Monday, 20 October 2014 08:12

ማላላ በቦኮ ሃራም የታፈኑ ልጃገረዶችን ለማስፈታት ጥረት እንዲደረግ ጠየቀች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ባለፈው ሳምንት የኖቤል የሰላም ሽልማት የተቀበለችው ፓኪስታናዊቷ የህጻናት መብቶች ተሟጋች ማላላ ዮሱፋዚ፣ የናይጀሪያ መንግስትና አለማቀፉ ማህበረሰብ ቦኮ ሃራም በተባለው አሸባሪ ቡድን የታፈኑትን 219 የአገሪቱ ልጃገረዶች በአፋጣኝ ለማስለቀቅ በስፋት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረቧን ቢቢሲ ዘገበ፡፡የመብት ተሟጋቾች ከስድስት ወራት በፊት በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱትና አሁንም ድረስ በአሸባሪዎች ቁጥጥር ስር የሚገኙት የአገሪቱ ልጃገረዶች ነጻ እንዲወጡ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ያቀረበችው ማላላ፣ ልጃገረዶቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀልና ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ትምህርት ማግኘት ይገባቸዋል ብላለች፡፡“የአገሪቱ መንግስት እና አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ አፋጣኝና ሰላማዊ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያደርጉትን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድጉ እጠይቃለሁ” ብላለች ማላላ፡፡ማላላ ባለፈው ሃምሌ ወር ወደ ናይጀሪያ በማምራት በጉዳዩ ዙሪያ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ጋር መወያየቷን የጠቆመው ዘገባው፣ ልጃገረዶቹ ባለፈው ሚያዝያ በሰሜን ምስራቃዊ ናይጀሪያዋ ቺቦክ ከተማ ወደሚገኘው የአዳሪ ትምህርት ቤታቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ  በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች መጠለፋቸውን አስታውሷል፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ልጃገረዶቹን ለማስለቀቅ በቂ ጥረት አላደረገም የሚል ትችት እንደሚሰነዘርበት የጠቀሰው ቢቢሲ፤ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአገሪቱ ሚኒስትሮች ግን ትችቱን እንዳጣጣሉት አመልክቷል፡፡በቅርቡ “ልጃገረዶቻችንን መልሱልን” የሚል ዘመቻ ያዘጋጁ የናይጀሪያ የመብት ተሟጋቾች፣ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ አቡጃ  ወደሚገኘው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቤት ማምራታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ፖሊሶች ወደ ስፍራው እንዳይደርሱ እንደከለከሏቸው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1859 times