Saturday, 25 October 2014 10:56

በሜዳ ቴኒስ የወዳጅነት ውድድር ተዘጋጀ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

አፍሪካ ፕሮፌሽናሎች ለምን የሏትም?
በአዲስ አበባና ከናይጄርያ በመጣው ኢኮዬ የተባለ የሜዳ ቴኒስ ክለቦች መካከል ለሶስት ቀናት የሚቆይ የወዳጅነት ውድድር  በድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ተዘጋጅቷል ፡፡ በወዳጅነት ውድድሩ ከ50 በላይ አንጋፋ የሜዳ ቴኒስ  ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው፡፡ በግብዣ ከናይጄርያ ድረስ ከመጣው ኢኮዬ የሜዳ ቴኒስ ክለብ ፤ ከአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ፤ ከፓይለቶች ማህበር እና ከድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ተውጣጥተዋል፡፡ በሜዳ ቴኒስ የወዳጅነት ውድድሩ ባለፈው ሃሙስ ብስራተ ገብሬል በሚገኘው ኢንተርናሽናል ቴኒስ ክለብ ሜዳዎች ተጀምሯል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው ውድድር ዛሬ ይፈፀማል፡፡
ሀሙስ በተደረገው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ የተገኘችው ታዋቂዋ ድምፃዊት፤ በጎ አድራጊ እና ስፖርተኛ ቻቺ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ በስፖርት ልታድግ የምትችል  አገር መሆኗን ተናግራለች ከወዳጅነት ውድድሩ ከፍተኛ ልምድ ስለሚገኝበትና አገር ስለተዋወቅበት አዘጋጅተነዋል ብላለች፡፡ በበጎ አድራጎት ተግባራቷ በጣም የምትደነቀው አርቲስት ቻቺ ታደሰ ህፃናት በራስ መተማመናቸው እንዲያድግ፤ ሃላፊነት ተሰምቷቸው እንዲያድጉ እና ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ ስፖርት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እምነቷ ነው፡፡ በቻቺ አርት ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል የሚመራው ድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ባለፈው ሐሙስ ውድድሩ አስጀምሮታል፡፡ የሜዳ ቴኒስ የወዳጅነት ውድድሩ የተዘጋጀው የስፖርቱን እድገት ለማነቃቃት፤ የቱሪዝም  ስራዎችን ጎን ለጎን ለማከናወንና የመዝናኛ መድረክ ለመፍጠር እንደሆነም አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን የእውቅና ሰርተፊኬት ያለው ድሪም ቢግ ስፖርት በአካዳሚ ደረጃ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በመስራት ፈርቀዳጅ ነው፡፡ የአካዳሚው ዲያሬክተር እና የሜዳ ቴኒስ አሰልጣኝ አቶ ሰለሞን ደመቀ እድሜያቸው 4 ዓመት እና ከዚያም በላይ ለሚሆናቸው ታዳጊዎች ብቁ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ስልጠና እየሰጠ ነው ይላሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ውስጥ የሚገቡ ታዳጊ የሜዳ ቴኒስ አትሌቶችን ለማፍራት ራእይ መኖሩንም ገልጿል፡፡ የድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ዲያሬክተር  አቶ ሰለሞን ደመቀ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በ15 ዓመቱ በብሄራዊ ቡድን አባል ለመሆን የበቃ ነው፡፡ በአሜሪካዋ ግዛት ሚሲሲፒ በሚገኘው ስቴት ዩኒቨርስቲ  በስኮላርሺፕ እድል ተምሮ በማርኬቲንግ ቢኤ ዲግሪ ሰርቷል፡፡ ከኮሌጅ ትምህርቱ ጎን ለጎን በሜዳ ቴኒስ ተጨዋችነት እና አሰልጣኝነት አሜሪካ ውስጥ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ በተለይ  በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በታዋቂ የአሜሪካ አካዳሚዎች ኮርሶችን ለመከታተል ከመብቃቱም በላይ የአሰልጣኝነት ትምህርቱን በተግባር ከፍተኛ ልምድ አካብቶበታል፡፡  በዚሁ ዓለም አቀፍ ልምድ መነሻነትም ከቻቺ ታደሰ ጋር አካዳሚውን በአገር ውስጥ ለመክፈት መቻሉን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡
የናይጄርያውን ኤኮዮ ሜዳ ቴኒስ ክለብ ወክለው ድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ባዘጋጀው የወዳጅነት ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጡት በውድድሩ ደስተኛ ናቸው፡፡ በኢንተርናሽናል ቴኒስ ክለብ ሜዳ ያገኘናቸው እነዚህ ናይጄርያውያን ስፖርቱ በአፍሪካ ደረጃ ፐሮፌሽናል ተጨዋቾች አለማፍራቱ ያስቆጨናል ብለዋል፡፡ በናይጄርያ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ሰፊ ተሳትፎ እንዳለው የገለፁት ናይጄርያውያኑ፤ እስከ 25 ሺ ዶላር የሚያሸልሙ አገር አቀፍ ውድድሮች ቢኖሩም  በአመዛኙ ግን እንደጤና ስፖርት የሚዘወተር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ቴኒስ ክለብ ሜዳ በሸክላ አፈር መሰራቱ እንደተመቻቸው የገለፁት ናይጄርያውያን፤ በተለይ ለጤና ስፖርተኞች ይህ አይነቱ ሜዳ የአካል ብቃትን ለማጠናከር ይጠቅማል ብለዋል፡፡ አፍሪካ በዓለም የሜዳ ቴኒስ ስፖርት የውድድር መድረኮች መሳተፍ የማትችለው ስፖርቱ ለልምምድ እና ለአጠቃላይ ዝግጅት በርካታ ወጪ ስለሚጠይቅ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ታዳጊዎችን አሰልጥኖ  እና በክለቦች አቅፎ በየደረጃው ውድድሮችን በማድረግ በትጋት ከተሰራ ግን ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል  ብለዋል፡፡ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚደርሱ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች በዓለም የውጤት ደረጃ ከገቡ በዓመት ከ5 እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚኖራቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውጥ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ከ50 ዓመታት በላይ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቢቆይም አገሪቱ በስፖርቱ ከክፍለ አህጉራዊ ዞን እንኳን መውጣት አልቻለችም፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ በበርካታ ስፍራዎች ለሜዳ ቴኒስ ስፖርተኞች በአባልነት ክፍያ የሚንቀሳቀሱ  የማዘውተርያ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ከጤና ስፖርተኞች ባለፈ ግን ስፖርቱ ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ ማደግ ተስኖታል፡፡ ዋናው ምክንያትም የናይጄርያ ስፖርተኞች እንደገለፁት ለዝግጅት፤ ለስልጠና እና ለጉዞ የሚያስፈልገው በጀት ከፍተኛነት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ሁለት ተወዳዳሪዎች በኢትዮጵያ ቴኒስ ፌደሬሽን የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ በቦትስዋና በተካሄደው የአፍሪካ የቴኒስ ሻምፒዮና ተሳትፈዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ስፖርተኞች በላቀ ደረጃ ከታዳጊነታቸው ስልጠናውን በማግኘት የተዘጋጁ ባለመሆናቸው የረባ ውጤት አላስመዘገቡም፡፡
ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ለማግኘት አገር አቀፍ ውድድሮች ያስፍጋሉ አለማካሄዳቸውም የስፖርቱን እድገት ያጓተተ ምክንያት ሆኖም ይጠቀሳል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች በአገሪቱ ከ16 በላይ የሜዳ ቴኒስ ክለቦች እንደሚንቀሳቀሱ ያመለክታሉ 10 በአዲስ አበባ፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ክለቦች በኦሮምያ እና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በሃረሪ እና በድሬዳዋ ሌሎች ሁለት የሜዳ ቴኒስ ክለቦች ሲገኙ በፌደሬሽኑ አባል ሆነው እየሰሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ አንዳንድ የቴኒስ ስፖርት አፍቃሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርቱ ማሰልጠኛ አካዳሚ መገንባት ለውጥ ያመጣል ብለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል በአይነቱ ፈር ቀዳጅ የሆነው ድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ በዚሁ አቅጣጫ ከፍተኛ ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አባል የሆነው የአፍሪካ ቴኒስ ኮንፌደሬሽን 50 አገራትን በአባልነት በማቀፍ በቱኒዚያ ተቀማጭ ሆኖ ይሰራል፡፡ ባለንበት ጊዜ በብሩንዲ እና በሴኔጋል አበረታች የሜዳ ቴኒስ ስፖርት እንቅስቃሴዎች ሰሉ፡፡ ፕሮፌሽናል ሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾችን በማፍራት ከአፍሪካ ብቸኛዋ ተጠቃሽ አገር ግን ደቡብ አፍሪካ ናት፡፡ በዓለም የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ደረጃ ለመግባት የቻሉት ሁለት የደቡብ አፍሪካ ስፖርተኞች ናቸው፡፡ ኬቨን አንደርሰን 35ኛ እንዲሁም ቻኔሌ ቺፕርስ 92ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡  ዓለም አቀፉ የሜዳ ቴኒስ ማህበር በአፍሪካ ሶስት የእድገት እንቅስቃሴ ኦፊሰሮች በመመደብ ለረጅም አመታት ቢሰራም ውጤት አላገኘበትም ፡፡ስለዚህም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሚሆኑ ፕሮፌሽናል የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ማፍራት ተስኖታል፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገራት ለሜዳ ቴኒስ ስፖርት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊነት ከመንቀሳቀስ ይልቅ በትራክ የአትሌቲክስ ውድደሮች ላይ ያተኩራሉ፡፡
 የሜዳ ቴኒስ ስፖርት በመወዳዳርያ ቁሳቁሶቹ ውድነት፤ በዝግጅት ከፍተኛ ወጪው እና በሚያስፈልገው የላቀ የአኗኗር ደረጃ ለብዙ አፍሪካውያን እንደቅንጦት የሚታይ ወይንም ለጤና ብቻ የሚደረግ ስፖርት አድርጎታል፡፡ በዓመት ለስልጠና እና ለዝግጅት እንዲሁም ለጉዞዎች ለአንድ ስፖርተኛ እስከ 80ሺ ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡

Read 3023 times