Monday, 03 November 2014 08:05

“አንተ ፍየል፣ አጎት የለህም?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ሰውየው እንትናዬውን ‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ ምን ይላታል መሰላችሁ…  
“የኩላሊትና የጉበት ስፔሻሊስት ነኝ፡፡”
“ወይኔ ዕድሌ!  ግን እውነትህን ነው?”
“አዎ፣ በተለይ በኩላሊትና በጉበት ቀደዳ የሚደርስብኝ የለም፡፡”
እሷም የኩላሊትና የጉበት ስፔሻሊስት እንትና እንዳላት ታወራለች፡፡ በቃ… ምን አለፋችሁ… በጓደኞቿና በቤተሰብ አካባቢ ዓቢይ አጄንዳ ሆና ከረመች፡፡ ልክ ነዋ…እንዲህ በሰው ዘንድ የሚነገርላቸው በአሪፎቹ እንትናዬዎች ተጠልፈው… የተረፍነው ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች፣ አይነቶች ነና! ቂ…ቂ…ቂ… የምር ግን…ምን ይገርመኛል መሰላችሁ…እንዳለነው ጋዜጠኞችና አርቲስቶች ብዛት ሆሊዉድና እነ ‘ኒው ዮርክ ታይምስ’ና ‘ዋሺንግተን ፖስት’ እዚህ አለመቋቋማቸው ግርም አይላችሁም! ኒኦ ሊበራሎች እንዲህ ነክሰው ይያዙን! ቂ…ቂ…ቂ…
ታዲያላችሁ… አንድ ቀን አጅሪት ከጓደኞቿ ጋር ቁርጥ ልትበላ ልኳንዳ ስትገባ ማንን ብታይ ጥሩ ነው…የኩላሊትና የጉበት ስፔሻሊስት ወዳጇን! ለካስ ሰውየው ‘ስፔሻላይዝ’ ያደረገው ሉካንዳ ቤት ነው! አሀ… ከበሬው ኩላሊቱንና ጉበቱን ለይቶ ለማውጣትም ልዩ ሙያ ያስፈልጋላ!
እሷዬዋ እኮ ይሄኔ ለቤተሰቦቿ… “ከዘመዶቻችን ወይ የጉበት ካንሰር፣ ወይ የኩላሊት ኢንፌክሽን ያለበት ካለ አትጨነቁ፡፡ ለእኔ ንገሩኝ…” እያለች…ጉራ ነስንሳ ይሆናል!
ይቺን አሪፍ ታሪክ ስሙኝማ…ባልና ሚስቱ የገጠር ሰዎች ናቸው፡፡ እናላችሁ… ባል ቀኑን ሙሉ ከመሬት ጋር ሲታገል ነው የሚውለው፡፡ የሚያግዘው ሌላ ሰው ስለሌለ ሲወጣ ሲወርድ ማታ ቤቱ ሲገባ ‘ጨርቅ’ ሆኖ ነው የሚገባው፡፡ ሚስትም በበኩሏ ቤት ውስጥ ጉድ፣ ጉድ ማለቷ አልቀረም፡፡ ግን የባሏን ያህል አይደክማትም፡፡
እናማ… እራት ተበልቶ ወደ መኝታ ሲኬድ…አለ አይደል… ሁል ጊዜ ‘ነገርዬው’ አይቀርም፡፡ (እንደ ‘ዴዘርት’ በሉት! ቂ…ቂ…ቂ…) ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…የአቅም ጉዳይ! እሱ ለራሱ ድክም ብሎታል… የእሷን ጉልበት እንዴት ይቻለው!
