Monday, 03 November 2014 08:14

ሚሊዬነርነትን በሊስትሮ ሳጥን የተቀዳጀ ጀግና

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(3 votes)

የሊስትሮ ቢዝነሱን ወደ አሜሪካና እንግሊዝ ሊያሻግር አስቧል
ለፓርላማ ወጥ ቤት እንቁላል ይሸጥ ነበር
ዓመታዊ ገቢው ከ4 ሚ. ብር በላይ ደርሷል

        ሰሞኑን ያነበብኩት የCNN የስኬት ታሪክ መንፈስ የሚያነቃቃ ነው፡፡ በእርግጥ በቀላሉ የሚታመን አይነት አይደለም፡፡ ከምንም ተነስቶ ጫማ እየጠረገ ከሚሊዬነሮች ተርታ መሰለፍ ስለቻለ ስኬታማ የቢዝነስ ሰው ነው ሲኤንኤን የሚተርከው፡፡ ደስ የሚለው ደግሞ የታሪኩ መቼት አውሮፓ ወይም አሜሪካ አለመሆኑ ነው፡፡ እዚሁ አፍንጫችን ስር ነው የተከሰተው፡፡ በአህጉራችን ደቡብ አፍሪካ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ኤርፖርት ጫማዎትን አስጠርገው የሚያውቁ ከሆነ፤ የጠረገልዎት ሌሬ ማጋዪዩ መሆን አለበት፡፡ እሱ ባይሆን እንኳ እሱ ያቋቋመው ኩባንያ እንደሚሆን አይጠራጠሩ፡፡
“በአፍሪካ ትልቁ የሊስትሮ ኩባንያ ነን” ይላል የድርጅቱ መስራች፤ ዕብሪት ባልተጫነው ቅላጼ፡፡ “በጆሃንስበርግ 350 ገደማ ጥንድ ጫማዎች፤ በኬፕ ታውን 120 ገደማ፤ በደርባን እንዲሁ 120 ጥንድ ጫማዎችን በየቀኑ እናሳምራለን” ይላል ማጋዪዩ፡፡ “ሌሬ የሊስትሮ ኩባንያ” በሦስቱ ትላልቅ የአገሪቱ አየር ማረፊያዎች በአጠቃላይ 45 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን አሁን ባለቤቱ ዓይኑን የአሜሪካና የእንግሊዝ ሸሪኮች በማፈላለግ እንዲሁም በመላው አፍሪካ  ስራውን በማስፋፋት ላይ ጥሏል፡፡
የ40 ዓመቱ ማጋዪያ ለሲኤንኤን ቃለ ምልልስ በሰጠበት ዕለት ክላርክ ጫማ ነበር ያደረገው፡፡ አሁን ዓመታዊ ገቢው 227ሺ ዶላር (ከ4 ሚ. ብር በላይ) የደረሰ ሲሆን ገፅታው እንደጫማው ሁሉ ምቹነት ይንፀባረቅበታል፡፡
ለእዚህ ሰው ነገሮች ሁሌም እንዲህ ምቹ ነበሩ ማለት ግን አይደለም፡፡ መለኛው ደቡብ አፍሪካዊ  ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ ተከታታይ ውድቀቶችን አስተናግዷል፡፡ ብዙ ጊዜ ወድቆ ብዙ ጊዜ ተነስቷል፡፡ ብርታቱም ይሄው ነው - ወድቆ አለመቅረቱ፡፡
ሙያዊ ጅምር
በደቡብ አፍሪካ በሊስትሮ ስራው ከመንገሱ እጅግ ቀደም ብሎ ሙያዊ ሥራውን አሃዱ ብሎ የጀመረው ለደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ የአውሮፕላን መሳፈሪያ ካርዶችን በማከፋፈል ነበር፡፡ በአየር መንገዱ ውስጥ ለ5 ዓመት ከሰራና በሱፐርቫይዘርነት ከተሾመ በኋላ ግን ከሥራ የመቀነስ ክፉ እጣ ወደቀበት፡፡ ያኔ ለመልቀቅ ዝግጁ እንዳልነበር ያስታውሳል፡፡ “እውነቱን ለመናገር ፈርቼ ነበር፤ ግን መቀነሴ አበረታኝ” ብሏል፡፡
ከአየር መንገዱ እንደወጣ በቤተሰቡ የከብቶች ማጓጓዝ ቢዝነስ ላይ ተሰማራ፡፡ “ወጣ እያሉ መስራት ያስደስተኝ ነበር” ያለው የቢዝነስ ሰው፤ “ግቦቼን ማስቀመጥና ማሳካትም ያረካኛል” ይላል፡፡
ሆኖም በቤተሰብ ቢዝነስ ውስጥ ህይወት አልጋ በአልጋ አልሆነለትም፡፡ በራሱ ለመንቀሳቀስ ወሰነ፡፡ እናም ብድር ወስዶ በግሉ ኮንትራቶችን እየተቀበለ የመስራት ሃሳብ ሲያመነጭ አጎቱ “ግፋበት” አሉት፡፡ ብዙም ሊገፋበት ግን አልቻለም፡፡ ከዓመት በኋላ ሥራ ፈትቶ ተቀመጠ፡፡
ያልተሳኩ ሙከራዎች
