊጐች መገኘታቸው የማይቀር ይመስላል፡፡

17 ክለቦች በየሊጋቸው ያለፈው የውድድር ዘመን ሻምፒዮን ሆነው የሚሳተፉበት ውድድር ቢሆንም ማለት ነው፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ በገቢው ከፍተኛነት የሚታወቀው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ በተረጋጋአስተዳደርና አትራፊነቱ እንደተምሳሌት የሚቆጠረው የጀርመን ቦንደስ ሊጋ እንዲሁም በተወዳጅነት እና በክዋክብት ስብስቡ የደመቀው የስፔን ላሊጋ ለሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ቋሚ ተፎካካሪ ሊጎች ከሆኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በተለይ ከሻምፒዮንስ ሊጉ የዋንጫ ፉክክር ከራቁ ሶስት የውድድር ዘመናት ያለፋቸው የእንግሊዝ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ግማሽ ፍፃሜ መድረሳቸው እየተጠበቀ ነው፡፡ ቼልሲ፤ ማንችስተር ሲቲ ፤ ሊቨርፑልና አርሰናል እንግ ለዋንጫ እንደሚያበቁ በየአቅጣጫው ሰፊ ትንታኔዎችን ተሰጥተዋል፡፡ ይሁንና ባለፉት ስምንት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ሰባቱ የስፔንና የጀርመን ክለቦች መሆናቸው ከባድ ክፍተት ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ሁለቱም ከስፔን ነበሩ ፡፡ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ደግሞ በግማሽ ፍፃሜ ሁለት የላሊጋው ክለቦች ቋሚ ተሰላፊዎች ሆነው አሳልፈዋል፡፡ በ2011 ባርሴሎና እንዲሁም በ2014 ሪያል ማድሪድ ዋንጫን መውሰዳቸውም የስፔኑ ላሊጋ ከቦንደስ ሊጋው በላቀ ግምት እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል የጀርመኑን ቦንደስ ሊጋ የሚወክለው ባየር ሙኒክ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ለ3 ጊዜ ፍፃሜ መድረሱ እና በ2013 ዋንጫውን መውሰዱና ከፍተኛ ግምት አሰጥቶታል፡፡ ዘንድሮ ፍፃሜው በበርሊን ከተማ መዘጋጀቱ ደግሞ የአሸናፊነት ግምቱን ለጀርመኑ ክለብ ያበዛለታል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የስታትስቲክስ ሰነድ የአምስቱ ታላላቅ ሊጎች በሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ ስላላቸው የውጤት የበላይነት በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡

ከ1993 እስከ 2014 እኤአ በሻምፒዮንስ ሊጉ 27 የዋንጫ ጨዋታዎች ተካሂደው ዋንጫዎቹን 13 ክለቦች ሰብስበዋል፡፡ 7 ጊዜ የስፔን፤ 5 ጊዜ የጣሊያን፤ አራት ጊዜ የእንግሊዝ፤ 3 ጊዜ የጀርመን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የፈረንሳይ፤ የሆላንድ እና የፖርቱጋል ክለቦች ዋንጫዎቹን ወስደዋል፡፡ አራቱን ዋንጫ በመውሰድ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው እኩል ሶስት ጊዜ የሻምፒዮናነት ክብር ያገኙት ደግሞ የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን እና የስፔኑ ባርሴሎና ናቸው፡፡ እኩል ሁለት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ እና የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ሲጠቀሱ፤ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ዋንጫ በማግኘት የተሳካላቸው ክለቦች የፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ማርሴይ፤ የሆላንዱ አያክስ፤ የጣሊያኑ ጁቬንትስ፤ የጀርመኑ ቦርስያ ዶርትመንድ፤ የፖርቱጋሉ ኤፍሲ ፖርቶ፤ የእንግሊዙ ሊቨርፑል፤ የጣሊያኑ ኢንተርሚላንና የእንግሊዙ ቼልሲ ናቸው፡፡ ባለፉት 27 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ዘመናት ስፔን 22 ጊዜ በግማሽ ፍፃሜ በመወከል ትቀድማለች፡፡ 19 ጊዜ እንግሊዝ፤ 13 ጊዜ ጣሊያን፤ 12 ጊዜ ጀርመን እንዲሁም 6 ጊዜ ፈረንሳይ በክለቦቻቸው የግማሽ ፍፃሜ ውክልናን አግኝተዋል፡፡ ስፔን በ4 ክለቦች ለ11 ጊዜያት ለዋንጫ ጨዋታ በመቅረብ አሁንም ግንባር ቀደም ነች፡፡ ጣሊያን በ3 ክለቦች ለ11 ፤ እንግሊዝ በ4 ክለቦች ለ9፤ ጀርመን በሶስት ክለቦች ለ8 እንዲሁም ፈረንሳይ በ2 ክለቦች ለ2 ጊዜያት ለዋንጫ ተጫውተዋል፡፡ በሌላ በኩል ከ1955 እሰከ 2014 እኤአ በተደረጉት 59 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የውድድር ዘመኖች 14 ጊዜ የሻምዮናነት ክብሩን በመውሰድ የስፔን ክለቦች ይመራሉ፡፡

