Monday, 20 October 2014 08:37

ምድጃ ዳር፥ ለገላ ነዉ ለትዝታ?

Written by  -አብደላ ዕዝራ
Rate this item
(2 votes)

ከኤፍሬም ሥዩም ዉርስ ትርጉም
የግዕዝ ጉባኤ ቅኔን እንደ ማንበብ

‘ተዋናይ’ በጐጃም የነበረ ፈላስፋ፣ ታላቅ ሊቅ፣ ቅኔን የፈጠረ ባህረ ምስጢሩን ዋኝቶ የመረመረ መሆኑን ተነግሮለታል:: ስሙ ለመጽሐፍ ርዕስ መሾሙ አግባብ ነዉ። ተዋነይ (ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና) 83 ግጥሞች ከግዕዝ ወደ አማርኛ ዳግም የተተቀኘባቸዉ፥ ዘመነኛ ተደራሲያን እንደገና ከግዕዝ ስንቅ ለመቋደስና በእሳቦቱም ለመደመም የፈቀደ ድንቅ መጽሐፍ ነዉ። ኤፍሬም ሥዩም ለስድስት አመት ያክል የግሉን ፈጠራ እየተቀኘ በተጨማሪም ከግዕዝ የሚተረጉመዉን ለመምረጥ ብዙ ዳክሯል፤ በዉርስ ትርጉም ግዕዙን በአማርኛ ዳግም ለማንጠር አልሰሰተም። ሻማ ቡክስም በሚመጥነዉ ጥራትና ዉበት አሳትሞ ለሀገር ቅርስ አብቅቶታል። ዛሬ በየስርቻዉ በተራ ወረቀት በድብቅ ሌላዉ አሳትሞት ሲነግድበት ለሱ ወይም ለነሱ ሳሙና ሰርቆ እንደ መቸርቸር ርካሽነት ቢመስልም፥ ለባለቅኔዉ ሆነ ለኢትዮጵያ ሥነጽሁፍ ለሚስገበገብ ይሰቀጥጣል፤ ይጐዳል፤ ወንጀልም ክህደትም ነዉ። “ጥበብ ለምን አንገቱን ይድፋ?”ብሎ ለመጠየቅ ብቻዬን ሰልፍ መዉጣት ባልችልም፥ ቢያንስ ቢያንስ ኤፍሬም ሥዩምን <ሀቅህ ያብጠረጥራል> ለማለት አንድ የግዕዝ ጉባኤ ቃናን ለማንበብ ደፍሬያለሁ። ይህ መጽሐፍ በሚመጥነዉ ኮስታራ ግምገማ ለመደመም የግድ ግዕዝን እንደ ቋንቋ መቻልን፥ ግጥሞቹ የተፍታቱበትም የተወሳሰቡበትም ዳራና ዐዉድ ማጤንን ይሻል። ጉባኤ ዘርግተዉ ቅኔና ትርጓሜ መጻሕፍትን ሲያስተምሩ ግዕዝ በአመዛኙ ሃይማኖታዊ ለሆነ ጉዳይ አድሯል። ቢሆንም አልፎ አልፎ የእለት ህይወትን፥ ለኑሮ መብሰልሰልን፥ ፈጣሪ መሞገትን፥ በሄዋን ገላ መጐምጀትን ... ከመሰለ ሰመመን መቅዘፉ መች ቀረ ? ከ83 ግጥሞች አንዱን ያዉም በአማርኛ መንቶ፥ በግዕዝ ጉባኤ ቃና የተባለዉን ባለ ሁለት ስንኝ ደፍርኩ እንጂ የተቀሩት ሰማንያ ሁለቱ ያመቁትን፥ እዉስጣቸዉ ያደባዉን ለማባበል አቅም ይጠይቃል።

ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ
አኮኑ ትዉዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ

