Monday, 20 October 2014 08:10

የኢቦላ ተጠቂዎች ቁጥር እስከ ነገ ከ9ሺ እንደሚበልጥ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እስከ ነገ ከ9ሺህ በላይ ይደርሳል  ተብሎ እንደሚጠበቅ የአለም የጤና ድርጅትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ባለፈው መጋቢት ወር በጊኒ የተከሰተውና በምዕራብ አፍሪካ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ 8ሺህ 914 ሰዎችን እንዳጠቃና ከነዚህ ውስጥም 4ሺህ 447 ያህሉ ለህልፈት እንደተዳረጉ የጠቆመው ዘገባው፣  ቁጥሩ ዛሬና ነገ ከ9ሺህ በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ረዳት ዳይሬክተር ብሩስ አይልዋርድ እንዳሉት፣ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በተከሰተባቸው አንዳንድ አካባቢዎች አዳዲስ ሰዎችን የማጥቃቱ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም፣ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተስፋፋ በመሆኑ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ድርጅቱ እንደተነበየው፤ የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ በየሳምንቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ አስር ሺህ ሊደርስ ይችላል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ኢቦላ በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት በቫይረሱ የተጠቁና የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ ይፋ እየተደረጉ ያሉ መረጃዎች፣ የተዛቡና ከትክክለኛው ቁጥር ያነሱ ናቸው ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ችግሩን ለመቅረፍ ተገቢው ጥረት እንዳይደረግ የሚያዘናጋ ነው ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው ባለፈው ረቡዕ በኢቦላ ዙሪያ ለመምከር በዋይት ሃውስ በጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ፣ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የጤና ባለሙያዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ የቫይረሱን ስርጭት መግታት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑንና የአገሪቱ መንግስትም ኢቦላ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው መግለጻቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሲዲሲና ከሚመለከታቸው የአገሪቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ብሄራዊ ግብረሃይል አቋቁመው በአፋጣኝ ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ኢቦላን ለመዋጋት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የተለያዩ የዓለም አገራት መሪዎችን እንደሚያግባቡ መናገራቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ቢቢሲ ከአፍሪካ ውጭ ያለውን የኢቦላ ክስተት በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ የዘንድሮው ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በአሜሪካ 8፣ በጀርመን 3፣ በስፔን 3፣ በኖርዌይ 1፣ በፈረንሳይ 1 እና በእንግሊዝ 1 በድምሩ 17 ሰዎች በኢቦላ የተያዙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም አንድ አሜሪካዊ፣ አንድ ጀርመናዊና ሁለት ስፔናውያን ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ ከሶስቱ ሰዎች በስተቀር ሁሉም በቫይረሱ የተያዙት ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት በሄዱበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የታዋቂው የማህበረሰብ ድረገጽ የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙክበርግ የኢቦላን ወረርሽኝ ለመግታት የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ የሚውል የ25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ብሉምበርግ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ዙክበርግና ባለቤቱ ፕሪስኪላ ቻን ገንዘቡን ለአሜሪካው ሲዲሲ ፋውንዴሽን ያስረከቡ ሲሆን፣ የህክምና ማዕከላትን ለማቋቋምና አፍሪካውያን ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የመሳሰሉ ስራዎች እንደሚውል ተነግሯል፡፡
“ኢቦላ የበለጠ ከመስፋፋቱና አለማቀፍ የጤና ቀውስ ከመሆኑ በፊት በአፋጣኝ በቁጥጥር ውስጥ ልናውለው ይገባል” ብሏል ዙክበርግ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት፡፡





Read 2343 times