Saturday, 25 October 2014 10:16

ዘጠኝ ፓርቲዎች በትብብር ለመስራት ተፈራረሙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ኢ/ር ይልቃል በሰብሳቢነት ተመርጠዋል

ዘጠኝ ህብረ ብሄራዊና ብሄር ተኮር ፓርቲዎች በአገሪቱ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የትብብሩ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የትብብር ስምምነቱን የፈረሙት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፣ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ)፣ የሶዶ ጎርዶና ህዝብ ዴሞክራሲዊ ድርጅት (ሶጎህዴድ)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ)፣ የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢህዴህ)፣ የከምባታ ህዝቦች ኮንግረስ (ከህኮ) እና የጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌህዴድ) ሲሆኑ የትብብር ስምምነቱን የመሰረቱት በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ለመስራት እንደሆነም ከትላንት በስቲያ በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዋና ጉዳዮች የተባሉት ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ተአማኒ ምርጫ እንዲኖር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በሚመለከት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡
“የትብብር ስምምነቱን ለመመስረት ጉዞ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል” ያሉት ሰብሳቢው ኢ/ር ይልቃል፤ በተለይም እስካሁን የተደረጉ የትብብር ጥረቶች ለምን አልተሳኩም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስና መፍትሄ ለመስጠት የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ባደረጉት ግምገማና ዳሰሳ ውጤት ላይ በመመስረት ለእነዚህ የግምገማ ውጤቶች ምላሽ ለመስጠት በጋራ የሚሰሩበትን የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡ የትብብር ስምምነቱም በአገሪቱ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡ ስምምነቱ በዋናነት በ2007 ምርጫ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች በጋራ የሚቆሙበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት አጠንክረው በመቀጠል በኢትዮጵያ መምጣት ያለበትን ለውጥ መሰረት በማድረግ በትብብር ለመስራት የሚችሉበትን ጠንካራ የጋራ የፖለቲካ ኃይል ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ለትብብር ስምምነቱ ባደረጋችሁት የዳሰሳ ጥናት እስከዛሬ ለትብብሩ አለመሳካት እንቅፋት ሆነው ያገኛችኋቸው ምክንያቶች ምንድንናቸው? የትብብር ስምምነቱን የተፈራረማችሁ ፓርቲዎችስ እርስ በእርስ ምን ያህል ተዋውቃችኋል?” በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ “እስከዛሬ ትብብሮች ያልተሳኩት እርስ በእርስ አለመደማመጥ፣ የፖለቲካ ባህሉ የሃሳብ ልዩነቶችን የሚያከብር አለመሆን፣ በጠራ ሃሳብ ላይ የቆመ ወጥ ሃሳብ አለመኖርና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሲያጠፉ እነሱን መናገር የተቃውሞውን ጎራ ይጎዳል በሚል ነገሮችን አለባብሶና አደባብሶ ማለፍ ስለነበረ ነው” ብለዋል፡፡ ፓርቲዎች ምን ያህል ተዋውቃችኋል የሚለውን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም፤ “ፓርቲዎች ስምምነት ላይ የደረሱት በአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ላይ በትብብር የተግባር ስራ (functional relation) ለመስራት እንጂ የመዋቅር ጉዳይ ባለመሆኑ ችግር አይፈጠርም” ብለዋል፡፡ ለትውውቁም ቢሆን በቂ ጊዜ ነው፤ ይህ ስምምነት ከ33ቱ ፓርቲዎች ትብብር ጥንስስ የመጣ ነው ያሉት የትብብሩ ኃላፊዎች፤ ግንኙነታችንን አጠንክረን እስከ ውህደት የሚያበቃንን የረጅም ጊዜ እቅድም ታሳቢ አድርገናል ብለዋል፡፡ እስከዛሬ ብዙ ትብብሮች አልተሳኩም፤ ይሄኛውስ ለቀጣይነቱ ምን መተማመኛ አለው፣ ብሄር ተኮርና ህብረ ብሄር ፓርቲዎች አብረው መስራታቸውስ በትብብሩ ላይ እንቅፋት አይፈጥርም ወይ በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የትብብሩ ሰብሳቢ ኢ/ር ይልቃል፤ “እስከዛሬ በታየው የትብብሮች አለመሳካት የተነሳ በእኛም ትብብር ላይ እንደ ዜጋ ጥርጣሬ ቢያድርባችሁ ተገቢ ነው” ካሉ በኋላ፣ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች በዳሰሳ ጥናቱ ችግሮቹን ለመለየት ባደረጉት ሙከራ ለትብብሩ አለመሳካት እንደችግር ከተነሱት ውስጥ ፓርቲዎች የውስጥ ችግሮቻቸውን መፈተሽ አለመቻል፣ በመከባበር ሽፋን ችግሮችን አለባብሶ ማለፍና ሌሎችም በመገኘታቸው እነዚህን ጉዳዮች በድፍረት ተነጋግረው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
 “የእኛ ትብብር ረጅም ርቀት እንዲጓዝ የሚያስችለውን በጠራ ሃሳብ ላይ የመቆም ሁኔታ በዋና መሰረትነት አስቀምጠናል” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ እስከዛሬ እንቅፋት ሆነው ትብብርን ሲያደናቅፉ የነበሩ የፓርቲና የግለሰብ አይነኬዎች፣ የአሸናፊና ተሸናፊ አይነት ሂደቶችና በውስጥ ችግራችን ምክንያት ለውጭ ተፅዕኖ የምንጋለጥባቸውን አሰራሮች ከእንግዲህ ተሸክመን ላለመቀጠል በግልፅ ስለተነጋገርን ትብብራችን እክል ይገጥመዋል ብለን አናስብም ብለዋል፡፡ የብሄር ተኮር እና ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች በጋራ መስራታቸውን በተመለከተም ሁለቱም አይነት ፓርቲዎች የሚጮሁት ለነፃነትና ለእኩልነት በመሆኑ አብሮ መስራታቸው ችግር እንደሌለው የትብብሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ ተናግረዋል፡፡
ትብብሩን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰብሳቢ፣ አቶ ግርማ በቀለ ም/ሰብሳቢ፣ አቶ ኤርጫፎ አርዴሎ ፀሐፊ፣ አቶ ካሳሁን አበበ ም/ፀሐፊ እንዲሁም አቶ ኑሪ ሙደሲር የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው መመረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም ወደ ትብብሩ በመምጣት በአገራቸው ጉዳይ ላይ አብረው እንዲሰሩ የትብብሩ ኃላፊዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡


Read 2833 times