Monday, 20 October 2014 08:01

ወሮበላው ጋዜጠኛ

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(10 votes)
  • እህቱን አግብቷል
  • ሴቶችን እያስገደደ ይደፍር ነበር
  • ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ኢትዮጵያን አተራምሷል

          የተወለደው እ.ኤ.አ ሐምሌ 29 ቀን 1883 ነው፤ ቦታው ደግሞ በሰሜን ጣሊያን ሮማኛ አውራጃ ውስጥ ቫራኖ ዴደ-ኮስታ በተባለ ወረዳ ነው፡፡ አባቱ የብረታ ብረት ፋብሪካ ሠራተኛ ሲሆን እናቱ የአንደኛ ደረጃ መምህርት ነበረች፡፡ አባቱ ከወጣትነቱ ጀምሮ የሶሻሊስት ፓርቲ አባል የነበረ ቢሆንም የሚታወቀው ግን በወረበላነቱና በሰፈር አዋኪነቱ ነው፡፡ በየአደባባዩና በየመንደሩ እየዞረ በከፍተኛ ጩኸት መንግሥትን በመቃወም ታዋቂ እንደነበረም ተዘግቧል፡፡ ሰካራም፣ ሴቶችን በማደን የሚታወቅና በወንጀለኞች መዝገብ ተደጋጋሚ ሪከርድ ያለበት መሆኑንም ታሪክ ጸሐፊዎች ይገልፃሉ፡፡
ከዚህ አይነቱ ነውረኛ ወዛደር የተወለደው ልጅ፣ እንደ መምህርቷ እናቱ ደግና ለሰው አሳቢ ከመሆን ይልቅ የአባቱን ፈለግ በመከተል ታላላቆችንና መምህራኑን በማዋረድ ገና በለጋ ዕድሜው መደዴ ጠባዩን በህዝብ ዘንድ አስመሰከረ፡፡ መምህርቷና ካቶሊካዊቷ እናቱ “ቤኒቶን ሳሌዚያኖ” በተባለ የካቶሊኮች ትምህርት ቤት አስገብታ ከአቅሟ በላይ ገንዘብ በመክፈል ትልቅ ሰው እንዲሆንላት፣ ጠባዩም እንዲታረምላት ከፍተኛ ጥረት አድርጋ ነበር፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በት/ቤቱ ቢቆይም ክፍያው ከአቅሟ በላይ ስለሆነ ከቤኒቶን ሳሌዚያኖ ማስወጣት ግድ ሆነባት፡፡
ምንም እንኳ በጠባዩ እጅግ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም በቀለም አቀባበሉ ጐበዝ ስለነበር የነፃ ትምህርት እድል እንዲያገኝ እናቱ ያለ የሌለ ጥረት አደረገች፡፡ ግን በብልሹ ሥነምግባሩ የተነሳ ጥያቄዋ በት/ቤቱ መምህራንና ኃላፊዎች ዘንድ ተቀባይነት አጣ፡፡ ት/ቤቱ የነፃ ትምህርት እድሉን የነፈገው ህፃኑ፤ አንድ ቀን “መምህሬ አበሳጭቶኛል” ብሎ ቀይ ቀለም በመበጥበጥ ከመምህሩ ፊት ላይ በመድፋቱ፣ የክፍል ጓደኛውን በጩቤ በመውጋቱና ለወደፊቱም ከዚህ አይነቱ ሰይጣናዊ ግብሩ ሊመለስ ይችላል የሚል እምነት ስላጣበት ነበር፡፡
ተስፋ የማትቆርጠው እናቱ ከቤኒቶን ሳሌዚያኖ ት/ቤት አስወጥታ አነስተኛ ክፍያ ወደሚጠይቅ ሌላ አዳሪ ትምህርት አስገባችው፡፡ ወጣቱ እዚያም መበጥበጡንና ጓደኞቹንም ሆነ መምህራኑን ማወኩን ሲቀጥል አዳሪነቱ ቀርቶ በተመላላሽነት እንዲማር ተወሰነበት፡፡ ይህ ውሳኔ ለእናቱ እጅግ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ምክንያቱም ለትምህርቱ ከምትከፍለው በተጨማሪ ለቤት ኪራይና ለቀለቡ የሚሆን ሌላ ወጪ በመምህርነት ደሞዟ መቋቋም የምትችለው አልነበረም፡፡
