Monday, 20 October 2014 08:21

ዋሽንግተን - በአዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

        ለትምህርት ወደ አሜሪካ የሄዱት በወጣትነታቸው ነው - በ20 እና በ21 ዓመታቸው፡፡ ከአገር የወጡበትን ዓላማ ለማሳካት ኮሌጅ ገብተው ሴቷ ስለ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር)፣ ወንዱ ደግሞ ስለ ቴክኒክ ሙያ ተምረዋል፡፡
በአሜሪካ መኖር የሚቻለው እየሰሩ ነው፡፡ ያለበለዚያ ዶላር የሚመነዝር ቅልጥጥ ያለ የከበርቴ ልጅ መሆን የግድ ነው፡፡ ወጣቶቹ እንደዚያ ስላልሆኑ፣ ተግተው መሥራት ነበረባቸው፡፡ በዋሺንግተን ዲሲና ሜሪላንድም “አዲስ አበባ” የተባለ ምግብ ቤት ከፍተው የኢትዮጵያን ባህልና ምግብ በማስተዋወቅ ከ30 ዓመት በላይ እየሰሩ ኖረዋል፡፡
ዕድሜአቸውን በሙሉ በውጭ አገር መኖር አልፈለጉም፡፡ ወደ አገራቸው ተመልሰው በቋጠሯት ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ፣ ለወገኖቻቸው የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ወሰኑ፡፡
ወ/ሮ ወርቅነሽ ጌታቸውና አቶ አስፋው አምዴ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ አቶ አስፋው፣ በቀድሞው ልዑል መኮንን በአሁኑ አዲስ ከተማ መሰናዶ ት/ቤት የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አሜሪካ የሄዱት እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም ነው፡፡
ወ/ሮ ወርቅነሽ ደግሞ 1ኛ ደረጃን በአርበኞች ት/ቤት፣ 2ኛ ደረጃን በቀድሞው እቴጌ መነን፣ በአሁኑ የካቲት 12 መሰናዶ ት/ቤት ጨርሰው ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን የተጓዙት ከአምስት ዓመት በኋላ ነበር፡፡
በዚያው ዓመት ነበር ሁለቱ ጥንዶች የተዋወቁት፡፡ ከዚያም እንደ ድርጅትም እንደ ማህበረሰብም ሆነው ከዚህ የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያን በመቀበል፣ አገሪቷንም ለአሜሪካ በማስተዋወቅ በአምባሳደርነት ሲያገለግል የቆየውንና ታዋቂውን “አዲስ አበባ ምግብ ቤት” እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ መክፈታቸውን ይናገራሉ፡፡
እዚያም የኢትዮጵያን ምግብና ባህል በማስተዋወቅ ለ21 ዓመት ሰሩ፡፡ ምግብ ቤቱ የበለጠ ታዋቂ እየሆነ፣ የሚያስተናግደው አበሻም ሆነ ፈረንጅ እየጨመረ ሲሄድ፣ መኪና ማቆሚያ ቦታ ጠበበ፡፡
 በ2005 ዓ.ም ሜሪላንድ ወደተባለችው ከተማ ተዛውረው፣ እዚያም ታዋቂውን አዲስ አበባ ምግብ ቤት መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሜሪላንድ 8 ዓመት ከሰሩ በኋላ ነው ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ የመጡት፡፡ጥንዶቹ ከ10 ዓመት በፊት ቦታ ገዝተው የሆቴል ግንባታ ጀመሩ፡፡
70 የመኝታ ክፍሎች ያሉትና አትላስ አካባቢ የሚገኘው ዋሺንግተን ሆቴል ሥራ የጀመረው በቅርቡ ቢሆንም በሚሰጠው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ወ/ሮ ወርቅነሽ ይናገራሉ፡፡
ለስብሰባ፣ ለመዝናናትም ሆነ ለሥራ… ከውጭ ለሚመጡ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና የቢዝነስ ሰዎች ያዘጋጀነው 5ኛና 6ኛ ፎቅ ያሉት ቪአይፒ ክፍሎች እኛን ከሌሎች ሆቴሎች ይለዩናል ያሉት ወ/ሮ ወርቅነሽ፤ በሁለቱ ፎቆች ያሉት ክፍሎች ለአንድ መሪ ቤተሰብ፣ ባለሥልጣናትና አጃቢዎች ወይም ለአንድ አገር ዲፕሎማትና አብረውት ለሚመጡ የሥራ ኃላፊዎች ወይም ለአንድ አገር የቢዝነስ አባላት ቡድን … የሚከራዩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ቪአይፒ ክፍሉ የራሱ ሳሎን፣ የራሱ ምግብ ማብሰያ (ኪችን) ለቤተሰብና አብረው ላሉ እንግዶች የሚሆኑ 5 መኝታ ክፍሎች፣ ጃኩዚ፣ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ ዋና መኝታ ቤት፣ የራሱ ባርና መዝናኛ ቴራስ፣ ልዩ የደህንነት ጥበቃ… ያሉት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አሁን ያልተጠናቀቁ ነገሮች ስላሉ ሁሉም ነገር ሲያልቅ ሆቴሉ በጠቅላላ 180 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ያሉት አቶ አስፋው፤ ዋሺንግተን በነበረው አዲስ አበባ የባህል ምግብ ቤት የተሰየመው የምግብ አዳራሽ ሁሉንም ዓይነት ባህላዊ ምግቦች ያዘጋጃል ብለዋል፡፡
 ኮሎምቢያ በማለት የበሰየሙት ዘመናዊ ሬስቶራንት ከ40 በላይ የውጭ አገር ምግቦች እንደሚያዘጋጅ፣ ሁለት ባር እንዲሁም በመቅደላ የተሰየመ ትልቅ አዳራሽ፣ ጆርጅታውን ጂምና ስፓ፣ አዲስ አበባን 360 ዲግሪ እያዩ የሚዝናኑበትና በ18 ዲስትሪክት የተሰየመ ቴራስ ሬስቶራንትና ባር፣ … እንዳሉት ገልጸው፤ ሆቴሉንና የተለያዩ አገልግሎት መስጪያዎችን በውጭ አገር ስሞች የሰየሟቸው ለብዙ ዓመታት የሚያውቋቸውን የአሜሪካ አካባቢዎች ለማስታወስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡የሆቴሉ ምግብ በእንግዶች የተወደደ ንፁህ፣ ጣፋጭና ጥራቱን የጠበቀ ቢሆንም ዋጋው ተመጣጣኝ በመሆኑ ኪስ አይጐዳም፣ አንድ ምግብ በ150 ብር መመገብ ይቻላል፣ ከዚያም በታች አለ ብለዋል፡፡
የመኝታ ክፍሎቹ ዋጋ ሲንግል ቤድ 95 ዶላር፣ ደብል ቤድ 120 ዶላር፣ ሱት ክፍሎች 160 ዶላር፣ ልዩ የሆነው ቪአይፒ 950 ዶላር እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ስብሰባ ሲኖርና አስጐብኚ ድርጅቶች በርከት ያሉ እንግዶች ሲያመጡ የዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ሆቴሉን ሲሰሩ ነገሩ ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ የጠቀሱት አቶ አስፋው፤ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሰጠው ዕድል ቋሚ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዳስገቡ ገልፀው፣ ከባንክ ብድር ማግኘት፣ የጉምሩክ ቢሮክራሲ፣ ባለሙያ የሆነ የኮንስትራክሽን ሠራተኛ እጥረት… ዋና ዋናዎቹ ችግሮች እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ ሆቴሉ ለ130 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረም ለማወቅ ተችሏል፡፡      

Read 3440 times