Monday, 20 October 2014 08:34

የአዳም ረታ “ሕጽናዊነት” ምንድን ነው?

Written by  ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(2 votes)

መግቢያ
ከጥቂት ጊዜያት በፊት ፌስቡክላይ በሚገኝ የአዳም ረታ አድናቂዎች ቡድን ውስጥ አንድ ሰነድ አገኘሁ፡፡ ይሄ ከሀያ ገፆች በላይ ያለው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ አዳም በተለያየ ጊዜ በአንባቢዎቹ ለተጠየቃቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጠበት መድበል ነው፡፡ ፋይሉን አንብቤ እንደጨረስኩ ይሄንን ጽሑፍ ማግኘት ላልቻሉ ሰዎች ባጋራ ማንንም እንደማይጎዳ ስላመንኩበት ነው ይሄንን ጥሑፍ ማዘጋጀቴ፡፡ ዋናው ዓላማዬ ግን ሕጽናዊነት ምንድን ነው የሚለውን ትልቅ ጥያቄ በአጭሩ ለመመለስ ያደረግሁት ደፋር ሙከራ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ የአዳምን ጽሑፍ በረጃጅሙ ወስጃለሁ፡፡ አዳም በመጻሕፍቱ ውስጥ ካስቀመጠልን ማብራሪያዎች ላይም ቀነጫጭቤያለሁ፡፡ በአጭሩ ለጋዜጣ ፅሑፍነት እንዲስማማ ማመቻቸት ስለ ነበረብኝ አንዳንድ ቦታ ላይ ብቻ ማያያዣ የሚሆኑ አረፍተ ነገሮችን፤ አንቀፆችንና ምሳሌዎችን ከማስቀመጤ በስተቀር ቀሪው የራሱ የአዳም ቃል ነው፡፡
 አዳም እና እንጀራ
እንጀራ ለአዳም የጽሑፉን ቅርፅ የሚቀዳበት ሞዴል ብቻ አይደለም፡፡ “It is more than a model. It is a metaphor” ይላል በራሱ ቃል፡፡ “ከሞዴልነት በላይ ነው፡፡ እንጀራ ተለዋጭ ዘይቤ ነው፡፡ እንጀራ ክብ ነው፡፡ ባለ ሦስት ዲሜንሽን ነው፤ ግን ደግሞ ጠፍጣፋ፡፡ ቀዳዳዎች አሉት ግን ደግሞ ልሙጥ ነው፡፡ በጠጣር እና ጠጣር ባልሆነ ቁስ መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የእንጀራው ቀዳዳዎች (ዐይኖቹ ማለቴ ነው) ራሳቸውን ችለው የቆሙ ይመስላሉ፤ ሆኖም ውስጥ ውስጡን ውስብስብና ረቂቅ በሆኑ ቱቦዎች የተያያዙ ናቸው፡፡ በተቃርኖዎች የተሞላ መዋቅር ኖሮትም እንኳ እነኚሁ ተቃርኖዎቹ ‘ቀጥ ብሎ እንዲቆም’ የሚያስችሉት አላባውያኑ ሆነው ይሠራሉ” (It has a contrasting structure signified by opposites and yet all contributing to its whole physical ‘survival’).