ሆኖም ልጇ አንድ ደረጃ ደርሶ የማየት ህልሟ ከፍተኛ የነበረው እናቱ፤ ጓደኞቿንና በቅርብ የሚያውቋትን ሰዎች እያስቸገረች ትምህርቱን እንዲቀጥል አደረገች፡፡ “ፎርሊምፓፓሊ” በመባል ከሚታወቀው ኮሌጅም የሁለት ዓመት የመምህርነት ስልጠና ወስዶ ለሥራ ዝግጅ ሆነ፡፡ ግን በብልሹ ሥነምግባሩ የተነሳ በየትኛውም የገጠር ት/ቤት ተቀባይነት አጣ፡፡ የወሮበላ አባቱ ሥነምግባርም ለልጁ ሥራ ማጣት የላቀ ድርሻ ነበረው፡፡
ለአንድ ዓመት ያህል ለመምህርነት ሥራ ደጅ ቢጠናም ሊሳካለት ባለመቻሉ ሲበሳጭና ሲያዝን የቆየው ያ ወጣት፤ በሚኖርበት የሮማኛ አውራጃ “ፕሬዳፒዮ” በተባለ ማዘጋጃ ቤት የጸሐፊነት ሥራ ማስታወቂያ ወጣና ተወዳደረ፤ በፈተናውም የተሻለ ውጤት በማምጣት ማለፉ ተረጋገጠ፡፡ ግን ከንቲባው “ፈተናውን በከፍተኛ ውጤት አንደኛ ሆነህ ብታልፍም ብልሹ ምግባርህን ስለምናውቅ ቦታውን አታገኘውም” የሚል መልስ ስለሰጠው ወጣቱ ከመጠን በላይ ተበሳጨ፡፡ ይህን የሰማው ዱርዬ አባቱም በደም ፍላት ወደ ማዘጋጃ ቤቱ በማምራት “…እናንተ ምቀኞች ዛሬ በስልጣናችሁ ያጠቃችሁትን ይህን ልጅ ጌታዬ ብላችሁ ጫማውን የምትስሙበት ጊዜ ይደርሳል” ሲል ዛተ፡፡በዚህም የተነሳ ወጣቱ ማተቡን በጥሶና የካቶሊክ እምነቱን ክዶ፣ የሶሻሊስት ፓርቲ አባል በመሆን በየአደባባዩ “እግዚአብሔር የለም!” በማለት መደንፋቱን ቀጠለ፡፡ በየቀኑ ጥዋት እየተነሳ ከአባቱ ጋር በመሆን ወደ ፓርቲው ጽ/ቤት ከመሄድና ተገቢ ስራ ከማከናወን ይልቅ በእግራቸው የሚሄዱ አቅመ ደካማ ሽማግሌዎችንና አሮጊቶችን ንብረት እየቀማ ማምለጥ ዕለታዊ ተግባሩ አደረገው፤ በሚያገኘው የውንብድና ገንዘብም በየመሸታ ቤቱ በመዞር መስከር፣ ከመሰሎቹ ጋር መደባደብ፣ የመዝናኛ ቦታዎችን የአንባጓሮ መናኸሪያ ማድረግ በማዘውተሩ በየጊዜው በፖሊስ እየተያዘ ዘብጥያ ይወርድ ጀመር፡፡
የኋላ ኋላ የዱርየነት ህይወት እንደማያዋጣው ሲገነዘብ፣ በሰኔ 1902 (እ.ኤ.አ) ወደ ስዊዘርላንድ ተሰደደ፡፡ ወደ ስዊዘርላንድ መሄድ የፈለገው ከ1900 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በርካታ የሀገሩ ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ በመሄድ በግንበኝነት ሥራ ተሰማርተው ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ስለነበር እሱም እድሉን ለመሞከር ነው፡፡ ግን “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም” እንደሚባለው፣ እዚያም  ያ ብልሹ ምግባሩ ተከትሎት ነበርና የሀገሩን በርካታ ስደተኛ ሰራተኛ አእምሮ የሚረብሽ ሀሳብ በማቅረብ ሰላማቸውን በጠበጠው፡፡
