ከሁለት ሳምንት በኋላ በጀርመን በሚከናወነው የበርሊን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ሜሪል ስትሪፕ የህይወት ዘመን የክብር ተሸላሚ በመሆን “ጎልደን ቢር” የተባለውን ሽልማት እንደምትቀበልም ይጠበቃል፡፡በቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር ጠንካራ ሰብእና፣ የፖለቲካ አቋምና ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች መማረኳን የገለፀችው ስትሪፕ፤ ገፀባህርያዋን በቅጡ ለማወቅና ለመተዋወቅ የተለያዩ ጥናታዊ ዘገባዎችና የቪድዮ ፊልሞችን ለወራት እንደተመለከተች ተናግራለች፡፡ ማርጋሬት ታቸር ለ11 ዓመት ያህል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል፡፡ 10 ሚሊዮን ዶላር በጀት በወጣበት በዚህ ፊልም ላይ የተወነችው ሜሪል ስትሪፕ ኦስካር ልትሸለም እንደምትችል የተገመተ ሲሆን ግምቱ እውን ከሆነ ለስትሪፕ ሦስተኛ የኦስካር ሽልማት ይሆንላታል፡፡በኦስካር የሽልማት ታሪክ የዘንድሮውን ሳይጨምር ለ16 ጊዜያት በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ በዕጩነት በመቅረብ ክብረ ወሰን ያላት ሜሪል ስትሪፕ፤ በሁለት ፊልሞች የኦስካር ሽልማት የወሰደች ሲሆን ለ26 ጊዜያት በጎልደን ግሎብ ሽልማት እጩ ሆና ቀርባ ሰባት ጊዜ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ከ44 በላይ ፊልሞች ላይ የተወነችው ስትሪፕ፤ በጠቅላላው 2.7 ቢሊዮን ዶላር ማስገባቷንና በአንድ ፊልም በአማካይ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታስገኝ ቦክስ ኦፊስ ሞጆ ጠቁሟል፡፡