ሕይወት ራሷ ከተቃርኖዎች ውህድ የተገመደች ነች፡፡ በዚህም እንጀራ ከሕይወት/ህልውና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለመጠቆም አዳም የምሳሌያዊ ንግግሮቻችንን እንደ ማስረጃ ያነሳል፡፡
እንጀራውን ጋገረ፤ እንጀራ ፈላጊ፤ የእንጀራ ገመዱ ተበጠሰ፤ እንጀራ በሬው፤ እንጀራውን ያበስላል ወዘተ፡፡ ህላዌ ቅጥ አልባና የተሰደረ ሁለቱንም ነው፤ ወይም የተሰደረ ቅጥ አልባነት፡፡ (Ordered chaos እንደማለት) አንዱ ከአንዱ የተያያዘ… እንጀራ ይህንን የህላዌን ተቃርኗዊ ግንኙነቶች የሚገልፅ ምሳሌ ነው፡፡ እኔም ይሄንን ዘይቤ ወደ አጻጻፍ ስልትነት ብለጥጠው ብዙም ከዕውነታው አልራራቅም፡፡ “Existence is both chaotic and ordered; or ordered chaos. Interconnected……Injera is used as a metaphor for describing or illustrating existence. And it is not far from the truth if I stretch this metaphor into a writing technique” ይላል አዳም፡፡
እንጀራዊ/ እንጆሪያዊ ቅርፅ
ከሕጽናዊነት በፊት እንጀራዊ/እንጆሪያዊ ቅርፅ ነበር፡፡ ሆኖም የቃላት መለዋወጥ እንጂ ጠለቅ ያለ የትርጉም ልዩነት አይታይም፡፡ ምናልባት እንጀራዊ ቅርፅ የሕጽናዊነት እርሾ ወይም ሕጽናዊነት የእንጀራዊ/እንጆሪያዊ ቅርፅ እጅግ የተጠና፤ የላቀና ምልዑ በኩልዔ የሆነ ‘ቨርሽኑ’ ነው፡፡ በ”ግራጫ ቃጭሎች” መግቢያ ላይ እንጆሪያዊ ቅርፅ እንዲህ ተብራርቷል፡ “የዚህን መጽሐፍ የአጻጻፍ ቅርፁን የተዋስኩት ከእንጀራ ቅርፅ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ምዕራፎች ከእንጆሪው ጠቃጠቆ/ንዑስ ፍሬዎች ጋር ወይም ከእንጀራው ዐይኖች ጋር እንዲማሰሉ ሆኖ ነው የቀረበው (አንድ ዐይን ወይም ጠቃጠቆ አንድ ምዕራፍ) … ታዲያ በአሰያየም ውሰት ከእንጆሪ ወደ እንጀራ ከመጣን ለምን ከእንጀራ ወደ እንጆሪ አንሄድም? ከዚያ ወደዚህ የወሰደን መንገድ አይመልሰንም ማን አለ? ወደ መነሻው ሄድኩና ለዚህ ልብ ወለድ ቅርፅ እንጆሪ የተሰኘ ስያሜ ሰጠሁት ወይም መረጥኩ”፡፡
የእንጆሪ ቅርፅ ለሕጽናዊነት እንደ ጥንስስ ቢሆንም  ስሙን ይዞ መቆየት አይችልም (“የእንጀራ ቅርፅ” ካልተባለ በስተቀር)፡፡
አዳም በቅርቡ “መረቅ” የተሰኘው መጽሐፉ በሃገር ፍቅር ቴያትር ቤት ሲመረቅ፣ ከታዳሚያኑ መካከል በአንደኛው በቀረበለት አስተያየት መሠረት፤ እንጆሪ የሚለውን ቃል ምንም ዓይነት የቲዮሪ መፋለስ ስለማያስከትል ማውጣት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡ (ይህ አስተያየት ሰጪ እንዳለው የእንጀራ ዓይኖች (ሰው ሠራሽ በመሆናቸው) አንዱ ከሌላው ያለው ርቀት ዘፈቃዳዊ ነው፤ የእንጆሪው ጠቃጠቆዎች ግን (ተፈጥሯዊ በመሆኑ) በስሌት ሊቀመጥ የሚችል ቅጥ አላቸው)፡፡
ከእንጀራ/እንጆሪያዊነት ወደ ሕጽናዊነት
