Print this page
Saturday, 25 October 2014 10:26

ላቪሲን ኢንተርናሽናል ኤክስፖ የገናን ባዛርና ኤግዚቢሽን ያዘጋጃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ላቪሲን ኢንተርናሽናል ኤክስፖ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የገናን ባዛርና ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት ጨረታውን በ6.1 ሚሊዮን ብር ማሸነፉን የድርጅቱ የሁነቶች ማናጀር አቶ አዶኒስ ወርቁ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ላቪሲን ኢንተርናሽናል ኤክስፖ የቫካይና አጠቃላይ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር አጋር ኩባንያ ሲሆን ላለፉት 16 ዓመታት በፈረንሳይና በሌሎች የአውሮፓ አገራት በሚካሄዱ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍና በጋራ በማዘጋጀት፣ የኢትዮጵያን ባህል፣ ቱሪዝምና የንግድ እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የቆየ ተቋም መሆኑን አቶ አዶኒስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚዘጋጀው የገና በዓል ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ ከ400 በላይ የውጭና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ የገለፁት አቶ አዶኒስ፤ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
ጎብኚው ከመግቢያ ትኬት የተለያዩ ሽልማቶች የሚያገኝ ሲሆን በዝግጅቱ መዝጊያ ቀን ለእድለኞች የመኪና ሽልማት መዘጋጀቱም ተጠቁሟል፡፡
በእለቱ ለቀይ መስቀል ደም ለመለገስ ለሚፈልጉ በጎፈቃደኞች እና ለአባይ ግድብ ቦንድ ለመግዛትም ሆነ ግድቡን ለመጎብኘት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች እድል ለመስጠት ለአባይ ግድብ አስተባባሪዎችና ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቦታ በነፃ ለመስጠት ድርጅቱ ቃል መግባቱን የገለፁት አቶ አዶኒስ፤ የመፅሃፍ ማንበብ ልምድ ለማዳበርም የመፃህፍት መሸጫ ቦታ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡ ከዝግጅቱ ፍፃሜ በኋላ የንግዱ ማህበረሰብ የአባይ ግድብን የሚጎበኝበትና በስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት የሚካሄድበት መድረኮች የተመቻቹ ሲሆን የገና በዓል አንድም ዛፍ ሳይቆረጥ በአርቴፊሻል ዛፍ የሚከበርበት ሁኔታም እንዲሁ የፕሮግራሙ አካል መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ኤግዚቢሽኑ ታህሳስ 10 ቀን ተከፍቶ እስከ ታህሳስ 28 ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡

Read 1413 times