Monday, 03 November 2014 08:01

ዛሬና ነገ በኤግዚቢሽን ማዕከል ጮማ ይቆረጣል፤ ቢራ ይጠጣል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

     ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ (ቢጂአይ) “በጥቅምት አንድ አጥንት” በሚል መሪ ቃል ዛሬና ነገ በኤግዚቢሽን ማዕከል የቢራና የባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል እንደሚካሄድ አስታወቀ፡፡ በፌስቲቫሉ ቢራ ይጠጣል፣ ጥሬ ሥጋ (ጮማ) ይቆረጣል፣ በታዋቂ አርቲስቶች የሙዚቃ ዝግጅት ይደምቃል ተብሏል፡፡
የፌስቲቫሉ ዓላማ ምን እንደሆነ የቢጂአይ ቢራ የአዲስ አበባ ሽያጭ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ አባተ ሲያስረዱ፣ በተለያዩ አገራት የቢራ ፌስቲቫል የተለመደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በጀርመን ሙኒክ ከተማ ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው የቢራ ፌስቲቫል 6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡
የቢራ ፌስቲቫል በአገራችን አዲስ አይደለም ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ ሂልተን ሆቴል የቢራ ፌስቲቫል ያካሂዳል፡፡ ተጠቃሚዎቹ ግን ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ስለሆኑ ተደራሽነቱ ውሱን ነው፡፡ የእኛ ቢራ ተጠቃሚዎች (ደንበኞች) መካከለኛ ገቢ ያላቸው ስለሆኑ ይህን የቢራ ባህል ወደ ህብረተሰቡ በማውረድ ለማስለመድ እንፈልጋለን፡፡ ከአሁን በኋላ በየዓመቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በፌስቲቫሉ ጥሬ ስጋ ለምን ተካተተ? ብለን ጠይቀን፣ ጥሬ ስጋ ባህላዊ ምግባችን ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራም ተወዳጅ መጠጥ ስለሆነ አብረው ቢቀርቡ ጥሩ ነው የሚል ውሳኔ ላይ ደረስን፣ በመዲናዋ ታዋቂና ስም ያላቸው 6 ተመራጭ ሥጋ ቤቶች፡- ጨርጨር፣ አሹ፣ ኬርሻዶ፣ መዝገበ፣ በእምነትና ዋአካን ሥጋ ቤቶች በፌስቲቫሉ በመሳተፍ፣ ጥራት ያለው ሥጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ፡፡ ጥሬ ስጋ ለማይበላ ሰውም ጥብስ አለ ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ 220 ብር ደርሷል ያሉት ኃላፊው፤ ብዙ ደንበኞቻችን መጥተው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲጠቀሙ በማድረግ የስጋ ቤቶቹን ወጪ ስለምንደጉም፣ የአንዱን ኪሎ ስጋ ለወትሮው ከሚሸጡበት ዋጋ 40 በመቶ ቀንሰው በ130 ብር ያቀርባሉ ብለዋል፡፡
ፌስቲቫሉ፣ መግቢያ ቢኖረውም ብዙ ሕዝብ እንዲሳተፍ ስለፈለግን 20 ብር አድርገናል፡፡ በሁለቱን ቀን ዝግጅትም እስከ 20 ሺህ ህዝብ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
በፌስቲቫሉ የሚቀርበው ድራፍት፣ ቢራና ጥሬ ስጋ ብቻ እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ኢሳያስ፤ ታዋቂዎቹ “ዛጎል” ና “ጊዜ” ባንዶችና ታዋቂ ዘፋኞች፡- እነ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ማህሌት ገ/ጊዮርጊስ፣ ግርማ ተፈራ ካሳ፣ ተሾመ ወልዴና ሌሎችም ህዝቡን ያዝናናሉ፡፡ ለልጆች መጫወቻ ስላለ ሰው፣ ልጆቹንና ቤተሰቡን ይዞ በመምጣት፣ እየበላና እየጠጣ፣ በሙዚቃው እየተዝናና በሥራ የደከመ አካልና አዕምሮውን ዘና ያደርጋል በማለት አስረድተዋል፡፡    


Read 1131 times