አዳም ከእንጀራ/እንጆሪያዊ ቅርጽ ወደ ሕጽናዊነት ለመሸጋገር ወደ ትናንት ርቆ ይጓዛል፤ በንባቡና በማሰላሰሉ፡፡ “የድሮ ሰዎች እንደኛ ርቱእ (literal) አይደሉም፡፡ ከፊደል ገበታቸው እስከሚበሉት ነገር ብታይ የሆነ ዓይነት ለመፈታት የሚጠብቅ ሚስጥር አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ግንዛቤ ላይ ለመድረስ በሆነ ዓይነት ስነ-ውበታዊ ልምድ (aesthetic experience በሚባለው) ውስጥ አለፍኩኝ፤ ከዚያ ጊዜ በኋላ የዚያን ጠፍጣፋ ዳቦ ትርጓሜ ሳሰላስል ቆይቻለሁ”፡፡
የእንጀራን ዘፍጥረት ፀሐይ ትመለክበት ከነበረው ዘመን እንደሚነሳ ይናገራል አዳም፡፡ “እንጀራ የሚገርም ቅርፅ አለው፡፡ ዘፍጥረቱም ፀሐይ ትመለክበት ከነበረው ዘመን ይነሳል፡፡ በዚያን ዘመን ፀሐይ በክብ ምልክት ትወከል ነበር፡፡ የኛ ፊደል ፀሐዩ ‘ፀ’ የፀሐይ ወኪል ነው፡፡ ዐይኑ ‘ዐ’ም  የተባለው ፀሐይ በሰማዩ ላይ ያለች ‘ዐይን’ በመሆኗ ነበር፡፡ የእንጀራን ጉድጓዶች ‘ዐይን’ ማለታችን ገጠመኝ አይመስለኝም”፡፡
“ክብ ከጥንት ጀምሮ የሕብረት፣ የአንድነትና የዘላለማዊነት ምሳሌ ነው፡፡ መካከሉ ላይ አንድ ነጥብ ያለው ሰርከምፓንክ የሚባል ክብ ደግሞ አለ፡፡ ፀሐይን እና የፀሐይ አምላክ (ግብፅ ውስጥ “ራ” የሚባለውን) ይወክላል፡፡ (“እንጀራ” ውስጥ ያለችው “ራ” ከዚህ ጋር ግንኙነት ቢኖራትስ?) ክቡ እና ነጥቧ የወንዴና ሴቴ ኃይሎች መንፈሳዊ ውሕደት ትዕምርት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አለም አቀፋዊ ትርጓሜ ነው” (This is a universal/cosmic sensibility)፡፡   
ታዲያስ እንጀራ ስላለፈው ዘመን እንዲዘክር በዕቅድ የተወጠነ፣ የወደፊቱንስ የሚያመላክት ጽሑፍ/ሐውልት ነው ለማለት አንችልምን? (አዳም ረታ)፡፡
ስለ እንጀራ አመጣጥ ሚቶሎጂ ደግሞ እንዲህ ያትታል…
“በአንድ አምላክ መመለክ ከመጀመሩ በፊት የኖሩ ማኅበረሰቦች ለእያንዳንዱ ፍጡር እና ባሕርይ የሚያብራሩት ትረካዎች ነበሯቸው፡፡ ኃላፊነትን ሁሉ ጠቅልለው ለአንድ አምላክ ከመስጠታቸው በፊት በነበረው በዚያን ዘመን የፍጡራን እና የፍጡራኑ ግብር በጠቅላላው በሚቶችና በአፈታሪኮች የማብራራት ልማድ ነበራቸው፡፡ ከ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ጋር ባደረግሁት ቃለ ምልልስ የጤፍን አመጣጥ የሚያብራራ አፈታሪክ ነገር እንደማይጠፋ ተናግሬያለሁ፡፡ (ያኔ ማግኘት አልቻልኩም ነበር እንጂ)፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በለስ ቀንቶኝ ጤፍ እንዴት የኢትዮጵያዊያን ዋና ምግብ ሊሆን እንደቻለ የሚያብራራ አንድ ታሪክ አነበብኩ፡፡ አሁን የታሪኩን ዕውነተኛነት ጥያቄ ውስጥ አላስገባም፡፡ ሁሌም ቢሆን ሚቶችን ስናነብ የምናደርገው ስለ ዕውነተኛነታቸው መጨነቅ ሳይሆን ሚስጥራቸውን ፈልፍሎ ለማውጣት መጣር ነው፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች ከላይ ሲታዩ እርባና ቢስ የሚመስሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱባቸው ተረኮች እንዳሏቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ለምንድን ነው ቀበሮ ጭራ የበዛው ጅራት ያላት? ውሻ እንዴት ለማዳ ተደረገ?  ጨረቃ ለምን በየወሩ ትመጣለች? ሰው የተፈጠረው እንዴት ነው?
