Saturday, 25 October 2014 10:21

የጉራጌ አገር የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

ዘሙቴ ማርያም

የማስታወሻ - ንዑስ - ማስታወሻ
ይህን የጉዞ ማስታወሻ በማዘጋጀት ላይ ሳለሁ በዘሙቴ ማርያም ጉዞዬ ቃለ-ምልልስ ካደረግሁላቸው በሳል ሰዎች መካከል አቶ ጃቢር ቱፈር በድንገት ህይወታቸው አልፎ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በለኩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መቀበራቸውን ሰምቼ በጣም አዘንኩ፡፡እግዚአብሔር ነብሳቸውን ይማር፡፡ ለቤተሰባቸውም መፅናናትን ይስጣቸው!

 “ቀና ሰዎች የጊዜም የቦታም         መለኪያ ናቸው!”
 “የጉራጌ ሀብቱ ምርቃቱ!!”
እንግዲህ አብሬ ዘሙቴ የምገባው “ከዘሙቴ ማርያም ወዳጅነት ማህበር” አባላት ጋር ነው፡፡ ሊቀመንበር፣ ፀሐፊ፣ ገንዘብ ያዥ የሌለውና ሁሉም ነገር አብሮ ተባብሮ በማሰብና በመመካከር፤ የሚኖር ማህበር ነው፡፡ መደበኛ (Formal) የሆነ መዋቅር የለውም፡፡ ይሄንን ማሰብ ደስ ይላል፡፡ አጥር እንደማፍረስ፣ ገደብ እንደመጣስ ያለ ስሜት አለው፡፡ ሁሉም አንተ ትብስ፣ አንተ ትብስ የሚባባልበት ማህበር፡፡ ሁሉም እኩል፡፡ የተለያየ የሙያና የኑሮ መስክ ውስጥ ካለ ሰው ጋር መቀላቀል ደስ ይለኛል፡፡ ፋርሚሲስት፣ ነጋዴ፣ ሐኪም ወዘተ
“ዘሙቴ መሄድ ላንተ ምን ትርጉም አለው?” ስለው ዋንኛው ወዳጄ እንዲህ አለኝ፡-
“ለሰው የተወለደበት ቦታ ትርጉም አለው፡፡ ዛሬ አባቴ የለም - ምንም አይጠቅመውም የእኔ ሀብት፡፡ እዚህ ጋ ግን አንድ እንሠት ብተክልለት. ለእኔ፣ ለህሊናዬ ይጠቅመኛል፡፡ አባቴ ያስቀመጠልኝን እየመነዘርኩ ስበላ ኖሬያለሁ፡፡ መሠረቴ ስለሆነ ነው፡፡ እዚህ ጋ አይኔ፣ እጄ፣ እግሬ፣ መኖሩን፣ ነብስ እንዳለኝ የማውቀው፤ እዚህ መጥቼ ስደሰት ነው - ከእትብቴ ጋር እንደተገናኘሁ ነው የምቆጥረው፡፡ አባቴ አንድ እንድሠራለት የሚፈልገውን ሥራ እየሠራሁለት እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ እዚህ ዕውነተኛ - ትርጉም ያለው ደስታ ይሰማኛል - አካላዊም፣ መንፈሳዊም፡፡ የአባቴን ትዕዛዝ ስፈጽም ህሊናዬ የአባቴን ማግኛ መንገድ ሰጠኝ የምልበትን ዘዴ ያገኘ መስሎ ይሰማኛል! ስለሱ አስቤ፣ አሳስቤ፣ ከሰው ጋር በልቼ፣ ጠጥቼ ስሄድ፤ ነብሱን አግኝቼ የተመለስኩ ይመስለኛል፡፡
አሁን ራኬብ (የኔን መካከለኛ ሴት ልጅ ማለቱ ነው) በምን እንደምትደሰት ካወቅክ ከዚያ በላይ ደስታ የለም፡፡ አባቴ መሞቱን ሁሉ እረሳዋለሁ፡፡ ይህ አገር ለእሱ ምን ያህል እንደሆነ ስለማውቅ እዚህ ስመጣ የማስደስተው ይመስለኛል - የት አግኝተህ ነው የምታስደስተው ብትለኝ - ዘሙቴ ስመጣ! የሱን ሥራ ስሰራ፣ ያዘዘኝን ስፈጽም፣ ሁሉን ነገር ፈጽመህ ስታበቃ ፀጉርህን ስለማይደባብስህ ብቻ ባዶነት አይሰማህም - ፈቃዱን ሞልተህለታላ! ከሱ በመወለዴ በጣም ደስተኛ ነኝ!”
