Monday, 20 October 2014 08:19

ህዳሴ ቴልኮም የሞባይል ፋብሪካ ለማቋቋም ከZTE ጋር ተፈራረመ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

        ሕዳሴ ቴልኮም አክሲዮን ማኅበር፣ የZTEን ስማርት ፎኖች ለማከፋፈልና በአገር ውስጥ የሞባይል ስልኮች መገጣጠሚያና ማምረቻ ፋብሪካ ለማቋቋም ከድርጅቱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
ሰነዱ በተፈረመበት ወቅት የሕዳሴ ቴልኮም ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ታደሰ አስፋው በሰጡት መግለጫ፤ የድርጅቱ ምርት የሆነውን ZTE Smart Phone ስልኮች በኢትዮጵያ ለማከፋፈል መስማማታቸውን ጠቅሰው፣ ስልኮቹ እጅግ ዘመናዊና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ በመሆኑ ተጠቃሚው የተሻለ አማራጭ እንደሚያገኝ በማሰብ ZTEን እንደመረጡ ገልጸዋል፡፡
አቶ ታደሰ፣ ሞባይል ስልኮችን ከማከፋፈል በተጨማሪ የቴክኖሎጁ ሽግግር ወደ አገራችን በማምጣት፣ የውጭ ምንዛሪ ከማዳን አልፎ የሞባይል ስልኮችን ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሞባይል መገጣጠሚያና ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ከ ZTE ጋር መስማማታቸውንና የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡
የፋብሪካው መቋቋም የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል፣ የሥራ እድል ይፈጥራል፣ ZTE Smart Phones ወደ ምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያመጣል፣ ዜጎች የሚፈልጉትን ዘመናዊ ቀፎ በተሻለ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ፋብሪካውን ለመትከል ረዥም ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ፣ በአገር ውስጥ ትርፍ የሞባይል መገጣጠሚያ ካላቸው ድርጅቶች ጋር መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሰረት፣ የ ZTEን ቴክኖሎጂና ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ከሁለትና ከሶስት ወር ባልበለጠ አጭር ጊዜ ZTE Smart Phones እናመርታለን ብለዋል፡፡
በመግባቢያ ሰነዱ ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ ኢትዮጵያ በቴሌኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ እያደረገች ያለውን ታሪካዊ ዕድገት መመስከር ችለናል ያሉት የ ZTE ተወካይ ጥቂት መቶ ሺዎች የነበሩት የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፣ ገቢውም ከበፊቱ ከ10 ጊዜ በላይ ጨምሯል ብለዋል፡፡
ዘመኑ የደረሰበትን የመጨረሻ የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቅመን የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ የ ZTE ስማርት ፎኖችን በአዲሱ የህዳሴ ፋብሪካ እንደሚገጣጥሙ ጠቅሰው፣ እኛ ሰፊ አማራጭ ያለው ሸሪክ እንፈልጋለን፡፡ ህዳሴ 800 ማከፋፈያዎችና 1,000 የሽያጭ ሰራተኞች ስላሉት ነው አብረን ለመስራት የመረጥነው፡፡ ስለዚህም ምርቶቻችን በመላ አገሪቱ እንደሚዳረሱ እምነታችን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እዚህ የምናመርታቸውን ZTE ስማርት ስልኮች ከህዳሴ ጋር ወደ ጎረቤት አገሮች እንልካለን በማለት ገልፀዋል፡፡
ህዳሴ ቴልኮም አክሲዮን ማህበር፣ ኢትዮቴሌኮም ባደረገው የመዋቅር ለውጥ ምክንያት ምደባ ባላገኙ ሰራተኞች የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ2,500 በላይ አባላት ያሉት ኩባንያ መሆኑን አቶ ታደሰ ገልጿል፡፡
ኩባንያው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎት መሰረታዊ የመገናኛ አገልግሎት ከመስጠት ተነስቶ በተለያዩ የቴሌኮም ምርቶች ስርጭትና በሌሎችም ዘርፎች በመሳተፍ ካፒታሉን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደጉ መልካም ስምና ዝና እያገኘ በመሆኑ እህት ኩባንያዎችን በመክፈት ዓለማቀፍ ኩባንያ ለመሆን ማቀዱን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ከሚያከፋፍላቸው የቴልኮም ምርቶች ቫውቸር ካርድ፣ ሲም ካርድ የሞይል ቀፎዎች፣ የኢንተርኔት መጠቀሚያ CDMA፣ ገመድ አልባ CDMA፣ የስልክ ቀፎዎች … ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

Read 2372 times