የጤፉ ጉዳይ ለየት የሚያደርገው የተወሰነ አመክንዮአዊ ድባብ አለው፡፡ የሆነ ሊታመን የሚችል ነገር፡፡
እንግዲህ ይሄ ታሪክ የተከሰተው ከክርስቶስ በፊት 1500 አካባቢ ነው፡፡ ክስተቱም በእውኑ ዓለም ከነበረ ሰው ጋር ተያያዥ ነው፡፡ ይሄውም ሰው ኢስዬል፣ አጋቦስ (የንግሥና ሥም) የሚባል ኢትዮጵያዊ ንጉስ ነው፡፡ (‘አፄ’ የሚለውን የማዕረግ ሥም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመ ንጉስ)፡፡ ሌላኛው ስሙ ሰንደቅ አላማ ይባላል (ብዙ ስሞች አሉት)፡፡ ሰንደቅ አላማ ዘንዶ ንጉስ ነበር፡፡ (ይህቺ የዘንዶ አፈታሪክ ዓለም አቀፋዊ ናት)፡፡ ከሕይወት ታሪኩ እንደምንረዳው፤ ይህ ሰው ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ‘ሳይንቲስትም’ ነበር፡፡ ዘመሚትን፣ በቅሎን፣ የሜዳ አህያን የመሳሰሉ እንስሳትን ተያያዥነት ያላቸውን ዝርያዎች በማዳቀል እሱ እንደፈጠራቸው ይነገራል፡፡ ሰንደቅ አላማ በተፈጥሮ ላይ ይመሰጥ ስለነበር፣ የራሱ የሆነ የአትክልት ቦታ እና የእንስሳት ማቆያ ነበረው፡፡ ረዥም ዕድሜ ለመኖር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለመፈልሰፍ ታድሎም ነበር፡፡ በዚህም ከ425 ዓመታት በላይ መኖር ችሏል፡፡ የሚበላውና የሚጠጣው ሁሉ ከሰው የተለየ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሚጠጣው ውሃ ከአለቶች መካከል ከሚፈልቅ ምንጭ ይቀዳል፤ ‘የሕይወት ውሃ’ ነበር የሚባለው፡፡ እያደር ወጣት የሚያደርግ ኃይል ያለው ድንጋይ ላይም ይተኛ ነበር፡፡
ሰንደቅ ዓላማ 425 ዓመታትን ከኖረ በኋላ ግን ሕይወት ሰለቸችውና መሞት ፈለገ፡፡ አንዲት ወጣት ልዣገረድ እንድትገድለውም አደረገ፡፡ አፄውን የገደለችው ይህች ወጣት ኋላ ላይ ንግሥት ማክዳ/ሳባ ሆነች፡፡ የቀደመ ስሟ ኢተያ/እትዬ/እቴጌ ነበር… ሳባ እንግዲህ ‘እቴጌ’ ተብሎ ለመጠራት የመጀመሪያዋ ንግሥት ነች፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ አላለቀም፡፡ እሱ ከሞተ በኋላ ሳባ ንግሥት ሆነች፡፡ በዘመነ መንግሥቷም ረሃብ በመላ አገሪቷ ተስፋፋ፡፡ የተራቡ ወገኖቿን መመገብ ያቃታት ሳባ፣ የሰንደቅ ዓላማ መቃብር ዘንድ ሄዳ አነባች፤ ፀሎት አደረሰችም፡፡
በሕልሟም እግዚአብሔር ቀርቦ በንጉሱ መቃብር ላይ ከሚበቅለው ሣር በሚገኘው ፍሬ ሕዝቧን እንድትመግብ ነገራት፡፡ እንደተነገረችው አደረገች፡፡ ያ የሣር ፍሬ ጤፍ ነበር፡፡ ‘ጤፍ’ ማለት ትርጉሙ ‘ጣፋጭ’ እና ‘የተትረፈረፈ ምርት’ ማለት ነው፡፡ ጤፍ ዝናዋ ገናን የሆነ ፍሬ ነበረች፤ ስለ እሷ በመስማት ብቻ ንጉስ ዳዊት የምወድስ ግጥም ጽፏል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ባዮሎጂስት የነበረ መሆኑ የጤፍ ግኝት የአጋጣሚ ነገር አይመስልም… ምናልባትም