“እናትህስ?” አልኩት፡፡
“እናቴ በጣም ታታሪ፣ ጠንካራ አሳቢ ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ ግን ፈጣሪ በፈለገ ጊዜ ጠራት፡፡ ማሪያምም የጌታ እናት 64 ዓመት ነው የኖረችው - የእኔ እናት ማናትና ነው ከሷ በላይ የምትኖረው? ንጉሥ ወልዳ፤ ማሪያም 64 ዓመት ነው የኖረችው! በአምላክ መፀፀት የለም፡፡ ዘሙቴ ላይ ያለው አንድ ሣር፣ ዘሙቴ ላይ ያለው አንድ እንሰት፣ አንድ ጐጆ… ለእኔ ትርጉም አለው! እናቴን ያህል ነው! መንፈሣዊ ኃይል ይጨምርልኛል፡፡”
ኮስተር ብሎ፣ በተመስጦ ነው የነገረኝ፡፡ እኔም ቀጥዬ፤
“ዕውነት ነው፡፡ አንተ አሜሪካንን አይተኸዋል፡፡ የኒውዮርክን ህንፃ አይተኸዋል፡፡ የከተማውን ብልጭልጭ አይተኸዋል… እዚህ ግን ያየሃት ቅንጣት ዕፅዋት፣ ቅንጣት እንሰት፣ ደሳሳ ጐጆ፣ ብርቱ ትርጉም ሰጥታሃለች፤ ቤት አለኝ የሚያሰኝ እፎይታን አጐናፅፋሃለች፡፡ እትብት ናት፡፡ አሁን በምሳሌ ብንጠቅስ፤ ወ/ሮ ታደለች (ሚኒስትሩ፣ አምባሳደሩ) ጤና ኬላ ታሠራለች ብለውኛል፡፡
እገሌ ቤተክርስቲያን፣ እገሌ ሆስፒታል፣ እገሌ ት/ቤት ወዘተ እያሠሩ ነው ብለውኛል፡፡ እነ የምሩን፣ እነጌቱ ኮሜርሻል፣ እነ ዲኤች ገዳን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ባለወልድ ቤተክርስቲያንን አቶ ባህሩ ሠርተዋል፡፡ ሁሉም በየራሱ መንፈስ ውስጥ የሚያስደስተውን ነገር ሠርቷል፤ ለሥርህ፣ ለትውልድ ቦታህ፣ የመቆም ስሜት ይሰማል፡፡
እዚህ ውስጥ ደም ይዘዋወራል፡፡ ነፍስ አለ፤ ነበርም፡፡ ከዚያ ስታሰፋው ልማት፣ ውድድር፣ አገር፣ መንግሥት ወዘተ አለው፡፡ በግልጽ መናገር እንደሚቻልህ፤ ትውልድ ቦታ ውስጥ ቀጭን ረዥም ጠንካራ እትብታዊ ክር አለ… በየዓመቱ ታስባቸዋለህ ማለት ነው?”
“አንተ እናት አባትህን ታስብ ዘንድ እግዚአብሔር ገልፆልሃል፡፡ በመንፈስ ተገናኝተህ ትመለሳለህ፡፡ እንሰት ቆጥረህ ይሆናል፡፡ ግቢውን ተቆጣጥረህ ይሆናል፡፡ ለከብት አጋጆቹ ረድተህ ይሆናል… ግን ይህን ሁሉ ለአባትህ ለእናትህ ነው ያደረከው! እኔ ለራሴ ስሜትና ነብስ ቅርብ የሆነውን ነገር ነው እማስተናግደው፤ የመጣሁትም ለዚህ ነው!” አለኝ፡፡
እኔም ቀጠልኩና፤
“ሰው ያለመላ እዚህ ቦታ ድረስ ዝም ብሎ አይመጣም፤ ግርማ ነግሮኛል፡፡ ከግርማ ከታላቅ ወንድምህ ስወያይ ያባትን በረከት እሺ ማለት ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ (የፀጋ - ብቅል ይለዋል ጸጋዬ ገ/መድህን) እንዳባቱ ፈቃድ በባህላዊ መንገድ አግብቶ ጥሩ ሴት ስትገጥመው ደግሞ የበረከቱን ጉልበት ታያለህ! የመንፈስ ቋጠሮ ይዘህ እንደመጓዝ ነው! የልብህ ሲሞላ በኩራት በደስታ ትጓዛለህ!