በክለቦቻቸው እያንዳንዳቸው 12 ዋንጫዎች ወሰዱት የእንግሊዝ እና ጣሊያን ናቸው፡፡ ሌሎች የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች 7 በጀርመን ፤ 6 በሆላንድ፤ 4 በፖርቱጋልክለቦች የተወሰዱ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ በክለቦቻቸው የአውሮፓን ክብር ያገኙ አራት አገራት ፈረንሳይ፤ሮማንያ፤ ስኮትላንድ እና ሰርቢያ ናቸው፡ 5ቱ የዋንጫ ተፎካካሪዎች የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ገና በምድብ ማጣርያ 4ኛ ዙር ጨዋታዎች ላይ ቢገኝም ለዋንጫው አሸናፊነት 5 ክለቦች እንደታጩ በተለያዩ ዘገባዎች እየተገለፀ ነው፡፡ ለዋንጫው ከታጩትዋናዎቹ ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና ከስፔን ፤ባየር ሙኒክ ከጀርመን እንዲሁም ቼልሲና ማንችስተር ሲቲ ከእንግሊዝ ናቸው፡፡የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በየዓመቱ በአማካይ እስከ 300 ሚሊዮን ተመልካች በመላው ዓለም የሚያገኝ ነው፡፡ ዘንድሮ ለ60ኛዋ ዋንጫ የሚደረገው ፍልሚያ ከ7 ወራት በኋላ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ውስጥ በሚገኘው ኦሎምፒያ ስታድዮን ይስተናገዳል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን 10ኛውን የሻምፒዮናነት ክብር በመቀዳጀት የተሳካለት የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ በተለያዩ ትንተናዎች፤ ቅድመ ትንበያዎች እና ውርርዶች ዘንድሮም ለሻምፒዮንነት በመጠበቅ የላቀ ግምት ወስዷል፡፡ ስለሆነም ሪያል ማድሪድ ምናልባትም ለ11ኛ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን በማሻሻል አዲስ ታሪክ ሊሰራ እንደሚችል በብዛት ተገምቷል፡፡ ይሁንና ባለፉት 24 ዓመታት በተከታታይ ሁለት የውድድር ዘመናት በማሸነፍ የሻምፒዮንነት ክብሩን ሊያስጠብቅ የቻለ ክለብ ግን የለም፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ የቅርብ ታሪክ ዋንጫዋን በተከታታይ ሁለት የውድድር ዘመናት ለማሸነፍ የበቃ ክለብ በ1990 እኤአ ላይ የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ብቻ ነው፡፡ ከዚያን በኋላ በተካሄዱት 24 የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ዘመናት በሻምፒዮንነት ክብሩ የቀጠለ አልነበረም፡፡ በውድድሩ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በቀደመው ዓመት ዋንጫውን አሸንፈው የሻምፒዮናነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ እስከ ፍፃሜ ደርሰው ያልሆነላቸው 4 ክለቦች ነበሩ፡፡ ኤሲ ሚላን፤ አያክስ፤ ጁቬንትስ እና ማንችስተር ዩናይትድ ናቸው፡፡ በዓለም የእግር ኳስ ስፖርት የሚንቀሳቀሱ እውቅ አቋማሪ ድርጅቶች ለዋንጫው ድል ከፍተኛ ግምት በመስጠት አነስተኛ የውርርድ ገንዘብ ያቀረቡት ለስፔኑ ክለብ ለሪያል ማድሪድ ነው፡፡ ባየር ሙኒክ፤ ባርሴሎና፤ ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ እንደቅደምተከተላቸው በአቋማሪዎች በየደረጃው የውርርድ ሂሳብ ወጥቶላቸው ለሻምፒዮንነት ክብሩ ተጠብቀዋል፡፡

