Saturday, 25 October 2014 10:22

‘ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው “የሚዜው ፈዛዛ…” ምናምን ሊባልለት ቀን ተቆርጧል፡፡ እናላችሁ…በመሀል ከአንድ ከሌላ እንትና ጋር እንደምትታይ ይነገረዋል፡፡ እሱም ለማጣራት ሲከታታል ከሆነ ሰው ጋር ያያታል፡፡ እሱም ከእንግዲህ የለም የእነታ እንጎቻ ከመባሏ በፊት ያልተጠናቀቁ ፋይሎችን እየዘጋች ነው ብሎ ግራ ይገባውና ጥቂት ጓደኞቹን ያማክራል፡፡ እናላችሁ…ያገኘው ዋናው ምክር ምን መሰላችሁ…“ተዋታ!  ደግሞ ሞልቶ ለተረፈ ሴት!...” ምናምን የሚል ነው፡፡ አብሯት ታየ የተባለው ሰው ከውጪ የመጣ ዘመዷ ሆኖ ለካስ ለሠርጓ ሸመታ እያገዛት ነበር፡፡
አንዲት ወዳጃችን ምን አለች መሰላችሁ…‘ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው፡፡’ በአጉል አጉል ውሳኔ ላይ የደረሰውን ቤቱ ይቁጠረው!
እናላችሁ…የምር አስቸጋሪ ነው…የዘንድሮ ‘መካሪዎች’ መሣሪያችን መገንቢያ ሲሚንቶና አሸዋ ሳይሆን ማፍረሻ ዲጂኖ እየሆነ ነው፡፡ “ተይዋ!… አገባሽ እንጂ አልገዛሽ!” ምናምን የተባሉ እንትናዬዎች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የመጠራጠር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙኝማ…ሔዋን ሆዬ አዳም ሌላ ሴት ለምዷል ብላ ትጠረጥረዋለች፡፡ ምክንያቱም ማታ ይወጣና እስኪነጋ ተመልሶ አይመጣም፡፡ በእሷ ላይ እየማገጠ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት ወሰነች፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ማታ ለሽ ብለው እንደተኙ ምን ብታደርግ ጥሩ ነው…የአዳምን የጎድን አጥንቶች አንድ፣ ሁለት ብላ ቆጠረች፡፡ ልክ ነዋ!…አንዲት አጥንት ብትጎድል ኖሮ ሌላ ሔዋን ‘አሠርቶ’ እነሆ በረከት እየተባባለ ነው ማለት ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ… (ምርቃት– አንድ ቀን ሔዋን አዳምን “አዳምዬ፣ ትወደኛለህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ አዳም ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“ምን አማራጭ አለኝ!” አሪፍ አይደል! ‘አማራጭ ስለሌለ’ የተወደዳችሁ እንትናዎችና እንትናዬዎች ‘ስታተሳችሁን አፕዴት’ አድርጉልንማ!)
እናላችሁ…ብዙ ጊዜ በተለይ በትዳርና በጾታዊ ግንኙነቶቸ አካባቢ የሚሰጡ ምክሮች…አለ አይደል… ያሉትን ቀዳዳዎች ከመድፈን ይልቅ ተጨማሪ ቀዳዳዎችን የሚጨምሩ አይነቶች ይሆናሉ፡፡ “እስቲ ምከሩበት!”  “ረጋ ብላችሁ ተነጋገሩበት…” ምናምን ከማለት ይልቅ “አንቺ በሰለጠነ ዘመን እንዲህ አትሁኚ እንጂ! ስንቱ እግርሽ ላይ ወድቆ የሚለምንሽ እያለ የምን እሱን ማባበል ነው!” አይነት ምክር ይበዛል፡፡
ስሙኝማ…ደስ የሚሉ የየዋሃን ወዳጅ ምክሮች ደግሞ አሉላችሁ፡፡
“ስማ፣ ትንሽ ገንዘብ ጠርቀም አድርግና አንዲት ካፌ ወይም ናይት ክለብ ቢጤ ለምን አትከፍትም!”
“ለታክሲ ከምትገፈግፍ አንዲት ቪታራ ቢጤ ለምን አትገዛም!”
“እየው፣ ወደዚህ ወደ አያት አካባቢ መሬት በሊዝ ይዘህ ለምን የሆነች ጂ ፕላስ ዋን ነገር አትቀልስም!”
ምን ይደረግ… ‘ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው፡፡’
ደግሞላችሁ…ዘንድሮ ለየት ያሉ ምክሮች አሉላችሁ…አለ አይደል…‘የአገርና የዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ’ የሚባሉ አይነት፡፡
“ስማ፣ አጉል ፕሪንሲፕል፣ ህሊና ጅኒ ጅቡቲ እያልክ እንዲሁ እንደ ደረቅህ ከሰው በታች ሆነህ ቀረህ፡፡ አሁን አንተ በሀይገር ስትጋፋ ሰው ጉድ አይልም! ከሰዎቹ ጠጋ ብትል እኮ፣ አይደለም እኛ፣ እኛ… ቀበሌ እንኳን ቀና ብላ አታይህም! ትናንትና ሱሪያቸውን እንኳን ከእኛ ለምነው ሲያስጥፉ የነበሩት እነእንትና ውሀ የመሳሰሉ መኪኖች ሲያሽከረክሩ አታይም!”
