Saturday, 25 October 2014 10:35

የቴሌቪዥን ድራማ ለማቅረብ ሁለት ድርጅቶች አሸነፉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

         ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የቴሌቪዥን ድራማ ለሚያቀርቡ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ባወጣው ጨረታ ከተሳተፉ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ ሮሆቦት ፕሮዳክሽን እና ሉላ ፊልም ፕሮዳክሽን ማሸነፋቸው ታወቀ፡፡ ሮሆቦት ፕሮዳክሽን 84 ነጥብ፣ ሉላ ፊልም ፕሮዳክሽን ደግሞ 80 ነጥብ በማምጣት ማሸነፋቸውን የድርጅቶቹ ስራ አስኪያጆች አቶ ሃይሉ ከበደና አርቲስት ብስራት ገመቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተካሄደ ጨረታ ድርጅታቸው ተወዳድሮ ካለፉት አራት ድርጅቶች አንዱ ሆኖ ጥሪ እንደተደረገላቸው ያስታወሱት የሮሆቦት ፕሮዳክሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይሉ፤ ማጣሪያውን አልፋችኋል፤ ማስተካከል ያለባችሁን ታስተካክላላችሁ ከተባሉ በኋላ “ሂደቱ ሙስና አለበት ብለን ስላመንን ለጊዜው ታግዷል” መባላቸውን ይናገራሉ፡፡ “ጉዳዩ ይጣራ ተብሎ በመጣራት ላይ እያለ ከሳምንት በኋላ ሙሉ በሙሉ ታግዷል የሚል ነገር መጣ” ያሉት አቶ ኃይሉ፤ በጉዳዩ በጣም አዝነው ትተውት እንደነበር ጠቁመው በድጋሚ ጨረታ ሲወጣ መጫረታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ድርጅታችን ትልልቅ ዓለም አቀፍ ስራዎችን የሚሰራ ነው” ያሉት አቶ ኃይሉ፤ በአንድ ጊዜ አራትና አምስት ፕሮዳክሽኖች መስራት የሚችል የሰው ኃይል እንዳላቸውም አብራርተዋል፡፡ “ከድርጅታችን ጋር የድራማውን ስክሪፕት ይዞ የቀረበውና 50 በመቶ ድርሻ ያለው ደራሲ አዶኒስ ነው” ብለዋል፤ የሮሆቦት ስራ አስኪያጅ፡፡ “ትልቅ አቅምና ብቃት ያለውን ደራሲ በመያዛችን እንዲሁም የድርጅታችን አደረጃጀትና ብቃት ተዳምሮ አንደኛ ልንወጣ ችለናል” በማለት አክለዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ስራ ለመግባትና ድራማውን ለመጀመር የቀራቸው ወይም አሟሉ የተባሉት ነገር እንዳለ የጠየቅናቸው ሥራ አስኪያጁ፤ ቀሪውን ሂደት “አንድ አገር ለመሄድ ቪዛ አግኝቶ ትኬት ለመቁረጥ እንደመዘጋጀት ነው” ሲሉ ገልፀውታል፡፡ “የካውንስሉ አባላት የሰጡን አስተያየት አለ፤ አስተያየቱ ፕሮፌሽናል በመሆኑ ተቀብለነዋል” ያሉት አቶ ሃይሉ፤ የድራማውን አንድ ክፍል ለናሙና ቀርፃችሁ አምጡ በመባላቸው እሱን በመጨረስ ላይ መሆናቸውንና ይህም የድርጅቱን አቅም፣ የተዋንያንን ብቃትና የድራማውን ይዘት ለመለካት የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ሃይሉ ከድርጅቱ ስራ አስኪያጅነት በተጨማሪ በድራማው ላይ ከአሸብር ካብታሙ ጋር በአዘጋጅነት እንደሚሳተፉም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቴሌቪዥን ድራማው ሁለተኛ አሸናፊ የሉላ ፊልም ፕሮዳክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ብስራት ገመቹ፤ በቅርቡ በተጠናቀቀው “ሰው ለሰው” ድራማ ላይ በፕሮዱዩሰርነትና በተዋናይነት ትሰራ የነበረ ሲሆን “መልህቅ” የተሰኘ የራሷ ፊልም መስራቷም ይታወቃል፡፡ አርቲስቷ በኢቢሲ በወጣው ጨረታ በግምት ወደ 28 ከሚጠጉ ድርጅቶች ጋር ተወዳድራ 80 ነጥብ በማምጣት ነው ሁለተኛ የወጣችው፡፡ “ይሄ ማለት አለቀ ማለት አይደለም፤ እንድናሟላና እንድናስተካክል የተነገሩን ነገሮች አሉ” ብላለች፡፡

Read 2703 times