ለናሙና ያህል ቢስፖርትስ የተባለ አቋማሪ ድርጅት ያወጣውን የውርርድ ስሌት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቢስስፖርትስ 32 ክለቦች በሚፎካከሩበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ፉክክር ሪያል ማድሪድ 19.03 በመቶ የአሸናፊነት ግምት እንደሚሰጠው አመልክቶ፤ ባየር ሙኒክ 16.69፤ ባርሴሎና 15.51 ፤ ቼልሲ 11.87 እንዲሁም ሲቲ 6.7 በመቶ የማሸነፍ እድል እንደሚኖራቸው በመጥቀስ የውርርድ ሂሳቡን አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ታዋቂው የእግር ኳስ ዘጋቢ ድረ ገፅ ጎል የአንባቢዎቹን ድምፅ በመሰብሰብ በሰራው የሻምፒዮንነት ትንበያ ላይ ዋንጫው የባርሴሎና ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ እንደጎል ድረገፅ አንባቢዎች ግምት 60ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለማሸነፍ 25.6 በመቶ እድል በመያዝ ባርሴሎና ቀዳሚ ነው፡፡ ቼልሲ በ25.5፤ ሪያል ማድሪድ በ13.2 እንዲሁም ባየር ሙኒክ በ11 በመቶ ድምፅ አግኝተው በተከታታይ ደረጃ ለዋንጫው ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከአሰልጣኞች መካከልም ለዋንጫው አሸናፊነትና ለታሪካዊ ስኬትም የተጠበቁ አሉ፡፡ ጆሴ ሞውሪንሆ ከፖርቶና ከኢንተር ሚላን በኋላ ከቼልሲ ጋር በሶስተኛ ክለብ ጋር ዋንጫ በማንሳት ታሪክ መስራታቸው ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ለሪያል ማድሪዱ አንቸሎቲ እና ለባየር ሙኒኩ ፔፔ ጋርዲዮላ ተመሳሳይ ታሪኮች ይጠበቃሉ፡፡ ክለባቸው አርሰናል ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ሻምፒዮንስ ሊግን ማሸነፍ እንደሚችል በይፋ የተናገሩት ደግሞ አርሴን ቬንገር ናቸው፡፡ ቬንገር 90 በመቶ የዋንጫ ግምቱ ለሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎናና ባየርሙኒክ ቢያጋድልም፣ በሻምፒዮንስ ሊግ ልምድ ያለው አርሰናልም ለመጀመርያ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን ተስፋ የሚኖረው ዘንድሮ ነው ብለዋል ፡፡

ከተጨዋቾች ለዋንጫው ያለውን እድል በተመለከተ ከተናገሩት ዋንኛው ተጠቃሽ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ ነው፡፡ የካታላኑ ክለብ ከ3 የውድድር ዘመናት መራቅ በኋላ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ሊወስድ የሚበቃው በሊውስ ስዋሬዝ ምክንያት እንደሚሆን ሊዮኔል ሜሲ ተናግሯል፡፡ የሮናልዶ የወርቅ ኳስ ሃትሪክ እና ትንቅንቁ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና በታዋቂው የፍራንስ ፉትቦል መፅሄት ትብብር ለሚከናወነው የ2014 የዓለም ኮከብ እግር ኳሰኞች ምርጫ የቀረቡ እጩዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ታውቀዋል፡፡ መላው ዓለም በጉጉት በሚጠባበቀውና ዋናው ሽልማት የሆነው የወርቅ ኳስ ነው፡፡ 23 ተጨዋቾች የመጨረሻ ዕጩዎች ሆነው ቀርበውበታል፡፡ አሸናፊው ከዓለም ዋንጫ ወይንስ ከሻምፒዮንስ ሊግ ይገኛል የሚለው ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡ የኮከብ ተጨዋች ምርጫው በስፖርታዊ ብቃትና ዲሲፕሊን ተለክቶ ይበረከታል፡፡ በድምጽ አሰጣጡ ላይ በታዋቂው ፍራንስ ፉትቦል መጽሔት አማካኝነት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ጋዜጠኞች እንዲሁም በፊፋ ስር ደግሞ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አባል የሆኑ አገራት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አምበሎች ይሳተፋሉ፡፡ ዘንድሮ ለወርቅ ኳስ ሽልማት ተፎካካሪ ከሆኑት 23 እጩዎች መካከል የስፔኑ ላሊጋ 10 ተጨዋቾች በማስመረጥ ይመራል፡፡

የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 6 እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 5 ተጨዋቾች ከእጩዎቹ ተርታ በማካተት ተሳክቶላቸዋል፡፡ ለ2014 ወርቅ ኳስ ሽልማት ዋና ተፎካካሪዎች የሆኑት የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶና እና የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ መሆናቸው በተለምዶ ቢነገርም የዓለም ዋንጫን ያሸነፉት የጀርመን ተጨዋቾች ዋና ተቀናቃዐኞቻቸው ናቸው፡፡ ጀርመናዊያኑ ፊሊፕ ለሃም፣ ቶምስ ሙለር፣ ማኑዌል ኑዌር እና ማርዬ ጐትዜ ፊፋ ለራሱ ውድድሮች በሚሰጠው ግምት ከመጨረሻዎቹ 3 እጩዎች ተርታ የመግባትና የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው እየተገለፀ ነው፡፡ ከጀርመናውያኑ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዎች ከባድ ፉክክር ባሻገር በ2014 የዓለም ኮከብ ተጨዋቾች ምርጫው ከፍተኛ የማሸነፍ ዕድል እንዳለው የሚነገርለት ፖርቱጋላዊው የሪያል ማድሪድ ተጨዋች ክርስትያኖ ሮናልዶ ነው፡፡ ሌላ የቅርብ ተፎካካሪው ሊዮኔል ሜሲ ነው፡፡