አሁን ምን ይስራ? የቀድሞ ሥራውን እንደሆነ የእናቱ ወንድም (አጐቱ) ቀምተውታል፡፡ ሳይደግስ አይጣልም እንዲሉ ግን ከገበሬ ደንበኞቹ ጋር ትስስሩን አላቋረጠም ነበር፡፡ በእሱ ተንጠላጥሎ ወደ ቀጣዩ ፕሮጀክት ገባ፡፡ አዲሱ ፕሮጀክቱ ከገበሬዎቹ ላይ እንቁላል እየተረከበ፣ ለደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ወጥ ቤት መሸጥ ነው፡፡ ከአንድ የእንቁላል ትሪ የሚያተርፈው ግን 6 ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ አዋጪ አልነበረም፡፡ “ለገበሬዎቹ በወቅቱ ገንዘባቸውን መክፈል አልቻልኩም” የሚለው ማጋዪያ፤ “የራሴን መኪና ለማንቀሳቀስ ገንዘብ አልነበረኝም፤ የአቅርቦት ሥራ ለመምራት ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስፈልጋል” በማለት ስራውን ያቋረጠበትን ምክንያት አስረድቷል፡፡
ገንዘቡ ተሟጥጦ ባዶ ኪሱን ቢቀርም ተስፋው ግን አልተሟጠጠም፡፡ ይሄኔ ነው በቴሌቪዥን በሚካሄድ Sandlam Money Game በተሰኘ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች ውድድር ላይ የተሳተፈው፡፡ የሬድ ቡል የማርኬቲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፤ እሱ የቀረጸውን የማስታወቂያ ሃሳብ ስለወደዱለት ማጋዪያ ውድድሩን አሸነፈ፡፡ ሽልማቱን 3ሺ100 ዶላር (62ሺ ብር ገደማ) ተቀበለ፡፡ ቀላል ገንዘብ አልነበረም፡፡
የራበው ሰው ማሰብ አይችልም
ይሄን ገንዘብ እንዳለ ያፈሰሰው በወቅቱ ጀምሮት በነበረው በዛፍ ተከላ ላይ ለተሰማራ ኩባንያ ነበር፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ግን ነገሮች ተበላሹ፡፡ ማጋዪያ ዳግም ቤሳ ቤስቲን የሌለው “ቺስታ” ሆነ፡፡ ተመልሶ ዜሮ ገባ፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄ ደቡብ አፍሪካዊ፣ በርካታ የመከራ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ መጪው ጊዜ ግን ቁርጠኝነቱ የሚፈተንበት ነበር፡፡ “ቋሚ ገቢ እፈልግ ነበር፤ እናም በኬፕ ታውን አየር ማረፊያ ጫማ የማሳመር (ሊስትሮነት) ቢዝነስ ለመጀመር ወሰንኩ፡፡ የራበው ሰው ማሰብ አይችልም፤ እኔም በጣም ተርቤ ነበር” ሲል የነበረበትን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡   
አየር መንገድ ውስጥ በሚሰራ ወቅት ያውቃቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጠረና የመስሪያ ቦታ እንዲሰጠው በፈረንጆች አቆጣጠር በህዳር 2002 ዓ.ም አመለከተ፡፡ የአየር መንገዱ ኃላፊዎች ፈቃድ ለመስጠት ዓመት ገደማ ፈጀባቸው፡፡ “ያን ጊዜ መኪናዬን ሸጬ ነበር…ለሦስት ወራት ያህልም በእንግዳ ተቀባይነት ሰርቻለሁ፡፡ ኑሮን ለመቋቋም እየለመንኩም እየተበደርኩም ራሴን አቆይቻለሁ” ብሏል ከሲኤንኤን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፡፡
የቢዝነስ ሥራ ጅማሮ
ስራውን ለመጀመር አንዳንድ  የመስሪያ ቁሳቁሶችን ማሟላት ነበረበት፡፡ ግን ገንዘብ አልነበረውም፤ ስለዚህ ፍሪጁን አሲዞ (ኮላተራል መሆኑ ነው) ጥቂት ገንዘብ ማግኘት ቻለ፡፡ ሁሉ ነገር አልቆ ሥራውን ሀ ብሎ በሚጀምርበት ቀን ግን ያላሰበው ችግር ተከሰተ፡፡ የሊስትሮ ሳጥኖች እንዲሰራለት ያዘዘው ሰው ቃሉን ሳያከብር ቀረ፡፡ ሌላ እንቅፋት ማለት ነው፡፡ ሆኖም በመላ ተወጣው፡፡ “ጫማ ጭኔ ላይ እያደረግሁ እጠርግ ነበር” ብሏል - ሳጥኖቹ እስኪደርሱ፡፡