ድንጋይ በመፍለጥ፣ በመጥረብ፣ አሸዋ እያቦኩ በመሸከም ለግንበኞች በማቅረብ መኖር እንደማያዋጣው ሲያውቅ፣ የሰራተኛ ማህበር ማቋቋምን እንደ መፍትሄ አድርጎ በመቀስቀስ፣ ስደተኛ ሰራተኞች ማህበር እንዲመሰርቱ በማድረግ፣ ከአገሩ ከወጣ ዓመት ሳይሞላው የማህበሩ ዋና ፀሐፊ በመሆን በከፍተኛ ድምፅ ለመመረጥ በቃ፡፡ የሰራተኛውን አዕምሮ በመሰሪ አቀራረቡ ስላነሳሳውም ብዙሃኑ ሰራተኛ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ጄኔቭን በሰላማዊ ሰልፍ አስጨነቃት፡፡
ያልተለመደ ነገር ያጋጠማቸው የስዊስ የፀጥታ ሰራተኞች “ዋና አስተባባሪዎች ናቸው” ያሏቸውን ግለሰቦች ይዘው ሲመረምሩ፣ ለምን እንደተሰለፉ እንኳ ማስረዳት አልቻሉም፤ በአንፃሩ አመጹን ያቀጣጠለው ስደተኛ ግን ከመሃላቸው አልተገኘም፡፡ የኋላ ኋላ እውነቱን ደረሱበትና ያለስራ ፈቃድ ገብቶ ከመኖሩም በላይ በሰላም ሲሰሩ የነበሩትን ስደተኛ ሰራተኞች ሰላም በማናጋቱ ከማህበር መሪነቱ ተሽሮ ሚያዚያ 6 ቀን 1904 (እ.ኤ.አ) ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ተደረገ፡፡
ወደ ሃገሩ ሲመለስም ህይወት ፊቷን አጨፍግጋ ጠበቀችው፤ አባቱ የተለመደ የወሮበላነት ተግባሩን ሲያከናውን ተገኝቶ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከርቸሌ የገባ ሲሆን ምስኪኗ እናቱ ደግሞ በሳምባ በሽታ ተይዛ ትማቅቅ ነበር፡፡ ዙሪያው ገደል የሆነበት ወጣቱ ስራ የሚያስገባው ቢያጣ ወታደራዊ አገልግሎት በመስጠት ህይወቱን ለማቆየት ተመዘገበ፡፡ የሁለት ዓመት ነፃ ወታደራዊ አገልግሎት ሰጥቶ በ1906 (እ.ኤ.አ) ወደ ትውልድ ቦታው ሲመለስ፣ የገጠመው ትልቁ ፈተና የተለመደው ስራ አጥነት ነበር፡፡
በዚህ የተነሳ ወደ ፈረንሳይ ተሻግሮ “ማርሴይ” ከምትባለው የወደብ ከተማ መኖር ቢሞክርም ወዲያውኑ ተይዞ ወደ አገሩ ተባረረ፡፡ ችግሩ እየጠነነበት ሲሄድም ራሱን ለማጥፋት ሁሉ ወስኖ ነበር፡፡ በመሃሉ ታዋቂው ፈላስፋ ካርል ማርክስ የሞተበት 25ኛ ዓመት በዓል ሲከበር በሶሻሊስቶች ጋዜጣ ላይ የጻፈው አንድ መጣጥፍ ከፍተኛ አድናቆትን አተረፈለት፡፡ አድናቆት ብቻ ሳይሆን መጠነኛ ድጎማ እየተሰጠው ጋዜጣው ላይ ጽሑፍ እንዲያቀርብም የሶሻሊስት ፓርቲው አባላት ፈቀዱለት፡፡