“እመነኝ ነው የምልህ… እሷን ልጅ ሙጭጭ ብለህ ያዝ፡፡ ለሽርሽር ጎርሜ ወንዝ ቋጥኝ ላይ ከምትቀመጥ ዱባይና ኒው ዮርክ እግርህን ሰቅለህ ትጠጣለህ፡፡ እሷ የማታውቀው ሰው አለ መሰለህ! ኸረ በእናትህ አትንከርፈፍ፣ ለእኛም ፍርፋሪ እንኳን ይድረሰን!“
“ዝም ብለህ በየግሮሰሪው ድራፍትህን ከምትገለብጥ፣ የፈለገው ቦታ ይሁን ብቻ የሆነ ቦተሊካ ማህበር ውስጥ ግባ፡፡ ወይ ፈረንካ፣ ቤት ምናምን ታገኛለህ፡፡ አለበለዛ ደግሞ አውሮፓና አማሪካን ትንሸራሸራለህ…”
ምን ይደረግ… ‘ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው፡፡’
ስሙኝማ…ሶቅራጥስ እንዲህ አለ ይባላል፡፡ “እንደምንም ብለህ ሚስት አግባ፡፡ ጥሩ ሚስት ከገጠመችህ ደስተኛ ትሆናለህ፡፡ መጥፎ ሚስት ከገጠመችህ ደግሞ ፈላስፋ ትሆናለህ፡፡” አሪፍ አይደል! ሕዝቤ ከመሬት ተነስቶ “የኒቼ አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋኝ!” ምናምን የሚለው ለካስ…ተዉትማ! እንኳንስ ደረስንበት፡፡ እኛ እኮ…“ይሄ ሰውዬ ሥራው ፍልስፍና መጽሐፍት ውስጥ ተቀብሮ መዋልና ማደር ሆነ!” እንል ነበር፡፡ (ስሙኝማ እንትና…ከእንትናዬህ ጋር እንዴት ናችሁ? ይቅርታ፣ ጥያቄዬን ላስተካክል…“ቀን የሰጠው ድንጋይ የቤተመንግሥት ግንብ ይሆናል…” ያለው ፈላስፋ ማን ነበር? ይህን ከመለስክልኝ ከእንትናዬህ ጋር እንዴት እንደሆናችሁ አንተ ሳትነግረኝ እኔ አውቀዋለሁ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ደግሞላችሁ…ሳንነጋገር እንዲሁ በስሜት በመግባባት የተለዋወጥነው ምክር አለ– ከዕድሜ ላይ መገንደስ! ብዙዎቻችንን የሚለያየን የ‘አገነዳደሳችን ጭካኔ’ ነው፡፡ ስሙኝማ…መቼም የዕድሜ ነገር ያው ‘የዕድሜ ነገር’ አይደል… ባልና ሚስት ሆዬ በሚጋቡበት ጊዜ “ስንት እንቁጣጣሽ ኖርክ…” “አባትሽ ዘጠና ሁለት ከሞላቸው አንቺ ስንት ዓመት ሆነሽ ማለት ነው?” ምናምን ነገር አልተባባሉም፡፡ (ስሙኝማ…አንዳንዶቹ ‘ካፕሎች’ ዕድሜ ሲቆጣጠሩ የሚገነድሱት ዕድሜ እንደ ብር ቢቆጠር ‘ስሞል ቢዝነስ’ ምናምን ያቋቁም ነበር የሚባለው እውነት ነው? እንዲሁ ለማወቅ ያህል ነው…ለሁለት ‘ቲንኤጀር’ ልጆቻቸው ያለማዳላት እኩል፣ እኩል ማካፈል የሚችሉትን ዕድሜ ስለሚገነድሱ ሰዎች በጭምጭምታም ቢሆንም ሰምተናላ!)  
