Monday, 20 October 2014 08:17

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ልታልፍም ላታልፍም ትችላለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

     በ2015 እኤአ  ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ልታልፍም፤ ላታልፍም ትችላለች፡፡ ይህ ሁኔታ  ብሄራዊ ቡድኑ የምድቡን አራተኛ ዙር ግጥሚያ ከሜዳው ውጭ ማሊን 3ለ2 ካሸነፈ በኋላ ተፈጥሯል፡፡ ከሳምንት  በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድቡ የ3ኛ ዙር ግጥሚያ በሜዳው ላይ በማላዊ 2ለ0  መሸነፉ የማለፍ ተስፋውን አደብዝዞት ነበር፡፡ በምድብ ሁለት ሌላ የ3ኛ እና 4ኛ ዙር ግጥሚያዎች  አልጄርያ ማላዊን በድምሩ 3ለ0 በሆነ ውጤት በሜዳዋ እና ከሜዳዋ ውጭ አሸንፋለች፡፡ ከእነዚህ ውጤቶቿ በኀላም አልጄርያ ቀሪ የሁለት ዙር የምድብ ጨዋታዎች በ12 ነጥብ እና በ6 የግብ ክፍያ ወደ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ያረጋገጠች የመጀመርያዋ አገር ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሜዳው ውጭ ባማኮ ላይ ማሊን 3ለ2 ማሸነፉ በጣም አስደንቋል፡፡ ዋልያዎቹ ለ40 ደቂቃዎች በ10 ተጨዋቾች በመጫወት ነው ይህን የተስፋ ጭላንጭል የፈጠረ ውጤት ያስመዘገቡት፡፡ በ53ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ የተባረረው ጌታነህ ከበደ ነበር፡፡  ጎሎቹን ኡመድ ኡክሪ ፤ ጌታነህ ከበደ እንዲሁም ባለቀ ሰዓት የማሸነፊያዋን ግብ አምበሉ አበባው ቡጣቆ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ ውጤቱ ያበሳጫቸው የማሊ ደጋፊዎች ሜዳ ላይ  የፕላስቲክ ጠርሙሶች በመወርወር ስሜታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከወር በኋላ የምድብ ማጣርያው አምስተኛ እና ስድስተኛ ዙር ግጥሚያዎች ይደረጋሉ፡፡ በ5ኛው ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታ  አልጄርያ በአልጀርስ ኢትዮጵያን ስታስተናግድ፤ ማላዊ በብላንታየር ማሊን ትገጥማለች፡፡ በመጨረሻዎቹ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ማላዊን ስታስተናግድ ማሊ በባማኮ አልጄርያን ትገጥማለች፡፡
ከምድብ ማጣርያው አራተኛ ዙር ግጥሚያዎች በኋላ አልጄርያ ምድቡን በ12 ነጥብ እና በ6 የግብ ክፍያ ትመራለች፡፡ ማሊ በ6 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ስትሆን ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ እንዲሁም ማላዊ በ3 ነጥብ እና በአምስት የግብ እዳ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው አፍሪካ ዋንጫ ለመብቃት ያለው እድል የተሟጠጠ አይመስልም፡፡ ቢያንስ በቀሪዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ ከአልጄርያ ጋር እንዲሁም በመጨረሻው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ በሜዳው የሚያስተናግደውን የማላዊ ቡድን ማሸነፍ ከቻለ በሌሎቹ የምድብ ግጥሚያዎች ላይ የተንተራሰ የማለፍ ተስፋ ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያና 4ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶ እቅድ
 ደቡብ አፍሪካ ካስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የውድድሩ መስተንግዶ በተለያዩ ምክንያቶች እያነጋገረ ነው፡፡ በአዘጋጆች ምርጫ፤ በፖለቲካ ግርግር እና አለመረጋጋት፤ በመሰረተ ልማት አለመሟላት የአፍሪካ ዋንጫ እየተስተጓጎለ ነው፡፡ አሁን ሰሞኑን ደግሞ ሞሮኮ በምዕራብ አፍሪካ በተስፋፋው የኢቦላ ወረረሽኝ ሳቢያ በ2015 እኤአ የምታስተናግደውን 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላታዘጋጅ እንደምትችል አስታውቃለች፡፡ ምክንያት ያደረገችው ደግሞ የኢቦላ ወረረሽኝን ነው፡፡ የኢቦላ ወረረሽኝ በቁጥጥር እስኪውል ድረስ ውድድሩን የማስተናገዱ ሁኔታ ወደ 2016 እኤአ ይዛወርልኝ ብላ ሞሮኮ ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ጥያቄ አቅርባለች፡፡ የኢቦላ ወረረሽኝ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ ክፍል ከ4000 በላይ ህይወት መቅጠፉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሞሮኮ ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካስገባችው ማመልከቻ በኋላ  ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎችን ያለ አዘጋጅ ናቸው፡፡ በ2017 እኤአ ላይ ሊቢያን በመተካት 31ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እንደሚያዘጋጅ  እስካሁን አልታወቀም፡፡ ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ የሞሮኮ ምትክ ሆኖ ለማስተናገድ ፍላጎታቸውን ወዲያውኑ ገልፀዋል፡፡  ሱዳንም ከሁለቱ አንደኛው የአፍሪካ ዋንጫ ይሰጠኝ እያለች ነው፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከወር በፊት በአዲስ አበባ ያደረገውን ጉባዔ ሲያጠናቅቅ የ3 አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጆችን መርጧል፡፡ በ2019 እኤአ 32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ካሜሮን፤ በ2021 እኤአ 33ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አይቬሪኮስት እንዲሁም በ2023 እኤአ 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጊኒ እንደሚያዘጋጁ አስታውቋል፡፡ ለሶስቱ አፍሪካ ዋንጫዎች አመልክተው በምርጫው ውድቅ የተደረጉት የሰሜን አፍሪካዋ አልጄርያ እና የደቡብ አፍሪካዋ ዛምቢያ ናቸው፡፡ በዚሁ የካፍ የአዘጋጅ አገሮች ምርጫ በተለይ የምስራቅ፤ የሰሜንና እና የደቡብ አፍሪካ ዞኖች ደስተኞች አይደሉም፡፡ ምክንያታቸውም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለምእራቡ የአፍሪካ ክፍል አድልቷል የሚል ነው፡፡ ይህን የሚያመለክቱ ማስረጃዎችም አሉ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው ዋና ስፖንሰር ኦሬንጅ የተባለው የሞባይል እና ኮሚኒኬሽን ኩባንያ በምዕራብ አፍሪካ ከፍተኛ ገበያ መያዙ ለኮንፌደሬሽኑ ውሳኔ ተፅእኖ ማድረጉን በመጥቀስ የተቹ አሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት ከተደረጉ 13 የአፍሪካ ዋንጫዎች ስድስቱ በምእራብ አፍሪካ አገራት መካሄዳቸው በዚህ ተፅዕኖ እንደተፈጠረ ይገለፃል፡፡  የመስተንግዶ እድሉን ካገኙት አገራት ሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅተው ያውቃሉ፡፡ ጊኒ ብቻ ለመጀመርያ ጊዜ የመስተንግዶ እድሉን አግኝታለች፡፡ ከምዕራብ አፍሪካ ውጭ የአፍሪካ ዋንጫን አንዴም አዘጋጅተው የማያውቁ ከ10 በላይ አገራት በተለያዩ የአህጉሪቱ ዞኖች ነበሩ፡፡  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከላይ በተጠቀሱት ሶስት አፍሪካ ዋንጫዎች አዘጋጆቹን ከምእራብ አፍሪካ መምረጡ በ2017 ለሚደረገው ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሊቢያ ምትክ የሆነ አዘጋጅን ከምዕራባዊ የአፍሪካ ዞን ውጭ ሊመርጥ ይችላል የሚል መላምት አሳድሯል፡፡  በ2017 ለሚደረገው ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማመልከቻው ጊዜ ቀነ ገደቡ ያለቀው ከ20 ቀናት በፊት ነበር፡፡ ለመስተንግዶው ያመለከቱት አገራት የሰሜን፤ የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ አገራት ይበዙበታል፡፡ ገና