ወጣቱ ያገኘውን የጋዜጠኝነት ዕድል ተጠቅሞ በመላ አገሪቱ በመዘዋወር የሶሻሊስት እንቅስቃሴውን ያጧጡፈው ጀመር፡፡ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት እየተቸ በሚያቀርበው ዘገባ ፖሊስ እያደነ ወህኒ ቢዶለውም ፍንክች የሚል አልሆነም፡፡ እንዲያውም እስር ቤት ያየውን ጉድ ሁሉ ጋዜጣ ላይ በመዘክዘክ ጋዜጣውን ተወዳጅ ከማድረጉም በላይ፣ ገቢውንም በእጥፍ ማሳደግ በመቻሉ ዱርየው አባቱ ሳይቀር ተጠቃሚ ሆነ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን እናቱ ሞታ አባቱ ቀደም ሲል ጀምሮ ይታማባት የነበረች ሴት አግብቶ ይኖር ነበር፡፡ ከቤታቸው ደግሞ “ራሄል” የምትባል አንዲት የ16 ዓመት ቆንጆ ልጅ ትኖራለች፡፡ ራሄል የተወለደችው የጋዜጠኛው እናት በህይወት እያለች አባቱ በውሽምነት ይዟት ከነበረችበት በኋላ ካገባት ሴት ነው ተብሎ በጎረቤት ነዋሪዎች ዘንድ ይታመናል፡፡
አንድ ቀን ጋዜጠኛው አባቱን ሊጠይቅ ወደ ቤቱ ጎራ ሲል ቆንጆዋን የ16 ዓመቷን ኮረዳ አየና ወዲያው በፍቅሯ ተንበረከከ፡፡ ለማግባትም ውሳኔ ላይ ደረሰ፤ አባቱና የእንጀራ እናቱ ጋብቻውን አጥብቀው ቢቃወሙም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ከአባቱ የምትወለድ እህቱን ማዘጋጃ ቤት ሄዶ በሚስትነት አስመዘገባት፡፡ ምስኪኗ ራሄልም ያለውዴታዋ የወሮበላው ጋዜጠኛ ህጋዊ ሚስት ሆነች፡፡
የወሮበላውን ጋዜጠኛ ህይወት የቀየረችው አጋጣሚ የተፈጠረችለት ግን ታህሳስ 1 ቀን 1912 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ”አቫንቲ” በመባል ለሚታወቀው የሶሻሊስት ፓርቲ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንዲሰራ መወሰኑን የምታበስረው ደብዳቤ ከደረሰችው ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
በሳምንት 20 ሺህ ቅጂ ብቻ የነበረው “አቫንቲ” ጋዜጣ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መቶ ሺህ ቅጂ ተመነደገ፤ የዋና አዘጋጁ ዝናም በአስደናቂ ፍጥነት በመላዋ አገሪቱ ናኘ፡፡ እ.ኤ.አ በ1915 ከሶሻሊስት አመለካከቱ ወደ ሊበራሎች ዞረና “ኢል - ፓፓሎ” የተባለ ጋዜጣ በማቋቋም ሶሻሊስቶችን መከራ ያበላቸው ጀመር፤ ይባስ ብሎ በ1919 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) “ፋሽስት“ ፓርቲ በማቋቋም፣ በአገሩ ህዝብ ዘንድ የላቀ ተደማጭነት አገኘ፡፡
ከዚያም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ሮማን ለ22 ዓመታት ቁምስቅሏን አሳያት፡፡ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስም ኢትዮጵያን ወርሮ በህዝቦቿ ላይ እጅግ ከፍተኛ ግፍ ፈፀመባት፤ ይህ ወሮበላ ጋዜጠኛ ዱቼ ሙሶሎኒ ይባላል፡፡
ምንጭ፡- ልዩ ልዩ የመረጃ መረቦችና ዘውዴ ረታ (የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ መንግስት 1ኛ መጽሐፍ)፡፡     

Read 4181 times