ንጉሱ ራሱ ይሆን ይሆናል መጀመሪያም ጤፍን ያገኘው፤ የማክዳ ተረት ነጋሪዎች ይሆናሉ የፀሎቷን፣ ሕዝብ የመመገቧንና የእግዜርን ነገር ያከሉበት፡፡ እንደው ነገሩ እንዲህ እንኳ ባይሆን፣ ጤፍ እንዲህ ባለ ንጉስ መቃብር ላይ መብቀሏ በራሱ እየሞተ ካለ የንጉሱ ገላ ረዥም ዕድሜ የመኖር ምስጢርን እየወረሰች ይመስልባታል”፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለች የተጀመረችው ጤፍ እንግዲህ ረዥም ዕድሜ መቆየት ብቻ ሳይሆን እንጀራ  በመሆን ዘላለማዊ ሆናለች፡፡ አዳምም እንጀራ ምግብ ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራ የአጻጻፍ ስልቴን የቀዳሁበት ሞዴል ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራ ዘይቤ ብቻ ሳይሆን እናት ዘይቤም (root metaphor) ነው ይላል፡፡
“እናት ዘይቤ ማለት…” ይላል አዳም “እናት ዘይቤ ማለት በአንድ ቋንቋ ወይም ባሕል ውስጥ በጥልቅ በመስረጉ ዘይቤ መሆኑ ከነጭራሹ ልብ እንኳ የማይባል ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከውስጡ ሌሎች ዘይቤዎች የሚወጡበት አንድ ዘይቤ ነው ሲሉ ይተረጉሙታል”፡፡ መቸስ እንጀራ ከዕለት ዕለት ተግተን የምናላምጠው ቋሚ ምግባችን እንደመሆኑ እንደ አዳም ቀንቶን “በሆነ ዓይነት ስነ-ውበታዊ ልምድ” ውስጥ ካላለፍን በቀር አንድም ጊዜ እንኳን አይደለም ሚስጥራዊ ዘይቤነቱ አመጣጡ እንኳን አስጨንቆን አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው እንጀራ እናት ዘይቤ (root metaphor) ነው የሚለው አዳም፡፡
አዳም ይቀጥላል… “የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ዝርዝር ጉዳዮቻችንን በዚህ የእንጀራ ዘይቤ ማብራራት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄን የምናደርግበት አንዱ መስክ ልቦለድ በመጻፍ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እየሠራሁበት ያለውን ይሄ ዓይነቱን አጻጻፍ ደግሞ ‘ሕጽናዊነት’ እለዋለሁ”፡፡
“ሕጽናዊነት”፡ የቃሉ አፈጣጠር/አመጣጥ
ሕጽናዊነት እና ዘይቤ ምን አገናኘው ብሎ የሚጠይቅ ይኖር ይሆናል፡፡ ‘ሕጽን’ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሁለት ፊደሎች መካከል ያለው ክፍተት ማለት ነው፡፡ ጽሑፍ ሊነበብ የሚችለው ይሄ ባዶ ቦታ በየፊደላቱ መካከል በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ በፊደል ገበታ ውስጥ ያሉት ክፍት ቦታዎች ደግሞ ማሕጸን ይሰኛሉ፡፡