ክርስትያኖ ሮናልዶ በ2014 ብዙ ስኬቶች ነበሩት፡፡ በአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች ኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ ለሶስተኛ ጊዜ መሸለሙ ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ከሪያል ማድሪድ ጋር 10ኛውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ድል በማግኘቱ፣ በ17 ጐሎች የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ መጨረሱ፣ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ምርጫ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ መመረጡና ከሁለት ሳምንት በፊት የላሊጋው ኮከብ ሆኖ አራት ልዩ የክብር ሽልማቶችን ማግኘቱ ለወርቅ ኳሱ ሽልማት የሚባቀበትን ሁኔታ አስፍቶለታል፡፡ ሮናልዶ ምንም እንኳን በዓለም ዋንጫ ከአገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር ስኬታማ ባለመሆኑ በምርጫው በፊፋ አባል አገራት ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ድጋፎች ቢያወርድበትም 2014 ከገባ በክለብ ደረጃ በ44 ጨዋታዎች 45 ጐሎች ማስመዝገቡ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች ያደርገዋል፡፡ ብራዚል ባዘጋጀችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ አገሩን አርጀንቲና ለፍፃሜ ያደረሰው እና የዓለም ዋንጫው ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ምናልባትም ከሮናልዶ ጋር ብዙ ተፎካካሪ የሚሆንበት ስኬት የለውም፡፡ ይሁንና ሊዮኔል ሜሲ በሻምፒዮንስ ሊጉ የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ክለቡ ባርሴሎና የሆላንዱን አያክስ 2ለ0 ሲያሸንፍ ሁለቱንም ጎሎች በማግባት በውድድሩ ታሪክ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢነትን በ71 ጎሎች ከቀድሞው ስፔናዊ ራውል ጋር በመጋራት ከሮናልዶ የቀደመ ስኬት ማግኘቱ ትኩረት እየሳበለት መጥቷል፡፡ ራውል 71 ጎሎች ያስመዘገበው በ144 ጨዋታዎች ሲሆን ሜሲ በ90 ጨዋታዎች ክብረወሰኑን ተጋርቶታል፡፡ ሮናልዶ በ107 ጨዋታዎች 70 ጎሎች አስመዝግቧል፡፡

ሊዩኔል ሜሲ የወርቅ ኳስ ሽልማትን ለ4 ጊዜያት ያሸነፈ ሲሆን ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያሸነፈው ደግሞ ሁለቴ ነው፡፡ በ2013 የዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ላይ ኢትዮጵያውያን በነበራቸው ተሳትፎ የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ሮናልዶ፣ ኢንዬስታ እና ኔይማር በማለት ኮከባቸውን በደረጃ አከታትለው ሲመርጡ ፤ የብሔራዊ ቡድን አምበል የነበረው ደጉ ደበበ ዣቪ፤አንድሬ ፒርሎና ቶሞስ ሙለርን ብሎ ነበር፡፡ በጋዜጠኞች ዘርፍ ደግሞ ታዋቂው መንሱር አብዱልቀኒ ፍራንክ ሪበሪ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ እና ሽዋንስታይገር ብሎ ድምፅ ሰጥቶ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሰሞኑን ፎርብስ ለዓለም ስፖርተኞች ለዓመቱ ከፍተኛ ገቢ ባወጣው ደረጃ ሮናልዶ በ64 ሚሊዮን ዩሮ ከእግር ኳስ ተጨዋቾች አንደኛ ከሁሉም ስፖርተኞች ሁለተኛ ደረጃ አለዐው፡፡ የሮናልዶ ገቢ 41.6 ሚሊዮን ዩሮው ከደሞዝ ሲሆን 22.4 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ ከተለያዩ የንግድ ውሊች እና የስፖንሰርሺፕ ክፍያዎች ያገኘው ነው፡፡ ሜሲ በ52፤ ዝላታን ኢብራሞቪች በ32.32፤ ጋሬዝ ቤል በ29.12፤ ፋልካኦ በ28.32 እንዲሁም ኔይማር በ26.88 ሚሊዮን ዩሮ ገቢያቸው ተከታታይ ደረጃ ወስደዋል፡፡ ፡

Read 4946 times