በዚህ 3-4 ቀን ኃይለኛ መንፈሳዊ ትስስር ነው ይዘህ እምትሄደው - ነፍስህን ነክቶሃላ!
ተፈጥሮ ይስብሃል - በራሱ ሰዓት ያመጣሃል፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ለመነጋገር ይቻላል የሚሉ ብዙ ቲዎሪዎች አሉ - ከነሱ አንዷን እኔ አግኝቻለሁ፡፡”
ዘሙቴ መግቢያ አፋፉ ላይ አረንጓዴ ነው፡፡ ግራ ቀኙ አረንጓዴ ነው፡፡ እየቀረብኩኝ ስሄድ፤ በገጣሚ ሆዴ እንዲህ አልኩኝ፣
ተራራው ላይ የተፈረፈረ አፈር አታይም፡፡ አረንጓዴው ጋራ ሰማዩን እየሳመ ነው፡፡
የአረንጓዴው ጋራ ግርጌ ወንዝ ነው፡፡ ሀቀኛ ልምላሜ የራባቸው ዐይኖች እዚህ ይጠግባሉ፡፡ ተፈጥሮ ሊመግብህ ይጠብቅሃል፡፡ አስፈላጊ ተፈጥሮአዊ ትእዛዛትና ፍቅር እዚህ አሉ፡፡ የአረንጓዴ አገር ተፅእኖ ያቅፍሃል - ይደግፍሃል፡፡ በልብህ ክትፎ ብቻ አስበህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡ ተፈጥሮ የራሱን ክትፎ አምርቶ ይጋብዝሃል፡፡ መስቀል ብቻ ሳይሆን የዝንተ-ዓለም በዓል እዚህ አለልህ!
ዘሙቴ በየውስጣችን አንድ አንድ ነገር ይፈጥራል፡፡ “ከከተሜ አርቲፊሻል ህይወት ተላቀቅ፣ ሁለት እጆቼን ዘርግቼ እጠብቅሃለሁ” ይልሃል፡፡
ይህ ቦታ፤ “የጉራጌ ሀብቱ ምርቃቱ!” እያለ ደጋግሞ “ኬር! ኬር! ኬር!” እያለ መንፈስህን ምሉዕ ያደርግልሃል፡፡
ምርቃት በጉራጌ ምድር ዋና አንጡረ-ሀብት (Resource) ይመስለኛል፡፡ ማለቂያ የሌለው ምርቃት ነው! መንፈስህን የሚያላውስ ቃል ውስጥህ ይገባል፡፡ ቃል ይገባልሃል… ቃል ያስገባሃል… ከዓመት ዓመት ያለ ጥርጥር ያደርስሃል!! ያመላልስሃል!! ኬ…ር ይሁን ትላለህ!