ሁለቱም ቃላት የተወሰነ የትርጉም መመሳሰል አላቸው፡፡ እነኚህ ባዶ ቦታዎች ከእንጀራ ዐይን ጋር በይዘት መመሳሰል እንዳለባቸው ነው የሚገባኝ፡፡ የሕጽናዊነት ዓላማ ይሄንን ባዶ ቦታ መሙላት ነው፡፡ የሚነበበው ነገር መሙያው ነው፤ አዲሱ ጽሑፍ ማለት ነው፡፡ ከ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ጋር ባደረግሁት ቃለ ምልልስ ይሄንን ነገር ‘ኢንተርቴክስቹዋሊቲ’ ብዬ አስቀምጬው ነበር፡፡ ይሄን ያደረግኩት ግን በወቅቱ ሕጽናዊነትን የሚያክል ተስማሚ ቃል ባለማግኘቴ ነበር፡፡
ገሃዱን ዓለም በማንፀባረቅ ረገድ አንድ ወጥ የሆነ ትረካ ሕጽናዊ ከሆነው ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚለው ጥያቄም ነበር፡፡ ከ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” [እ.ሎ.ሽ.] በፊት የጻፍኳቸውን ታሪኮች አሁን ላይ ሆኜ ሳያቸው የተሟሉ አይደሉም፡፡ ሕጽናዊነት በዚህ ረገድ የቀድሞ እኔነቴን በራሴ የለካሁበት/የሄስኩበት ስልት ነው፡፡ (“Hisinawinet” in this case becomes a critique of my earlier self)
ሕጽናዊነት የአንዱ ከሌላው መያያዝ ነው… ራሳቸውን እንደ ደሴት የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ ከላይ ሲታይ የተለዩ ይመስሉ ይሆናል፤ በጥልቅ ላጠናቸው ግን ሰዎች እርስ በራስ የተጠላለፉ/የተቆራኙ/የተዛመዱ ናቸው… በዘር፣ በቋንቋ፣ እልፍ የባሕል እሴቶችን በመጋራትም”፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸውን መረባዊ ግንኙነት ማሳየት የሕጽናዊነት አንዱ ግብ መሆኑ በአዲሱ መጽሐፍ “መረቅ” ውስጥ እንዲህ ተቀምጧል፡ “በሕጽናዊነት አመለካከት በሰው ልጆች መሃል ያለው የግንኙነት መስመር ቀጥተኛ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው በግልጽም ይሁን በሕቡዕ መረባዊ መሆኑን ማንሳት ነው” (ገጽ 599)፡፡
አዳም ቀጥሏል… “የሕዳግ ማስታወሻ የሚያገለግለው እነኚህን መረባዊ ግንኙነቶች ጠቅልሎ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት ነው፡፡ በእ.ሎ.ሽ. ከበደ ሚካኤልን ሳጣቅስ የእሳቸውን ፖለቲካዊ አቋም እደግፋለሁ ማለት አይደለም ወይም ደግሞ ባሕልን እንደሳቸው ሁሉ በወግ አጥባቂ ዐይን እቃኛለሁ ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ የእሳቸውን ያክል መልከ መልካም ነኝ ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ሎሚ ሽታን ወይም የፍቅረስላሴን ልጅ ታደሠን ያውቁታል ማለት አይደለም ወዘተ…  የባሕል መረቡ በቀስታ ተስፋፍቶ እዚያች ደረጃ ድረስ እንዴት እንደሚደርስ ለማሳየት ብቻ ነው፡፡ (showing how cultural network can percolate and present itself to that minute depth)