ከጅምሩ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ለመስተንግዶው ፍላጎት ያላቸው  አገራት በዋናነት ኢትዮጵያ እና ኬንያ መሆናቸው ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ኬንያ የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ጠብቃ ማመልከቻዋን በጥናታዊ ፊልም በማጀብ ስታስገባ ኢትዮጵያ ግን በተለያዩ ሚዲያዎች የማዘጋጀት ፍላጎቷን በፌደሬሽኑ እና በመንግስት አመራሮች ከመግለጿ በቀር ማመልከቻውን በቀነ ገደቡ ሳታደርስ ቀርታለች፡፡ ከሳምንት በፊት ካፍ በኦፊሴላዊ ድረገፁ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ያመለከቱት 7 አገራት  አልጄርያ፤ ግብፅ፤ ጋቦን፤ ጋና፤ ኬንያ፤ ሱዳንና ዚምባቡዌ ናቸው፡፡ ከመካከላቸው አራቱ ከዚህ በፊት ውድድሩን የማስተናገድ እድል ነበራቸው፡፡ እያንዳንዳቸው እኩል አራት ጊዜ ያስተናገዱት ግብፅ (1974,1986,2006) እና ጋና(1963,1978,200,2008)  ሲሆኑ፤ ሱዳን በ1962 እንዲሁም አልጄርያ ደግሞ በ1990 እኤአ የማዘጋጀት ታሪክ አላቸው፡፡   ለመጀመርያ ጊዜ መስተንግዶውን የጠየቁት ደግሞ ኬንያ እና ዚምባቡዌ ናቸው፡፡
በ2019 እና በ2022 ለሚደረጉት ሁለት አፍሪካ ዋንጫዎች የመስተንግዶ ማመልከቻ አስገብታ ያልተሳካላት አልጄርያ በ2017 እኤአ ውድድሩን ለማስተናገድ ሰፊ  እድል ይኖራታል፡፡የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የ31ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ በመወሰን የሚያስታውቀው በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2015 ሰኔ ወር ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እና መስተንግዶ ህልም በአግባቡ ካልተመራ የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን በአህጉራዊ ውድድሮች ያለው የተሳትፎ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይሄዳል፡፡ ሊቢያ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶን በተወች ማግስት ኢትዮጵያ አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት  ያላትን ፍላጎት ተቻኩላ ማቅረቧ  ሲናፈስ ቢሰነብትም ለመወዳደር በሚቀርብ የስራ እቅድ እና አቅም ሊካተቱ የሚገባቸው አቀራረቦች እና በመሰረተ ልማት ደረጃ ቅድመ ስራዎች ተሰርተዉ አለመጠናቀቃቸው የመፎካከሩን እድል አሳጥቷል፡፡ አንዳንድ የስፖርት ቤተሰቦች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ከምትሯሯጥ አስቀድሞ  የታዳጊዎች፤የወጣቶች እንዲሁም የሴቶችን አህጉራዊ ውድድሮች በማዘጋጀት ብቃቷን መለካት ተገቢ  እንደሆነ ጎን ለጎን ሲመክሩ ይሰማ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት አሳይታ በተገቢው ቀነ ገደብ ማመልከቻ ስላስገባች ከፉክክር ውጭ መሆኗን የሚያመለክቱ ዘገባዎች በሌሎች አማራጭ እቅዶች መንቀሳቀስ መጀመሯን አውስተዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በ2020 እኤአ ላይ ስድስትኛውን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ እንዲሁም በ2025 እኤአ ላይ 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ እናመለክታለን በማለት ለሱፕር ስፖርት የተናገሩት ከሳምንት በፊት ነው፡፡
 ከ29 የአፍሪካ ዋንጫዎች በአስሩ ላይ መሳተፍ የቻለችው ኢትዮጵያ ለሶስት ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ነበረች፡፡
በ1962 ውድድሩን በማዘጋጀት ሻምፒዮን ስትሆን እንዲሁም በሌሎች ባዘጋጀቻቸው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በ1968 እኤአ ላይ አራተኛ ደረጃ እና በ1976  እኤአ ደግሞ ከመጀመርያው ዙር ከውድድሩ ተሰናብታለች፡፡



Read 3399 times