 [ከተዋነይገፅ 152 (65ኛዉ ግጥም)የተወሰደ።]
መምህር ይኄይስ ወርቄ <ንባብ ወትርጓሜ ዘቅኔያት- አዕማደ ምሥጢራት>በሚል መጽሐፋቸዉ ገፅ 29 ቃል በቃል ተርጉመዉታል። የተቀኙትም ዘዋሽራ ተክሌ መሆናቸዉን ይገልጣሉ።
ድንግል ልጃገረድ ባልቴትን ትመስለናለች፤
እሳትን አቅፋ ትዉላለችና
በዕድሜ መፍካትና መክሰም ጠቢባን ሲብሰለሰሉበት ከተባዕት ይልቅ ለእንስት ገላና ዉበት ይነዝራሉ። እንዳለጌታ ከበደ በ’ዛጐል’ ልቦለዱ እንደ መለመላት አብይ ገፀባህርይ እሌኒ የመሰለች። ‘ወንድ . . . መቋጫዉ የረዘመ አረፍተ ነገር ነዉ:: ራሱን የሚያሰለች፣ የሚጠና:: ሴት ግን ትወሳሰብ ይሆናል፣ ቅኔ ትሆን ይሆናል፣ ... ቁጥብነቷ ይማርካል፣ ... ምን እንደሆነ የማይታወቅ ስሜት መጫር የምትችል!’ እስከ ማለት የበቃች ናት:: መምህር ዘዋሽራ ተክሌ ለመፈላሰፍ የሄዋንን ገላና እድሜ መቀንበባቸዉ አይደንቅም፤ እራሱ ኤፍሬም ሥዩም በዚህም ይደመማል። ‘ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር’ገፅ 34
የበአሉ ለታ
ሲበተን ያየነዉ አረንጓዴዉ ሁሉ
በበአሉ ማግስት
ሲጠረግ ያየነዉ ግራጫዉ ሳር ሁሉ
ያንቺን ወጣትነት ይወክላል አሉ።
ከድንግል ልጃገረድ እስከ ባልቴት የተዘረጋዉ ሆነ የተጠቀለለዉን እድሜ ዉስጣዊ ፍምና የምድጃ ዳር ትካዜን በሁለት ስንኝ የግዕዙ ቅኔ ሲቋጥረዉ ይፈትናል። ይህ እምቅና አሻሚ ግጥም ነዉ። [ambiguity አሻሚነት ይላል ብርሃኑ ገበየሁ “ከአንድ ፍቺ በላይ ትርጓሜ መያዝ፥ ከግጥሙ ዐዉደ ንባብ በመነሳት ቁርጥ ያለ ትርጓሜ ለመስጠት አለመቻል። ‘የአማርኛ ሥነግጥም ገፅ 411’] “አሞኛል ስላቸዉ በሽታዬን አጡት/ የላጡት ይደርቃል እንኳን የቆረጡት” የመሰለ ቃል-ግጥም ደግሞ አሻሚነትን ይበልጥ ያስረዳ ይሆናል። ኤፍሬም የግዕዙን ግጥም በአማርኛ ሲወርሰዉ ይህን አሻሚነቱን ሳይፍቅ ሳያደበዝዝ ጠብቆታል።
የዐሥራ አምስት ዓመቷ
ያቺ ልጅ እግር ድንግል፥
ዘመኗ የሄደ
ዕድሜዋ የገፋን ባልቴት ትመስላለች
ምክንያቱም ...
እሳት በጉያዋ
ታቅፋ መኖርን ወዳለች። [ተዋነይ፥ ገፅ 153]

