Saturday, 25 October 2014 10:07

በጓደኛዋ የፈላ ዘይት የተደፋባት ወጣት ህይወቷ አለፈ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

በድሬደዋ ገንደቆሬ አካባቢ ነዋሪ የነበረችው ወጣት ነፃነት መታፈሪያ፤ በጓደኛዋ በተደፋባት የፈላ ዘይት ህይወቷ አለፈ፡፡ ወጣቷ ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል ሪፈር ተደርጋ ለጥቂት ቀናት ህክምና ብትከታተልም ህይወቷን ማትረፍ አልተቻለም፡፡ በጓደኛዋ ላይ የፈላ ዘይት ደፍታለች ተብላ የተጠረጠረችው ወጣት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላለች፡፡ ሟች ነፃነት መታፈሪያ፤ ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ በዲግሪ በተመረቀች በሶስተኛው ቀን ነበር ከጓደኛዋ ጋር ስትጫወት ለማደር ከምትኖርበት ገንደቆሬ አካባቢ ሳቢያን ወዳለው የጓደኛዋ ቤት ያመራችው፡፡ምሽቱን በሳቅና በጨዋታ ያሳለፉት ሁለቱ የረዥም ዓመት ጓደኛሞች፤ ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ሲሆን ወደ መኝታቸው ያመራሉ፡፡ የቤቱ ባለቤት እንግዳ ጓደኛዋን ካስተኛች በኋላ መጣሁ ብላ ወደጓዳ ትመለሳለች፡፡ አንዳችም ክፉ ነገር ያልጠረጠረችው እንግዳ፤ ጋደም ብላ ጓደኛዋን እየጠበቀች ነበር - ጨዋታቸውን ለመቀጠል፡፡ ጓደኛዋ ግን ያሰበችውን ለመፈፀም ተዘጋጅታለች፡፡ እሳት ላይ ተጥዶ ሲፍለቀለቅ የቆየውን የፈላ ዘይት ይዛ ጓደኛዋ ወደተኛችበት አልጋ በመሄድ በሰውነቷ ላይ ገለበጠችባት፡፡ የዘይቱ ቃጠሎ አጥንቷ ድረስ ዘልቆ ያንገበገባት ተጐጂዋ፤ እሪታዋን አቀለጠችው፡፡ ወዲያው ጐረቤቶች ደርሰው ገላዋ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ በማፍሰስ ቃጠሎውን ሊያበርዱላት ሞከሩ፡፡ ሆኖም ስቃይዋን ሊያስታግሱላት አልቻሉም፡፡ ይኸኔ ነው ሌላ  ክፍል ተኝቶ የነበረው የተጠርጣሪዋ ባለቤት ወጣቷን በመኪናው ጭኖ ወደ ድል ጮራ ሆስፒታል የከነፈው፡፡ የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች የመጀመርያ ደረጃ የህክምና እርዳታ ካደረጉላት በኋላ ጉዳቷ ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልገው መሆኑን በማረጋገጣቸው አዲስ አበባ ወደሚገኘው የካቲት 12 ሆስፒታል ሪፈር አደረጓት፡፡ በወጣቷ ላይ የደረሰው ዘግናኝ አደጋ ክፉኛ ያስደነገጣቸው የወጣቷ ቤተሰቦች፤ ነፃነትን ይዘው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ ለጥቂት ቀናት በየካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላት ብትቆይም ለውጥ ባለማግኘቷ ቤተሰቦቿ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ወሰዷት፡፡ ተጨማሪ ህክምና ለማግኘት ግን አልታደለችም፡፡ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ኮሪያ ሆስፒታል እንደደረሰች ህይወቷ አለፈ፡፡ ፖሊስ በሟች ሰውነት ላይ የፈላ ዘይት በማፍሰስ ለህልፈት የሚያደርስ ጉዳት ፈፅማለች ባላት ተጠርጣሪ ወጣት ላይ  ምርመራ እያካሄደና መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን የድሬደዋ መስተዳድር ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ፣ ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡    

Read 4862 times