Monday, 03 November 2014 08:10

7ኛው “የኢትዮጵያን ይግዙ” ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክት ቤት ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚያካሂደው “የኢትዮጵያን ይግዙ” ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ሊካሄድ ነው፡፡ የንግድ ትርኢቱ ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚቆይም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ የሻው ደበበ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በንግድ ትርኢቱ 161 የአገር ውስጥና ከ34 በላይ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም ዋና ፀሐፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ጃፓን፣ ቱርክ፣ ሱዳን፣ ቻይና እና ሌሎች ከአስር አገሮች የተውጣጡ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን ዘንድሮ ተሳታፊ የውጭ ኩባንያዎች ከአምናው የ60 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸው ተገልጿል፡፡
በዘንድሮው ኢትዮ ቻምበር የንግድ ትርዒት በተለይ አዳዲስና ለግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ አጋዥና ጠቃሚ የፈጠራ ውጤቶችን የሰሩ 15 ያህል ወጣቶች ያለ ምንም ክፍያ ምርቶቻቸውን እንደሚያስተዋውቁና የገበያ እድል እንዲያኙ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብለዋል፤ ዋና ፀሐፊው በመግለጫቸው፡፡
ኢትዮጵያዊያን የአገራቸው የምርት ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ እንዲጐበኙና የጐበኚውን ቁጥር ለማብዛትም ሲባል የንግድ ትርዒቱ በነፃ እንዲጐበኝ መደረጉም የዘንድሮውን የኢትዮ ቻምበር የንግድ ትርዒት ለየት ያደርገዋል ተብሏል፡፡ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከዩኒቲ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተውጣጡ ተማሪዎችና ሰራተኞች ትርኢቱን እንዲጐበኙ ፕሮግራም መያዙም ተብራርቷል፡፡ ኤግዚቢሽኑ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በሆኑት በዶክተር ደብረፅዮን ገ/ማሪያም እንደሚከፈት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በንግድ ትርዒቱ ላይ ለተሳተፉ ኩባንያዎች ህዳር 3 በሂልተን ሆቴል የሚካሄድ የአቻ ለአቻ ውይይት የተዘጋጀላቸው ሲሆን ትርኢቱን በጥሩ ሁኔታ ያቀረቡ ኩባንያዎች መርጠው ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል፡፡
ህብረተሰቡ እየተዝናና ትርዒቱን እንዲጐበኝም የፋሽን ትርዒት፣ የሙዚቃ ድግስና ሌሎች አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡

Read 1879 times