ልጃገረድና ባልቴት፥ ለአቅመ ሄዋን የደረሰች እና ያረጀች ያፈጀች አሮጊት ሁለቱም የሚያቅፉት እሳት ለየቅል ነዉ።  በእድሜ ጠና ያሉት ከኑሮ ልምድና ተመክሮ የሰበሰቡት ማለፊያቸዉ ላይ ይበጃቸዉ ይሆን? ሎሬት ፀጋዬ በአፍላ ዕድሜዉ ስለ አንዲት አዛዉንት ያጤነዉ ያስደምማል። “ባንተያይ ባንወያይ፥ እቴቴ ዱብራ ኦሮሞ/ እንደልጅነት ሰመመን፥ ለካስ ዕድሜም ያማል ከርሞ።” ዘዋሽራ ተክሌ ዛሬ ፈክቶ ስለሚፋጅ ግን ከርሞ ስለሚያም ዕድሜ ነዉ የተቀኙት? ዓለማየሁ ገላጋይ በ’ኩርቢት’ ስብስቡ የቀረፃቸዉ ወደ እርጅና ጉዞ የጀመሩት ‘የቦኖ እናት’ ይታወሳሉ። “-ኧረ እኔስ ጨነቀኝ- አሉ የቦኖ እናት አፋቸዉን በአዳፋ ጨርቅ ሸፍነዉ። እታለማሁ መሀን በመሆናቸዉና ለሰፈርተኛዉ የቦኖ ዉኃ በማስቀዳታቸዉ ነው ‘የቦኖ እናት’ የሚል ቅጥል ስም የወጣላቸዉ። እታለማሁ በቅጽል ስማቸዉ አይከፉም። እንደዉም አንዳንዴ -እኔ የቦኖ እናት- እያሉ በራሳቸዉ ያሾፋሉ። ”የማኅበረሰቡ ሽኩሹክታ ገድበዉ ለመኖር ያልታከቱት ወደፊት ያለጧሪ ምድጃ ዳር ሲቆዝሙ ሊያሳስብ ይችላል። ልጃገረዷ እዉስጧ ፍትወታዊ ፍም ታቅፋ መፈልቀቅን ስታልም ባልቴትም መደበት ብቻ ሳይሆን በትዝታም እንደ መጋል እንደ መሎከስም ይዳዳቸዋል። “ትዝታ (ወደ ኋላ መፍሰስ) ትላንትን ዛሬ ላይ ከመመኘት የሚመጣ ነገር ነዉ። ዛሬ ላይ አብረዉን ያሉትን ሰዎች ወደ ኋላ አናስባቸዉም። ትናንት የተዉንን (የተዉናቸዉን) ሰዎች ግን ዛሬ ላይ ልናስባቸዉና ልንመኛቸዉ...ወደ ኋላ እንፈሳለን ከወንዙ ወደ ምንጩ”  ብሏል ኤፍሬም ሥዩም። [ፍቅር እዚህ ...] ለዚህም ነዉ ዘዋሽራ “አኮኑ ትዉዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ” ሲሉ አሻሚነቱ፤ እንደ መቆዘምም፥ በአለፈዉም ትዝታን ጐንጉኖ እንደ መፍካትም የተወሳሰበዉ። አዳም ረታ ‘በር’ በሚለዉ ትረካዉ የመለመላቸዉ ባልቴት የዕድሜ ቅዝቃዜ ብቻ ሳይሆን በትዝታም ግለት መሞቅና መቆጨትን ቋጥረዋል።
“ከሰዉ ሰዉ ደሞ ትዝ የሚላቸዉ፥ ኩታዉን እያመቻቸ መቶክቶክ የሚወደዉ ያ ብስል ቀይ፥ ነፍሱን ይማረዉና ነጭ ለባሽ ሆኖ ዉጋዴን ወድቆ የቀረዉ የአልጣሽ ልጅ፥ የሰፈር ወሬ ሲያቀብላቸዉ ነዉ። ከትዳራቸዉ ዉጭ የወደዱት ወንድ እሱ ብቻ ነበር። ግን ምንም አላደረጉም። ዛሬ ከሚቆጫቸዉ አንዱ የባቱን ጥንካሬ፥ ቁመቱንና አጨዋወቱን ያስታዉሱና ‘ቢሆን ኖሮ ማን ይጐዳ ነበር?’ ለራሳቸዉ ይላሉ። ለራሳቸዉ ይስቃሉ።” [ይወስዳል መንገድ ... ገፅ 228]
ከትዳር ቀለበት ሾልከዉ ሌላዉንም በወሲብ መቅመስ ሳይደፍሩ የቀሩት፥ በስተርጅና ለመቆጨትም በትዝታም ለመፍለቅለቅ እንደ ስንቅ ነዉ፤ ዕድሜ መች መክሰም ብቻ ሆነ? ዘዋሽራ ተክሌ ከነገረ መለኮት ሱባኤ ስሜታቸዉን ጐትተዉ ግራ ቀኝ ገላምጠዉ ድንግል ልጃገረድ ያቀፈችዉ እሳት እንዴት አባበላቸዉ? እንዴት ለመቀኘት እርሾ ሆናቸዉ? ቢያሰኝም በሄዋን ዉበት እና እጣ ፈንታ መመሰጥ ለባለቅኔ አንድ የህይወት ሰበዝ ነዉ። ጠና ያለ ምሁር ለአቅመ አዳም ባልደረሰች አጐጥጐጤ በፍትወት ፍላጐት ሲቅበዘበዝ እና ጣጣ ዉስጥ ሲወራጭ ዕዉቁ ደራሲ Nabokov በአብይ ልቦለድ አወሳስቦታል። Lolita በታተመ ወቅት ባህላዊና ሥነፅሁፋዊ ሽብር ለቆ ነበር። ዘዋሽራ የተቀኘላት