ታዲያ ከሌላ ደራሲ ሥራ የተወሰደን አጭር ተረክ በአንድ ወጥ በሆነ ልቦለድ ውስጥ መጠቀም አዲሱን ታሪክ የፊተኛው ጥገኛ፤ በራሱ መቆም የማይችል፤ ክፍተት ያለበት አያደርገውም? ብሎ ለሚጠይቅ ቅን አንባቢ፣ አዳም ይሄንን ይመልሳል… “እቴሜቴ ውስጥ ያካተትኩትን ያን የከበደ ሚካኤልን ተረት [በማር ጠብታ ውስጥ ስለሰጠሙ ሕዝቦች የሚተርከውን] ቆርጬ ባወጣው እንኳ ልቦለዴ ያለምንም የይዘትም ሆነ የሴራ እንከን ፍሰቱን ይቀጥላል”፡፡
አንዳንድ የሕጽናዊነት መገለጫዎች
ከሕጽናዊነት መገለጫዎች አንዱ ኢንተርቴክስቹዋሊቲ ነው፡፡ ኢንተርቴክስቹዋሊቲ ማለት በቀላሉ በአንድ ትረካ ውስጥ ሌላ ገጠመኝ፣ ሌላ ልቦለድ፣ የታሪክ አጋጣሚ ወዘተ ሲጠቀስ ማለት ነው፡፡ የዚሁ ትርጓሜ ተመሳሳይ የሆነው ኢንትራቴክስቹዋሊቲም መነሳት ይኖርበታል፡፡ የሁለቱ ልዩነት በአጭሩ ሲቀመጥ፤ የመጀመሪያው አንድ ደራሲ  የሌላን ደራሲ/ገጣሚ ሥራ (የዕውንም ይሁን ምናባዊ)፤ ከዕውነታው ዓለም የተቀዳ ገጠመኝ፤ የጋዜጣ ጽሑፍ ወዘተ ሲጠቀም ሲሆን ሁለተኛው ድሞ አንድ ደራሲ የራሱን ቀደምት ሥራዎች ሲያጣቅስ ማለት ነው፡፡
“ብዙ የተማረ ዜጋ/ብዙ ያነበበ ዜጋ ባላቸው አገሮች ዋቤ ሳይጠቅሱ (የዕውነት ያለን) ጽሑፍ ማጣቀስ የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ያ ጽሑፍ የሌላ ሰው እንደሆነ ይሄኛው ደራሲ ግን እንደ ወሽመጥ እየተጠቀመው ወይ ደሞ እየተረበው እንደሆነ አንባቢው ያውቃል፡፡
በእኛ አገር ግን አለመግባባትን ለማስወገድ በሕዳግ ማስታወሻ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ አለመግባባቱም ሁለት ዓይነት መልክ ሊኖረው ይችላል፡
አንደኛው አንዳንድ አንባቢ (በቅን ልቦናም ይሁን በተንኮል) ያ የተወሰደው ጽሑፍ የተሰረቀ ነው ብሎ ሊያስብ ስለሚችል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንባቢው የተጣቀሰው ጽሑፍ ዓላማ ላይገባው ስለሚችል ነው፡፡ አንባቢው ይሄን መረዳት ካልቻለ ደግሞ አንዱ የኢንተርቴክስቹዋሊቲ ግብ ልቦለድን ወደ ዕውነታዊ ክዋኔ ማምጣት (bring fiction as experience) ተኮላሸ ማለት ነው”፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን በምሳሌ እንመልከት፡፡ ደራሲው በእ.ሎ.ሽ. “በማር ጠብታ ውስጥ ስለሰጠሙ ሕዝቦች አንብቤያለሁ” ሲል በሕዳግ ማስታወሻ የከበደ ሚካኤል ታሪክ እንደሆነ ገልፆዋል፡፡ በ”መረቅ”ም “ግቡ እናንተ ተስፋ ያልቆረጣችሁ” (ገጽ 73) ሲል ከዳንቴ “ዲቫይን ኮሜዲ” እንደወሰደው ጠቅሷል፡፡ በሌላ መልኩ ማንም ያነበበው፤ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ታሪክ ነው ብሎ በማሰብ፤ ማንም “ባለ ቅን ልቦና” ወይ “ሴረኛ” የተሠረቀ (plagiarized)  ነው እንደማይለው በማመን፤ እንዲሁም ልቦለድን ወደ ዕውነታዊ ክዋኔ ለማምጣት (to bring fiction as experience) የፊታውራሪ መሸሻን፤ የሰብለን፣ የበዛብህን እንዲሁም የእንቆጳን ታሪክ (አንዳንድ ለውጦች ተደርገውባቸው) እንዲሁ በ”መረቅ” ውስጥ ተጠቅሟቸዋል፡፡
