Monday, 03 November 2014 07:46

የአንድነት ፓርቲ ውዝግብ ምርጫ ቦርድ ደርሷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ቦርዱ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል
ቅሬታ አቅራቢዎቹን የፓርቲው መዋቅር አያውቃቸውም ተብሏል

           የኢ/ር ግዛቸው ሽፈራውን ከስልጣን መልቀቅና ጠቅላላ ጉባኤው ሳይወስን አዲስ ፕሬዚዳንት መመረጡን የተቃወሙ የአንድነት ፓርቲ የተለያዩ ዞኖች አመራሮች የተቃውሞ ደብዳቤያቸውን ለምርጫ ቦርድ ያስገቡ ሲሆን ቦርዱ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል፡፡ የፓርቲው አመራሮች በበኩላቸው፤ የተሰራ ስህተት የለም ሲሉ ከትናንት በስቲያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የኢ/ር ግዛቸው ከስልጣን መልቀቅ ተገቢ አይደለም፣ በግፊትና በጫና ነው የለቀቁት ሲሉ ሰሞኑን በራስ ሆቴል መግለጫ የሰጡት ከአፋር፣ ከባሌ፣ ከአሩሲና ሌሎች አካባቢዎች የፓርቲው ተጠሪዎች ነን ያሉ ግለሰቦች ሲሆኑ የፓርቲው አመራሮች በበኩላቸው፤ ግለሰቦቹን የአንድነት መዋቅር አያውቃቸውም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ መጀመሪያውኑ ካቢኔያቸውን አፍርሰው ወደ ብሔራዊ ምክር ቤቱ መምጣታቸውን ያስታወሱት አመራሮቹ፤ ፓርቲው ያለ አመራር አንድም ቀን ማደር ስለሌለበት ብሄራዊ ምክር ቤቱ ባለው ስልጣን፣ የፓርቲውን ደንብ መሰረት በማድረግ ምርጫውን አከናውኗል ብለዋል፡፡
ከቀድሞው ፕሬዚዳንት የካቢኔ አባላት አንዱ የነበሩት የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን ስለጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢ/ር ግዛቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ይፋ ከማድረጋቸው አንድ ቀን በፊት ሁሉንም የካቢኔ አባላት ሰብስበው ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን በመግለጽ፣  የካቢኔ አባላቱንም መበተናቸውን በይፋ ተናግረዋል ብለዋል፡፡
በወቅቱ አመራሩን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይያዙ ተብሎ እንደነበረ የጠቆሙት አቶ ዘካሪያስ፤ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ መቀጠል አልችልም በማለታቸውና ደንቡም ስለማይፈቅድ በቀጥታ ካቢኔውን ማፍረስ አማራጭ የሌለው ሆኗል ብለዋል።
“የጠቅላላ ጉባኤው ውክልና ብሄራዊ ምክር ቤቱ አለው” ያሉት አዲሱ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ፤ “ኢ/ር ግዛቸው ካቢኔውን በትነው መልቀቃቸውን በማሳወቃቸው፣ ፓርቲውን አመራር አልባ ላለማድረግ በአስቸኳይ አመራሩ ተመርጦ ካቢኔው ሊዋቀር ችሏል ብለዋል፡፡
 የህግ ጥሰት ተፈፅሟል ያሉት ሰዎች የፓርቲው ተጠሪዎች ነን ቢሉም ከሁለቱ በስተቀር የፓርቲው የአመራር መዋቅር አያውቃቸውም  ተብሏል፡፡ በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በሰጡት ምላሽ፤ ከሁለቱም ወገኖች በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቦርዱ ነገሩን በትኩረት እየመረመረ ነው ብለዋል፡፡  በሌላ በኩል፤“በፖለቲከኛ እስረኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” በሚል አንድነት በሰጠው መግለጫ፤ በእስር ላይ በሚገኙት የፓርቲው አመራሮች፣አቶ ሃብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመ ነው ብሏል፡፡
አቶ ሃብታሙ ለእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች እየደረሰበት ያለውን በደል አቤት ቢልም ቀና ምላሽ አልተሰጠውም ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ አቶ ዳንኤል ሺበሺም የታፈነ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ በመደረጉ በተደጋጋሚ ለተቅማጥና ለተለያዩ በሽታዎች መዳረጉንና ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳይሄድ መከልከሉን  ለፍ/ቤት ቢያመለክትም ምንም ምላሽ አልተሰጠውም ብለዋል፡፡

Read 1826 times