በማግስቱም እንዲሁ ይሆናል…በማግስቱም…በማግስቱም…፡፡ ሁልጊዜም ደግሞ ‘ግፊቱ’ የሚመጣው ከሚስት ነው፡፡ (ድሮ… “ወደህ ነው፣ በቀበሌ ተገደህ!” የሚሏት ነገር ነበረች፡፡) እናላችሁ… ምርር ይለዋል፡፡ ቢላት ቢሠራት ምንም ልትለወጥ አልቻለችም፡፡ በመጨረሻ ሽማግሌዎች ዘንድ ይሄዳሉ፡፡ ሲፈራ ሲቸርም ጉዳዩን (‘ከእነ ብጉሩ’) ይነግራቸዋል፡፡ ሽማግሌዎቹም ለሚስቱ ረጋ እንድትል ይመክሯታል፡፡ ‘ነገርዬው’ ውል ሲልባቸው አንዳቸው ለሌላኛው ምልክት እንዲሰጣጡ ይመክሯቸውና ይስማማሉ፡፡
ታዲያላችሁ… ሚስት ሆዬ ደግሞ በአንድ ሌሊት ደጋግሞ ‘ውል’ እያለባት መከራ ማብላቷን አልተወችውም፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዳንድ እንትናዬዎች…‘ነገርዬውን’ ከደማችሁ የተዋሀደ ታስመስሉታላችሁ የሚባለው እውነት ነው እንዴ! ቢሆን ነው እንጂ!… አሀ… የ‘አፍ መፍቻ’ ቋንቋ አታስመስሉታ!)
ታዲያላችሁ…በመጨረሻ ድክም ሲለው እንደ ሶማሌ ተራ መኪና መቶ ትንንሽ ከመሆኑ በፊት ሳታየው ይጠፋል፡፡ ራቅ ባለ ስፍራ ወደሚገኘው የአጎቱ ቤት ሄዶ እዛው ይቀመጣል፡፡ ድካሙም እየቀለለው ሄደ፡፡
እናላችሁ… ጠዋት ወጥቶ መስኩን፣ ጋራውን ምናምኑን ሲያስተውል አንዲት ሴት ፍየል ወንዱን ፍየል ስታሳድደው ያያል፡፡ በማግስቱም እንዲሁ ታሳድደዋለች፡፡ ለብዙ ቀናት ሴቷ ፍየል ወንዱን እያሳደደች መከራውን ስታበላው ሲያይ ቆይቶ ምን ቢል ጥሩ ነው፣
“አንተ ፍየል፣ አጎት የለህም?”
እናላችሁ… “አንተ ፍየል፣ አጎት የለህም?” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ መቼም ምስኪኖች ላይ የማይበረታ የለም!
ይኸው ኑሮ ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረገን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በቃ እዚህ አገር ነገርዬው ሁሉ ዋጋው ሽቅብ ሲወጣ ጭጭ፣ ጭጭ ነው!
“ስድስትና ስምንት ብር ትሸጥ የነበረችው ቲማቲም በአቅሟ ሃያ ምናምን ብር ገባች…” — ጭጭ!
“መዳፍ ላይ ቁጭ ብላ እንኳን በደንብ የማትታይ ኪኒን ቢጤ ፉርኖ ብር ከሠላሳ…”— ጭጭ!    
“ሁለት ብር ከምናምን ትሸጥ የነበረች እንቁላል ሦስት ብር ከሠላሳ…”— ጭጭ!
እኔ የምለው…“ልክ አይደለም፡፡ ይሄ ግብይት ሳይሆን ቅልጥ ያለ ዘረፋ ነው!” የሚሉ የኤፍኤም ፕሮግራሞች እንኳን እንጣ! ቢያንስ፣ ቢያንስ የሆኑ ነገሮች ዋጋ ሲጨምሩ ማሳመኛ ምክንያት ቢነገረን እኮ አንድ ነገር ነበር!