አዳም ከቲዮሪ ባሻገር በሥራዎቹ ኢንተርቴክስቹዋሊቲን ብቻ ሳይሆን ኢንትራቴክስቹዋሊቲንም ይጠቀማል፡፡ በየመጽሐፎቹ ውስጥ እዚህም እዚያም የሚገኙት የግጥምና የዘፈን ስንኞች፤ ቦታቸውን እንዳገኙ ሁሉ ስክት የሚሉት የግዕዝ ሀረጋት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፤ ምናባዊ ማጣቀሻ መጻሕፍቱ እና የጋዜጣና የመጽሔት ቃለ ምልልሶች ወዘተ የኢንተርቴክስቹዋሊቲ አብነቶች ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ በአዳም ልዩ ልዩ መጻሕፍት መካከል እንዲሁም በአንድ የአዳም መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ትረካዎች መካከል ያሉ እንደ ዘሀ የቀጠኑ የግንኙነት መስመሮች የኢንትራቴክስቹዋሊቲ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ”ሕማማት እና በገና” ውስጥ ያለው ትንሽ ልጅ (የብርሃኑ ጓደኛ) “አለሙ” የተሰኘ የቤት ስም አለው፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” (ይ.መ.ያ.መ.) ላይ ያለው ዋና ገፀ ባሕሪ “አለሙ” ይሰኛል፡፡
ሁለቱም የሸማኔ ልጆች መሆናቸው የአጋጣሚ ነገር ይመስላችኋል? በ”መረቅ” ውስጥ በጨረፍታ ዳሰስ የተደረገችው ሊሊና የዚታዎ ሾፌር የሆኑት ጓደኛዋ ዘርአብሩክ በኩሳንኩስ ውስጥ አንድ የታሪክ አንጓ ተሰጥቷቸው አልተተረኩምን? የ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገዱ” ሸገኔ “መረቅ” ውስጥ ተጠቅሶ የለምን? እ.ሎ.ሽ. “ጉርሻ ተሻጋሪ ነው” በምትል ቀጭን መስመር ከ”መረቅ” አልተዛመደም? በይ.መ.ያ.መ. በእያንዳንዱ ትረካ ላይ ብቅ የሚለው ያ ጃን አሞራ በታሪኮቹ መካከል ትስስር አልፈጠረም? በእ.ሎ.ሽ. ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችስ አንዳቸው ከሌላቸው በገጸ ባህርያቱ የትውውቅ  እና የዝምድና መረብ የተጠላለፉ አይደሉ? “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” ውስጥ “ለብሮት” የሚለው ታሪክ ገጸ ባሕሪ ትርንጎ፤ በ”ሕማማት እና በገና” “የሳር ልጆች” ውስጥ ተመልሳ አልመጣችም? ብዙ ብዙ፡፡ ይሄ እንግዲህ በእኔ አቅም ሊታይ የቻለ ትስስር ነው፤ ጊዜውን ሰጥቶ በጥልቀትና በጥንቃቄ ለሚያጠናው ሰው ከዚህም በላይ ግንኙነቶችን መጥቀስ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ፡፡

Read 5207 times