እናላችሁ…ሚስት ሆዬ ደግሞ ዕድሜዋ የገፋ እንዳይመስል የተቻላትን ትጥራለች፡፡ እናማ፣ አንድ ቀን ገበያ ትወጣና ልዩ ልዩ መዋብያ ቅባቶች፡ ‘አይ ሻዶ፣’ ‘ማስካራ’ ቅብጥርስዮ ነገሮች ገዝታ ትመጣለች፡፡ ግማሽ ቀን ሙሉ መኝታ ቤቷን ቆልፋ ራሷን ስታሰማምር ትቆያለች፡፡ ከዛላችሁ…ባል ከሥራ ሲመጣ አይቷት ደንገጥ ይላል፡፡
ሚስትም እንዲሀ አለችው፣
“የእኔ ፍቅር፣ አንድ ነገር ልጠይቅህ፡፡ ሳትደብቅ ስሜትህን ትነግረኛለህ፡፡ እኔን ከዚህ ቀደም አታውቀኝም አሉ፣ አሁን ገና ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኸኝ፡፡ ገምት ብትባል ዕድሜዬ ስንት ይመስልሀል?” ትለዋለች፡፡ እሱም ከእግር እስከ ራሷ ያያታል፡፡
“ቆዳሽን ሳየው የሃያ ዓመት ኮረዳ ትመስያለሽ፤ ፀጉርሽን ሳየው የአሥራ ስምንት ዓመት ልጃገረድ ትመስያለሽ፣ ቁመናሽን ሳየው የሀያ አምስት ዓመት ሎጋ ትመስይኛለሽ፣” ይላታል፡፡
ሚስት ሆዬም ደስ ብሏት “አመሰግናለሁ የእኔ ፍቅር፣ አመሰግናለሁ!” ብላ ትጠመጠምበታለች፡፡ ይሄኔ “ቆዪ እንጂ፣ አትቸኩይ፡፡ መች ጨረስኩና…” ይላታል፡፡ እሷም ኮስተር ብላ “ምን ቀረህ?” ትለዋለች፡፡ ምን ቢላት ጥሩ ነው… “ገና መቼ ቁጥሮችን ደመርኳቸው!” ብሏት እርፍ!
እናማ… እንትናዬዎች፣ ዕድሜ በአካል ክፍል ተበታትኖ ሲገመትባችሁ ነገር አለውና “የቀጠሮ ሰዓት ደረሰብኝ…” ብላችሁ ሽው በሉማ!
እናላችሁ…የዘንድሮ ምክር አስቸጋሪ ነው፡፡
አቤቱታ… “መሥሪያ ቤት’ኮ በጭቅጭቅ አላስቀምጥ አሉኝ፡፡”
ምክር… “አንተ እዛ ቤት ቆርበሀል እንዴ!  ለምን ትተህላቸው አትወጣም!”  
መሥሪያ ቤት ለቆ መውጣት… “ቤት እንቀይር…” እየተባለ ከቡና ቤት፣ ቡና ቤት እንደመሸጋገር የሚቀል ይመስል፡፡
አቤቱታ… “ባለቤቶቹ አምስት መቶ ብር ቤት ኪራይ ጨምረውበኝ አራት ሺህ ብር አደረጉት፡፡
ምክር… “ትተህላቸው ውጣ! ደግሞ ለሞላ ኮንዶሚነየም!”
የሚከራይ ቤት ማግኘት እንዲህ ቀላል ይመስል… (“ቺኮች ፒክ እንደማድረግ…” የሚለውን ‘ማጣቀሻ’ የሚያነሱ ሊኖሩ ይችላሉ…)
ምን ይደረግ… ‘ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው፡፡’
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የ‘ምክር’ ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው መንገድ ላይ እየሄደ እያለ ድንገት የሆነ ድምጽ… “ባለህበት ቁም! አንድ እርምጃ ከጨመርክ ድንጋይ ይወድቅና ያልቅለሀል!” ይለዋል፡፡ ሰውየውም ይቆማል፡፡ ወዲያውኑ ከፊት ለፊቱ አንድ ድንጋይ ይወድቃል፡ ዘወር ብሎ ሲያይም አጠገቡ ማንም አልነበረም፡፡
እንደገና መንገዱን ይቀጥላል፡፡ የቅድሙ ድምጽ እንደገና… “ባለህበት ቁም! አንድ እርምጃ ከጨመርክ እየፈጠነ የሚመጣ መኪና ይበላሀል!” ይለዋል፡፡ ሰውየው ቀጥ ይላል፡፡ እንደ ነፋስ የሚበር መኪናም በአጠገቡ ያልፋል፡፡ ይሄኔ ግራ ይገባውና… “ለመሆኑ አንተ ማነህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ድምጹም “እኔ ጠባቂህና መካሪህ መልአክ ነኝ፣” ይለዋል፡፡
ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው… “ታዲያ መካሪዬ ከሆንክ ላገባ በወሰንኩ ጊዜ የት ነበርክ!” ብሎት እርፍ! ሚስት ጉዷን አልሰማች!
አንዱ ጠበቃው ለደንበኛው ስለሆነ ጉዳይ ምክር ይሰጠዋል፡፡ በመጨረሻም… “ሁለት መቶ ብር ክፈል…” ይለዋል፡፡ ሰውየውም “ለምን ብዬ ነው የምከፍለው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ጠበቃውም፣ “ምክር ስለሰጠሁህ ነዋ… ይለዋል፡፡ ደንበኛ ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ምክርህን መቼ ተቀበልኩና!”
“ምክርህን መቼ ተቀበልኩና!” ማለትን አንድዬ ያስለምደንማ!
‘ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል’ ቢሆንም…አለ አይደል… ‘በወንፊት ማጥራቱ’ የእኛው ፋንታ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 14226 times