እናላችሁ… ኑሮ ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረገን ነው፡፡
የ‘ብር’ እና የ‘ወንበር’ ነገር ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረገን ነው፡፡
ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም… ሚጢጢ ስልጣን ቢጤ ሲሰጠን ደረትና ትከሻችን የሚሰፋው የምንወጋው መርፌ ነገር አለ እንዴ! “ሰላምተኛ፣ የዋህ፣ ቤተክርስትያን ሳሚ…” ምናምን እንባል የነበረን ሰዎች በአንድ ጊዜ ከሰው አልፈን፣ የምንረግጠውን መሬት እንኳን ከፍ ዝቅ አድርገን መገላመጥ እንጀምራለን፡፡ በትንሽ በትልቁ ስልጣናችንን ለማሳየት ሰዉን መከራ እናበላለን፡፡
ስሙኝማ… ከ‘ፍሬሽ’ ባለወንበር፣ ከ‘ፍሬሽ’ አፍቃሪ፣ ከ‘ፍሬሽ’ ‘ታዋቂ አርቲስት’፣ ከ‘ፍሬሽ’ ገጣሚ፣ ምናምን … ይሰውራችሁማ!
እናላችሁ…ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል (‘መሸወጃ አነጋገር’ ልትሏት ትችላላችሁ…) ባለ ወንበሮች ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረጉን ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ ብላኝ ነው፡፡ ያው ነጋ ጠባ…
“ስልጣኔያችን እየናረ ነው…”
“ኒው ዮርክ በቅናት ዓይኗ ቀልቷል…”
“ፓሪስ እኛን አይታ ተንገብግባለች…” ምናምን አይነት ቃና ያላቸው አባባሎች እየለመዱብን ነው፡፡ የምር ግን የባቡር ሃዲድ አሪፍ ነው፣ ግን… ‘የስልጣኔ ከፍተኛ መለኪያ’ ሲያስመስሉት አሪፍ አይደለም፡፡ አሀ…ባቡር ጦቢያችን ከገባ መቶ ምናምን ዓመት ገደማ ሆኖታላ!
ደግሞ…ባለብሮች ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረጉን ነው፡፡
የብር ነገርማ ተዉት…መጀመሪያ ነገር ብሩ ሁሉ ‘‘ከየት እንደሚመጣ ግራ እየገባን ይኸው…አለ አይደል… እየተቁለጨለጭን አለን፡፡ እንደ ሰዋችን መዝናናት፣ እንደሚመዠረጠው ብርና ዶላር፣ እንደሚፈሰው ጎልድ ሌብል ምናምን… ግራ ቢገባን አይፈረድብንም፡፡
ታዲያላችሁ…ዋናው ነገር ባለብሮች (“አንዳንዶቹ…” “በርከት ያሉት…” ምናምን ማለት ይቻላል፡፡) እንዴት እንደሚሆኑ ስታዩ ታዝናላችሁ፡፡ ብር ስላለ ብቻ እኛንም ልክ እንደ ‘ግል ንብረታቸው’ የሚቆጥሩን ነው የሚመስለው፡፡
እናላችሁ…አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች በሉት፣ መዝናኛ ስፍራዎች በሉት፣ በየአውራ ጎዳናው በሉት..አለ አይደል…ቅድሚያ እንድንሰጥ ይጠበቅብናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እነዚሀ የማታ ሰፈሮች አካባቢ… ‘ብር ተቆልሎ’ ነገር ሥራቸውን ያሳጣቸው ሰዎች ዶላሩን፣ ፓውንዱን፣ ዩሮውን እየመዘዙና እየከተቱ የሚያሳዩትን ባህሪ ስትሰሙ በጣም ታዝናላችሁ፡፡
አንዳንድ ጊዜ እኮ… “ጥጋብም፣ ረሀብም አይችሉም... የምንባለው ነገር…አለ አይደል ዝም ብሎ የተፈጠረ አይደለም ትላላችሁ፡፡
እናማ…ባለብሮች ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረጉን ነው፡፡
ማንቼና አርሴ… ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረጉን ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ብቻ…አለ አይደል…ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ‘አጎት የሌለው ፍየል…’ እያደረጉን ስለሆነ የተሻለውን ነገር ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!!    


Read 4484 times