Saturday, 25 October 2014 10:01

በጋምቤላው ግጭት የተሳተፉ ባለስልጣናትን ለህግ ለማቅረብ እየተጣራ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአሁን ወቅት ሰላም ሰፍኗል ተብሏል በቴፒ ከተማ በተደረገው ውይይት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ተገኝተዋል

     በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሳምንታት ግጭት ተቀስቅሶባቸው በነበሩ አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት ሰላም ሰፍኗል የተባለ ሲሆን በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባሉ አመራሮችንና ሌሎች አካላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ወንጀለኛን የመለየት ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ ሰሞኑን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በተገኙበት ግጭቱ በተፈጠረባቸው የደቡብ ክልልና የጋምቤላ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች አመራሮችና ሌሎች የየክልሎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት የ3 ቀናት ውይይት በቴፒ ከተማ አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የጋምቤላ ክልል የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳይመን ቱርያል ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደው ውይይት በግጭቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ግጭቱ ተቀስቅሶባቸው የነበሩት የጎደሬ ወረዳና አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በአሁን ሰዓት መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ባለስልጣኑ፤ በአካባቢው ሰላም መስፈኑንም ተናግረዋል፡፡
የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎም ህብረተሰቡ ወደ ቀዬው ተመልሶ ሰላማዊ ኑሮውን እየመራ ነው የተባለ ሲሆን ት/ቤቶችም መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸውን መቀጠላቸውም ታውቋል፡፡
በግጭቱ የጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው ንብረት በመጣራት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በግጭቱ ተሳታፊ መሆናቸው በተረጋገጠባቸው አካላት ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡
በአካባቢው ለሁለት ሳምንት በዘለቀው ግጭት የውጭ ሃይሎች ተሳታፊ ሳይሆኑ እንዳልቀረም በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አመት ዋዜማ ከተቀሰቀሰውና በጎደሬ ወረዳ መዘንገር ዞን ከተፈጠረው ግጭት በተጨማሪ በዚሁ ወረዳ ቴፒ አካባቢ በቅርቡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች መንገድ ላይ አድፍጠው በመጠበቅ ከአስር በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ገድለዋል፡፡

Read 3088 times