እስቲ ደግሞ የዘሙቴ ማሪያም ቀዳሽ - ቄስ አብርሃም ታደሰ ያለኝን ላካፍላችሁ፡-
“ከየት ነዎት አባቴ?” አልኳቸው፡፡
“ጐንደር አካባቢው ወንዝ ዳር ላይ ነኝ፡፡ ከላስታ አዲሳባ መጣሁ፤ የቀን ሥራ ሞከርኩ፡፡ ከዚያ አንድ አባት አገኙኝና አማኑኤል (አዲሳባ - መርካቶ) አስገቡኝ - ሙዳየ ምፅዋት፡፡ የካሡ ዑርጂ እናት የሚባሉ ወስደው የማሪያም ዘካሪ አደረጉኝ፡፡ እሳቸው ሞቱ፡፡ ካራቆሬ ነው ቤታቸው - አፈላልጌ ለቅሶ ደረስኩኝ! እዛ ካሡን አገኘሁት፡፡ “ጥሩ ቤ/ክርስቲያን ልውሰድዎትና ለምን አስተዳዳሪ አይሆኑልኝም?” አለኝ፡፡ “የት አገር ነው?” ስል፤ “ጅማ” አለኝ፡፡ “እስቲ እንግዲህ እግዚሃር ያውቃል፤ ላስብበት” አልኩት፡፡ በሌላ ቀን አማኑኤል ቤተክርስቲያን ተገናኘን፡፡ “ጅማ ይርቀኛል” ስለው “እሺ እኔ የተወለድኩባት አለች - ዘሙቴ ማርያም የምትባል” አለኝ፡፡ “ወየት” ነው ስል “ሶዶ ጉራጌ በኩል ነው” አለኝ፡፡ “እስኪ መጀመሪያ ቦታውን ልየው” አልኩኝ፡፡ ይዞኝ መጣ - 2006 ዓ.ም ትዕሣሥ ማሪያም ማለት ነው፡፡ ቀደስኩኝ - ቦታውን አየሁትኝ፡፡ አካባቢው ገደላ - ገደል ቢሆንም ገዳም ስለሆነ በጣም ደስ አለኝ፡፡ እሺ እመጣለሁኝ አልኩትኝ፡፡ ባለቤቴንም ልጄንም ይዤ እመጣለሁኝ አልኩትኝ፡፡ በገዳሙ ልቀመጥ ይዘውኝ መጡ፡፡ አሁን ከቤተክርስቲያኒቱ ውጪ ያለ አቶ መኩሪያ መርጊያ ቤት እኖራለሁ፡፡ 8 ወሬ ነው፡፡
(የክትፎ አይቤና ጐመን ቁርስ መጣ በማህል፡፡ በጣባ ሳይሆን በእንቅብ እየተሻሙ አጋፋሪዎቹ ብሉ የሚሉ ይመስላሉ፡፡ የክትፎው ጠዋት ጀመረ!)
በዘሙቴ መብላት፣ መጠጣት፣ ማስቀደስ… መጫወት… መዝናናት… መመረቅ…. ያለ ነገር ነው፡፡ የማቱሳላ እድሜ ይስጥህ ትባላለህ፡፡ …
“ማቱሳላ ብዙ ኖሮ አልሰራም፡፡ አብርሃም ግን ብዙ ሰርቷል” አለ አንዱ አባል እንደ ሂስ፡፡
“የአብርሃም እድሜ … የሥራ ዕድሜ ይስጥህ” በሉኝ አለ ግርማ በማከል፡፡ መረቁት፡፡ “እድሜህ ይስፋ!” …. “አሜን!” አለ፡፡ በጉራጊኛ ጨማመረበት አቶ ካሳ ማረኝ፡፡ አባ አሳረጉ፡፡ ትላልቅ ሰዎች ቦታችንን ስለረገጡልን እግዚአብሔር ያክብርልን! ላመት ስቦ ለዚች ምድር ያድርሰን - አቡነዘበሰማያት!” አሉ፡፡ በግእዙ ቀጠሉና በመጨረሻ “ስናውቅ በድፍረት፣ ሳናውቅ በስህተት የሰራነውን እግዚአብሔር ይፍታን!” አሉ፡፡
እንግዲህ እኛ መስከረም 20 ሄደን በ21 ማሪያምን አክብረን ሐሙስ እርድ ነው… አርብን ቆይተን … ቅዳሜን ውለን … ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ ልንገባ ነው፡፡ አራቱ ቀናት ብዙ ደስታና ፌሽታ ያጨቁ ነበሩ፡፡
