Monday, 20 October 2014 08:15

በአሜሪካ ምርጫ የሚወዳደሩ ጥቁሮች ቁጥር ክብረ ወሰን አስመዘገበ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      በአሜሪካ በመጪው ወር ለሚካሄደው የግዛትና የኮንግረስ ምርጫ የሚወዳደሩ ጥቁር ፖለቲከኞች ቁጥር ክብረ ወሰን ማስመዝገቡንና የፖለቲካ ተንታኞችም፣ ባራክ ኦባማ በምርጫ አሸንፈው በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት መሆናቸው በጥቁር አማሪካውያኑ ላይ ለታየው የፖለቲካ ተሳትፎ እድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በሁለቱ ምርጫዎች የሚሳተፉ ጥቁር ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከ100 በላይ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ 83 ያህል ጥቁር የሪፐብሊካንና የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ለአሜሪካ ምክር ቤት እንደሚወዳደሩና ይህም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ አስታውቋል፡፡25 ያህል አፍሪካ አሜሪካውያን በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች ለሴናተርነት፣ ለገዢነት ወይም ለሌተናንት ገዢነት ስፍራዎች እንደሚወዳደሩና፣ ይህም በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛ እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡ከዚህ ቀደም ለአሜሪካ ምክር ቤት አባልነት በርካታ ጥቁሮች የተወዳደሩበት እንደሆነ የተመዘገበው፣ እ.ኤ.አ በ2012 የተካሄደውና ፕሬዚዳንት ኦባማ ለሁለተኛ ዙር አሸንፈው በስልጣን መቀጠላቸውን ያረጋገጡበት ምርጫ ሲሆን  በዚህ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ጥቁሮች 72 እንደነበሩ ዘገባው አስታውሷል፡፡ በግዛቶች ምርጫ በርካታ ጥቁሮች የተወዳደሩበት አመት እ.ኤ.አ 2002 እንደነበረ ጠቁሞ፣ በወቅቱ የተወዳዳሪዎች ቁጥር 17 እንደነበርም አስረድቷል፡፡ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካን አሜሪካን ፖለቲክስ ኤንድ ሶሳይቲ ማዕከል ዳይሬክተር  ፕሮፌሰር ፍሬዴሪክ ሲ ሃሪስ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ጥቁሮች በምርጫ ድምጽ እንዲሰጡና  ጥቁር ፖለቲከኞችም ከዚህ ቀደም በጥቁሮች ተይዘው በማያውቁ የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች ላይ ለመቀመጥ እንዲወዳደሩ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

Read 1925 times