Saturday, 25 October 2014 10:12

የኢምሬትስ አየር መንገድ ትኩረቱን አፍሪካ ላይ አድርጓል

Written by  ማህሌት ሰለሞን
Rate this item
(1 Vote)

የኢምሬትስ አየር መንገድ በቀጣይ አስር ዓመት ውስጥ ትኩረቱን በአፍሪካ ላይ በማድረግ የገቢ ድርሻውን በ40 በመቶ እንደሚያሳድግ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በዱባይ በተካሄደው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ ፎረም ላይ የኢምሬትስ አየር መንገድ ፕሬዚዳንት ቲም ክላርክ፤ አፍሪካ ለኢምሬትስ ትልቅ የዕድገት ምንጭ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኢምሬትስ በአፍሪካ የ7 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንዳለው ገልጸው በቀጣይ አመታት ውስጥም ተጨማሪ 10 መዳረሻዎችን በመጨመር አህጉሪቱ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከአውስትራሊያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ፣ ዱባይንም እንደማዕከል በመጠቀም አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር ለማገናኘት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
የአየር መንገዱ መረጃ እንደሚያመለከተው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት አየር መንገዱ 1.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ተሳፋሪዎችንና 40 ሺህ ቶን እቃዎችን በአፍሪካና በቻይና መካከል አመላልሷል፡፡ እስከ 2020 ዓ.ም ተጨማሪ 8.5 ሚሊየን መቀመጫዎችን ለአፍሪካ እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡
ከ5 መቶ ሺህ በላይ አፍሪካውያን በዱባይ እንደሚኖሩና በ2013 ከ8 መቶ ሺህ በላይ አፍሪካውያን ዱባይን እንደጎበኙ የተገለጸ ሲሆን በ2020 ዓ.ም 1.5 ሚሊዮን የሚደርሱ አፍሪካውያን ዱባይን እንደሚጎበኙ ተገምቷል፡፡

Read 1640 times