ስለዘሙቴ ከሚያውቁ ነዋሪዎች አንዱ ጋር ተጨዋወትን፡፡ ስሙ ካሳ ማረኝ ይባላል፡፡ ማሪያም አጠገብ ነው ቤቱ፤ ትውልድ ቦታውም፡፡ ለኩ ነበር የሚኖረው፡፡ “አባባም (ነብሳቸውን ይማር አቶ ጃቢር ቱፈርን ነው) ወደለኩ ይሄዳሉኮ ዛሬ” ስለው፤ “አዎ ከሳቸውማ የወንድማማቾች ልጆች አደለንም እንዴ?” አለና ቀጠለ፡፡
“የአባቶች ታሪክ አልረሳም፤ ታሪክም መከታተል እወዳለሁ፡፡ እነማን ዘሙቴንና ማሪያምን ቆረቆሩዋት የሚለውን መሰለኝ የፈለከው…” አለ ካሳ ራሱ ለራሱ ቃለ-መጠይቅ ፈጥሮ፡፡
“አዎ… ማሪያም ቆርቆሮ አልነበራትም ያኔ ሲሉ ሰምቻለሁ!... ኪዳነምህረት የመጀመሪያ ናት… በዚያን ወቅት የዱሮ ሰዎች ቀብር ይርቀናል በማለት ዘሙቴ ማርያም እንድትቆረቆር ፈለጉ፡፡ ተጋድሎ አደረጉ - ያለትግል መሰረት ያለው ነገር ይገኛል እንዴ?... አይገኝም፡፡ ….በዚያን ሰዓት ከነበሩት አንዱ የእኔ አያት ነበር፡፡ መሀይም ቢሆንም እዚያ ነበር፡፡ ሻሚሮ ዳውቴ ይባላል፡፡ ሁለተኛ በቅስናው የሚመሩት ቄስ ደምቢሶ ይባሉ ነበር፡፡ በቅስና ያገለግሉ ነበር በዚያን ዘመን፡፡ ያኔ ነው የተቆረቆረችው፡፡ የመጀመሪያ ጣሊያን የገባ ዘመን - ከ40 ዓመት በኋላ እመጣለሁ ሲል (የሚኒልክ ጊዜ ማለቴ ነው)፡፡ ሲወርድ ሲዋርድ ያኔ ማርያም ነበረች፡፡ 100 አመት በላይ ነው፡፡ የታገሉት ጃቢር ቱፈር፣ ታደሰ ተክሌ፣ ዋኬኔ ፈልዳሶ ወዘተ ነበሩ፡፡ ከሳር ወደ ቆርቆሮ ተቀየረ… ማቴሪያሉን አቶ ታደሰ ተክሌ ነው የቻሉት… አጥሩንም… ከ80 ዓመት በላይ ናቸው ሰዎቹ….
“እንዴት ቦታው ተመረጠ?” አልኩት አቋርጬ፡፡
በጥንት ሰዎች ነው - ተወያዩ… ተስማሙ…. መረጡ… መሰረቱ!
“ሌላ ቦታ ቤተክርስቲያን ሲሰራ ወይ በራዕይ ወይ በባህታዊ ህልም ወዘተ የሚመላከት አለ… እዚህ ግን እንደዛ አደለም፡፡”
“አዎ ሌላ ትውፊት የለውም፤” ደቡሬና ደምቢሶ ናቸው፡፡ ቀዳሹ ሀብቱ ናቸው፡፡ ዲኖ ጊዮርጊስንም ቆረቆሩ… ቀጠሉ፡፡ እየቆረቆሩ ነው የተጓዙት፡፡ ዋጮ እሚባል አገር ነበር መጀመሪያ አባ ወልዶ ከጐንደር ሲመጡ ያረፉት፡፡ (ሙኸር ውስጥ ወጮ፣ ቆላ ሳለል ምድረ-ከብድ ገዳም አሉ - የአባ ወልዱ ልጆች ካህናት ናቸው፡፡ ሁሉ አገር ተበትነዋል፡፡ አይመለል፣ ዋጮ፣ ላሊጌና ታቲጌ እሚባልም ውስጥ አሉ - እዚህ ግማሽ ጋሻ ይዘው ተተከሉ፡፡ ሁሉም የደምቢሶ ልጆች እዚያው ናቸው፡፡ ቀዳሾቹ ራሳቸው ነበሩ፡፡
ቤተክርስቲያኗ ልትዘረፍ ነበር ያኔ፡፡ 200 ዓመት ግድም በለው፡፡ የካህን መንደር ነው፡፡ … ደበላ ደምቢሶ፤ ምህረቱ ደምቢሶ፣ ተክሌ ደምቢሶ፣ ወልዴ ደምቢሶ… የልጅ ልጅ ናቸው! ሌሎቹ እነ ታደሰ ተክሌ፣ ካሳዬ ወልዴ፣ አበበ ደበላ፣… ይወርዳል፡፡”
“ጥምጥሙ እኛጋ ነው ያቆመው” አለ ግርማ አከል አድርጐ በመቀለድ!