ልጃገረድ የታቀፈችዉን እሳት ከሰብለወንጌል ጀምሮ በአያሌ ልቦለድ ተቀርፃለች፤ እንደ አዳም ረታ ግን በዝርግ ግጥም እስኪያደናግዝ ድረስ የተቀኘላት የለም። እንድያዉም የታቀፈችዉ ስሜታዊ እሳት ሲጥምም ሲጐመዝዝም የተተረከበት ‘የመጨረሻዋ የቀበሌ 01 ድንግል’ ልቦለድ አለዉ። ግን ‘ወተት’ የሚለዉ ትረካዉ ይበልጠ ዘዋሽራ “አኮኑ ትዉዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ” ላሉት ይመጥነዋል።
“እሁድ ከሰዓት በኋላ ነዉ፤ ጓደኛዬ ዳንኤል ቤት ስደርስ እህቱ የትምወርቅ ቧንቧ ስር ፀጉሯን ስትታጠብ አገኘሁዋት። ጡቶቿንም ። ከዚያንም ዕለት ጀምሮ ደህና እንቅልፍ አልወሰደኝም። ... ከቤት ስትወጣ ... አንድ ቄስ አቁመዉ ደረቷን ባረኩት።
‘ምን ብለዉ ባረኩሽ’ ስላት
‘እ እ እ’ ትላለች
‘እንዳይፈነዳ እሱዉ ይጠብቅልን?’
ጐኔን ቆነጠጠችኝ። እንደ ከረሜላ የሚጣፍጥ። መፈንዳቱ ይቀራል?... እጄን ትከሻዋ ላይ ጣል አደረክኩ ... በአንገቷ በኩል ወደታች አየሁ። የጡቶቿ መካፈያ(ሀ)ይመስላል፤ መልካም የተወለወለ ሀ ግዕዝ። ወይም የሚበር አሞራ። [ይወስዳል መንገድ ... ገፅ 210/218]
እንዲህ ከልጃገረድ አካል ከመሸገ ዉበት እንዲሁም ከባልቴት ባዶነት ሆነ ትዝታ ከተደበቀ ፍም ተላቀን ቅኔዉ ያጓተዉን የጊዜን ጥያቄ ብንነካካዉ በሰፊዉ ሊያወያይ ይችላል። ጊዜ እነ እትዬ አልታዬን “... በስዉር እጁ ይዞ በጭካኔ ሳይሆን እየሳቀ በዝግታ እንደ ወረቀት ጭርምትምት ...” ሲያደርጋቸዉ ስብሀት ተርኳል። እንደ አሜሪካዊ ደራሲ Faulkner አባባል፤ ጠቅላላ ችግሮቻችንን ማሸነፍ ብንችል ጊዜ ብቸኛዉ ችግራችን ሆኖ ይቀራል። የልጃገረዷ የየዋህነት ጊዜ፥ ባልቴቷም ላይ የተከማቸዉ ወቅት ለዘዋሽራ ተክሌ ሁለት አይነት እሳት -ብርሃንም ጨለማም- ይሆናል። የወጣት ገጣሚ ትዕግሥት ወራሽ ጥያቄ ያሳስበኛል።
ለምን ነበር?
መንጋትህ ላይቀር
ጨልመህ የነገስከዉ
መቅለልህ ላይቀር
እንደዚያ የከበድከዉ
ለምን ነበር ሌቱ
ቀንን የፈተንከዉ? [ነጭ ልብ  ከሚለዉ የግጥሞቿ ስብስብ የተወሰደ]
ጊዜ ጊዜን ሲፈትነዉ በቀንና ሌሊት ተምሳሌነት ገጣሚዋ መቅለሉንም መክበዱንም ስትጠይቅበት ዘዋሽራ ተክሌ ከልጃገረድ እስክ ባልቴት የተዘረጋዉን እድሜ ነዉ የተደመሙበት። Yevgeny ‘the Sole Survivor’ በሚለዉ መጽሐፉ “A poet’s autobiography is his poetry. Anything else is just a footnote” ያለዉ ያጠራጥራል። “የአንድ ባለቅኔ ግለህይወት፥ ታሪኩ ግጥሞቹ ናቸዉ፤ ሌላዉ ሌላዉማ የግርጌ ማስታወሻዉ ነዉ ”በግዕዝ የተቀኙት ግለታሪካቸዉ ከቤት ክህነት የተዋሀደ ቢሆንም እንደ ሰዉ የግርጌ ማስታወሻ አላቸዉ -የተሸሸገ። ይህን ለማግኘት መዳከር ኤፍሬም ሥዩም ቢሳካለትም የሐያሲያን ዝምታ ይገድበዋል። አንድ ባለ ሁለት ስንኝ ግጥሙ እንዲህ ከረቀቀብን ከ[ተዋነይ] መጽሐፉ የሚነዝሩት ሌሎች 82 ግጥሞች በምስጢራቸዉ ይማጠኑናል።
ጭራሽ በተራ ወረቀት እና ጥራት በሌለዉ ህትመት መጽሐፉ መዘረፉ፥ በድብቅ መታተሙ በዝምታ የሚታለፍ ከሆነ ያንሰራራዉን የአማርኛ ጥበበ ቃላት እጅጉን ይጐደዋል፤ ሥነፅሁፍ ግን የዉሸት ወንዝ አይንደዉም።

Read 2535 times