ቢዝነስ ስትጀምር በራስህ እምነት ሊኖርህ ይገባል  መጀመሪያ ላይ ማጋዪያና ብቸኛ ተቀጣሪ የስራ ባልደረባው ከእሁድ በስተቀር በየቀኑ ከማለዳው 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ነበር የሚሰሩት፡፡ “ጠዋት ቤተሰቤ ከዕንቅልፉ ከመንቃቱ በፊት ከቤት እወጣለሁ፤ ማታ ታናሽ እህቴ ከተኛች በኋላ እቤት እገባለሁ” ያለው ተርቡ  ደቡብ አፍሪካዊ፤ ሥራው ከባድ እንደነበርም አልሸሸገም፡፡
አንድ ደንበኛ የኩባንያው ስም የሥራውን ድባብ የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት ባለው መሰረት “ኤርፖርት የጫማ ማሳመሪያ” የሚለው ስያሜ “የሌሬ ጫማ ማሳመሪያ” በሚል ተተካ፡፡ ሁለተኛ ስሙ በሰዎች ዘንድ ተወደደለት፡፡ የደንበኞቹ ቁጥርም በፍጥነት ተመነደገ፡፡ ከአራት ወራት በኋላ ሦስት ሰራተኞች በመቅጠር ጠቅላላ የቡድኑ አባላትን ቁጥር ወደ አምስት አሳደገው፡፡ የዚያኑ ያህልም ገበያውም እየደራለት መጣ፡፡
ትላልቅ እቅዶች
የኬፕ ታውኑ ስኬት ህልሙን አላበረደውም፡፡ ከዓመት በኋላ የደቡብ አፍሪካ አየር ማረፊያዎች ሃላፊ የሆነች ሴት የማግኘት ዕድል ገጠመውና ያሰበውን አማከራት፡፡ ሃላፊዋ ሃሳቡን ወደደችለት፡፡ ወዲያው የማስፋፋት ስራው ተጀመረ፡፡ ኩባንያው የስኬት ጫፍ ላይ በደረሰበት ወቅት በመላ አገሪቱ በሚገኙ አምስት አየር ማረፊያዎች የተሰማሩ 60 ሠራተኞች (ሊስትሮዎች) ነበሩት፡፡ አሁን ማጋዪያ የአየር ማረፊያዎቹን ቁጥር ቀንሶ በሶስት ትላልቆቹ ላይ ብቻ አተኩሯል - ኬፕ ታውን፣ ደርባንና ጆሃንስበርግ፡፡ ግን ትላልቅ ህልሞችና ዕቅዶች አሉት፡፡ (Dream big የሚለው ሃሳብ ተዋህዶታል)
አሁን ትዳር ለመያዝ አቅም ስላበጀ ሚስት ማግባቱን ይናገራል፡፡ “የራሴ መኖሪያ ቤት አለኝ፤ ሴት ልጄንም በግል ት/ቤት አስተምራለሁ” ብሏል፤ ፊቱ በደስታ እያበራ፡፡ ዛሬ እንደ ቀድሞው ከማለዳው 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ አይሰራም፡፡ “ከ6 ሰዓት ጀምሮ ባለው አንድ ሽፍት ብቻ ነው የምሰራው” አለ እየሳቀ፡፡ ፈተናዎችን የተጋፈጠበት እልሁ ሳይሆን አይቀርም ያሳቀው፡፡ የአሁኑን የሥራ ሰዓት ቤተሰቡ እንደወደደለትም ገልጿል፡፡
“በደቡብ አፍሪካ ቢዝነስ ስትጀምሩ በራሳችሁ ላይ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል”  ይሄ ለወጣት የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች የሚለግሰው ቀዳሚ ምክሩ ነው፡፡ “ሁኔታዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ ፍፁም ምቹ አይሆኑም፡፡ ካልጀመራችሁ የትም አትደርሱም… ስለዚህ የግድ መጀመር አለባችሁ” ሲል አክሎ ይመክራል፡፡
ጀግናው የንግድ ሥራ ፈጣሪ፤ እስካሁን ወደፊት ከመገስገስ በቀር የማቆም ወይም የማፈግፈግ ፍንጭ አላሳየም፡፡ አሁን ደግሞ ከትውልድ አገሩ በመውጣት መላ አፍሪካን ለማዳረስ ሃሳብ አለው፡፡ ለጊዜው ግን የሊስትሮ ቢዝነሱን በአንጐላ፣ በኬንያናና በናይጄሪያ ለማስፋፋት እንዲሁም በእንግሊዝና በአሜሪካ በሽርክና ለመስራት ዓይኑን ጥሏል፡፡
የቢዝነስ ስኬቱ ከበርካታ ውድቀቶች ውስጥ የተወለደ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይሄ የንግድ ሥራ ፈጣሪ፤ ምንም ዓይነት ችግሮችና እንቅፋቶች ስኬትን ሊያደናቅፉ እንደማይገባ በደንብ አሳይቷል፡፡ ጐበዝ፤ ከዚህ ጀግና የቢዝነስ ሰው ብዙ መማር የምንችለው ቁምነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ልባም ሰው ከተገኘ በሊስትሮ ሳጥን የሚሊዮን ብሮች ኩባንያ መመስረት እንደሚቻል አይተናል፡፡ ሰናይ ሰንበት ይሁንላችሁ!!


Read 3574 times