ዛሬ ዛሬ ቀዳሾች ይከፈላቸዋል፡፡
“ዘሙቴ ምን ማለት ነው?”
“ታላቅ አገር ማለት ነው፡፡” ወደ ላይ የዋጮ ገበያ አለ፡፡ እዚያ ታዲያ ሰዉ ገበያ ለመግባት ሲፈልግ “ቆይ ዘሙቴ ይውጣለት” ይሉ ነበረ፡፡ ታላቁ መጀመሪያ ይገበያይ እንደማለት ነው፡፡ ቀደምትና ታላቅ ማለት ነው፡፡… በዘሙቴ በአንድ ገበሬ ማህበር 3 ደብር አለ፡፡ ዘና መድኃኒዓለም፣ ኪዳነምህረት፣ ዘሙቴ ማርያም፡፡ ሌላው አገር አንድ ብቻ ነው፡፡ዘና መድኃኒዓለም ወ/ሮ ታደለች (የቀድሞ ሚኒስትሯና አምባሳደሯ ማለቱ ነው) ጤና ኬላ እያሰራች ያለችበት ነው፡፡ የእናቷ አገር ነው፡፡ ያባቷ ዘሙቴ ማርያም ነው፡፡ ዙሪያው እነገድር፣ ዡጋን፣ በኬ ቢሳንጅልባ ይባላል፡፡ በዚህ አጨበር፡፡ ከክልል 4 ይዋሰናል ዳሩ፡፡ ይሄ ክልል 7 ነው፡፡”
“አንተ መቼ ተወለድክ?” አልኩት፡፡
“በ1951 ነው የተወለድኩት፡፡ መደበቅ አያስፈልግም - ስድስት ልጆች አሉኝ፡፡ ስራዬ እንሰት ነው፡፡
“የዘሙቴ ቤተክርስቲያን መቼ መቼ ትከበራለች - ለክብረ በዓሏይከበራል?” አልኩት፡፡
“ጥር ማርያም፣ ታህሣሥ 29 ለገና እና መስከረም 21፡፡ በሣምንት ማጠንት አለው በወር ይቀደሳል፡፡”
“ያኔ ሳር ቤት ውስጥ ይቀደሳል ማለት ነው?”
“አዎ፡፡ አሁን ግን ተተኪዎቹ ልጆች እያሳደጓት ነው! ዋናው መንገድ የዛሬ 2 ዓመት ከተሰራ እያደገች ናት፡፡
አለበለዚያ ያ አሣር የሚያሳይ ተራራ ነበር የሚፈታተነን… መንበሩን የሰጡ ብርሃኑ ኢዶ ናቸው…”
አባ በመሀል ገብተው አንድ ታሪክ ተረኩልኝ፡፡ ቄስ አብርሃም ታደሰ ነው ሙሉ ስማቸው፡፡
“ከአባቶች የሰማሁት ታሪክ ነው፡፡ አካባቢያችን ያሉ ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ አባት አሉ - ኃይሉ በየነ ይባላሉ፡፡ ሲያጫውቱኝ ታዲያ ቤተክርስቲያኒቱ ከተተከለች በኋላ ጠባቂ ተደረገላት - ግቢ ውስጥ፡፡
ጠባቂው ጦር ይዘው ሲጠብቁ አንቀላፍተው ኖሯል፡፡ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሌባው ፅላት ይዞ ሲወጣና እሳቸውን አልፎ ወደበሩ ሲያመራ፤ ነብር ድንገት መጥቶ አገደው፡፡ ነብሩ ፊት ፅላቱን ጥሎ ሰውዬው ጠፋ፡፡ ህዝቡ ደርሶ ፅላቱን መለሰ፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌባ እንደልማዱ ቤተ መቅደሱን ገልጦ ፅላቱን ይዞ ሲሄድ፤ መውጫው ላይ ሁለት እግሩን እባብ ተጠመጥሞ አስሮ አስቀመጠው፡፡ ፅላቱን አስጣለው!” የሚል ነው፡፡
(ይቀጥላል)  



Read 4730 times