Monday, 20 October 2014 08:11

የሉአላዊ አገር መስፈርት ምንድን ነው?

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(4 votes)

     በቅርቡ ከታላቋ ብሪታንያ ተገንጥላ ራሴን የቻልኩ ሉአላዊ ሀገር መሆን እፈልጋለሁ በሚል ህዝበ ውሳኔ በማካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንንና የንግሥት ኤልሳቤጥን ልብ ልታቆመው ደርሳ የነበረችው ስኮትላንድ በመጨረሻ የመገንጠሉን ሃሳብ ትታዋለች፡፡
ያኔ ጉዳዩ ትኩስ ኬክ ሆኖ በነበረበት ጊዜ የስኮትላንድን መገንጠል ከሚቃወሙት ወገኖች ከሚቀርቡት ምክንያቶች አንዱ “ስኮትላንድ ትንሽ ሀገር ስለሆነች እንደ ሉአላዊ አገር ራሷን ችላ መቆም አትችልም” የሚል ነበር፡፡
ዛሬ ከስፔን ተገንጥዬ ራሴን መቻልና ሉአላዊት ሀገር መሆን እፈልጋለሁ በሚል ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ በወር ተረኛነት ሽር ብትን እያለች የምትገኘው የካታላን ግዛት ነች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የስፔናውያን ወቅታዊ የመነጋገሪያ አጀንዳም ይሄው 7.6 ሚሊዮን ህዝብ የያዘችው የካታላን ግዛት ከስፔን የመገንጠል ጥያቄ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ብሎ ቀኑን ቁርጥ አድርጐ በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል እንጂ ሚሊዮን ህዝብ ያላት የቤልጅየሟ የፍሌሚሽ ግዛት (ዘራቸው ደች የሆነና ደችኛ ተናጋሪ ቤልጅየማውያን የሚኖሩበት አካባቢ) እና 4.9 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት የጣሊያኗ የቤኒቶ (ቬኒስ) ግዛት ከቤልጅየምና ከጣሊያን ተገንጥለው የራሳቸውን ሉአላዊ ሀገር ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ልክ እንደ ስኮትላንዳውያኑ ሁሉ የእነዚህን ግዛቶች መገንጠል የሚቃወሙት ቡድኖች በምክንያትነት ከሚያቀርቧቸው ጉዳዮች አንዱ የግዛቶቹ ትንሽነት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ጉዳይ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአንድ ግዛት ሉአላዊ ሆኖ እንደ ሀገር የመኖር እጣ ፈንታው በያዘው የግዛትና ህዝብ መጠን የሚወሰን ከሆነ፣ ለመሆኑ በትልቁ አለም ውስጥ ስንት ትናንሽ ሉአላዊ አገራት አሉ? ወይም በሌላ አገላለፅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአባልነት ከተመዘገቡት 193 ሉአላዊ ሀገራት ውስጥ 5.2 ሚሊዮን ዜጐች ካሏት ከስኮትላንድ ያነሱ ስንት ትናንሽ አገራት ይገኛሉ?
በ1990 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአባልነት የመዘገባቸው ሉአላዊ ሀገራት ቁጥር 159 ብቻ ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም ግን የአባል ሀገራት ብዛት ወደ 191 ከፍ ብሏል፡፡ ይህ ማለት በአስራ ሁለት አመታት ውስጥ ብቻ 32 ነፃና ሉአላዊ አገራት በአለማችን ተፈጥረዋል ማለት ነው፡፡አሁን ካሉት አንድ መቶ ዘጠና ሦስት ሉአላዊ የአለማችን አገራት ውስጥ ታዲያ እንደ ኳታር፣ ቆጵሮስ፣ ባህሬይን፣ ለክሰምበርግ፣ አይስላንድና ባርባዶስን ጨምሮ አርባ የሚሆኑ ሀገራት የጠቅላላ ህዝባቸው ቁጥር አንድ ሚሊዮን እንኳ አይሞላም፡፡ የእነዚህ አርባ ነፃና ሉአላዊ አገራት ህዝቦች በጠቅላላ ሲደመሩ 12.5 ሚሊዮን ብቻ ናቸው፡፡
5.2 ሚሊዮን ዜጐች ያሏት ስኮትላንድ፤ 78 ሀገራትን በህዝብ ብዛት ትበልጣለች፡፡ በቅርቡ ባካሄደችው ህዝበ ውሳኔ ነፃና ሉአላዊ ሀገር መሆኗን ብታውጅና አንድ መቶ ዘጠና አራተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገር ሆና ብትመዘገብ ኖሮ፣ በህዝብ ብዛቷ ቱርክሜንስታንን ተከትላና ኖርዌይን አስከትላ የአንድ መቶ አስራ ስድስተኛ ደረጃን ትይዝ ነበር፡፡ከጠቅላላው የአለማችን ሀገራት ውስጥ አንድ መቶ ስድስቱ የጠቅላላ ህዝባቸው ቁጥር ከአስር ሚሊዮን በታች ነው፡፡ እስካሁን የተመለከትናቸው መረጃዎች፣ የግዛት መጠንና የህዝብ ቁጥር ለአንድ ሀገር ነፃና ሉአላዊ መሆን ወሳኝ ነገር እንዳልሆነ በሚገባ ማስረዳት ይችላሉ፡፡ የግዛቶቹን ነፃነትና ሉአላዊነት ከዚህ ይልቅ መወሰን የሚችለው ጉዳይ የግዛቶቹ የኢኮኖሚ አቅም ነው፡፡   

Read 4418 times