Monday, 20 October 2014 07:59

የግጥምና ዜማ ደራሲው አበበ መለሰ የተሳካ የኩላሊት ተከላ ተደረገለት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

     አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን ዕውቅና ለመጐናፀፍ የበቁባቸውን ከሁለት ሺህ በላይ ግጥምና ዜማዎች በመድረስ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ዝነኛው የግጥምና ዜማ ደራሲ አበበ መለሰ፤ ለበርካታ አመታት ሲያሰቃየው ከነበረው የኩላሊት ህመም በተደረገለት የኩላሊት ተከላ የተሟላ ጤንነት መጎናጸፉ ኢትዮጵያዊያንን እንዳስደሰተ “የአበበ መለሰ የህክምና ድጋፍ አሰባሳቢ የኪነጥበብ ሰዎች ኮሚቴ” ሰሞኑን አዲስ አበባ በሚገኘው ዋሽንግተን ሆቴል በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡
የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው አባላት አርቲስት ሃይልዬ ታደሰ፣ ዮሴፍ ገብሬ፣ ንዋይ ደበበ፣ ዳዊት ይፍሩና የአበበ መለሰ የቅርብ ጓደኛ የሆነው አቶ ፍሰሃ ዘውዴ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአሁኑ ሰዓት አበበ መለሰም ሆነ ኩላሊቱን በሙሉ ፈቃደኝነት ያበረከተለት በ20ዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ የሚገኘው ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ለአበበ መለሰ ኩላሊታቸውን ለመስጠት 12 ሰዎች ተመዝግበው እንደነበር የገለፁት የኮሚቴው አባላት፤ በደም አይነትም ሆነ በሌሎች መስፈርቶች የወጣቱ ኩላሊት በመመረጡ በጐ ፈቃደኛው ለሌሎች የጤና ምርመራዎችና በቂ የስነ ልቦና ዝግጅት ለማድረግ ለአምስት ወራት ያህል በሆስፒታል ውስጥ የቆየ ሲሆን  ከመስከረም 17 እስከ 19 ደግሞ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጐለት መስከረም 20 በቀዶ ጥገና ኩላሊቱን ለአበበ ማስረከቡን አስታውሰዋል፡፡ አርቲስት አበበም መስከረም 21 ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት የተደረገለት የአምስት ሰዓት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በእስራኤል የሚገኘው የቤሊንሰን ሆስፒታል ሃኪሞች ማብሰራቸውን አርቲስት ሃይልዬ ታደሰ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡ ቤሊንሰን ሆስፒታል ከቴላቪቭ የ3  ደቂቃ ጉዞ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡  ከቀዶ ህክምናው በኋላ ህክምናውን ያደረጉለት ሃኪሞች “እንኳን ደስ ያለህ በሆስፒታሉ ታሪክ ስኬታማ ከሆኑ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናዎች አንዱና በጣም ስኬታማው ነው፤ ህክምናው ባለቀ በሁለት ሰዓት ውስጥ ሽንት መሽናት መቻልህ የህክምናው ስኬት መገለጫ ነው” እንዳሉት አበበ መለሰ መናገሩን የኮሚቴው አባላት ገልፀዋል፡፡ “ኩላሊት የሰጠኝ ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬ ለእኔ ጀግናና ከእህትም ከወንድምም በላይ ነው” ሲል አበበ ከፍተኛ ምስጋና ማቅረቡን የተናገሩት የኮሚቴው አባላት፤ “ለእኔ ኩላሊት ለመስጠት የተዘጋጁት ሌሎች 12 ሰዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ባለውለታዬ ነው” ማለቱን ጠቁመዋል፡፡
“አርቲስትም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ የጤና ችግር የነበረባቸው ሰዎች  በውጭ አገር  ህክምናቸው ተሳካ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፤ የአበበ ህክምና በስኬት መጠናቀቁ ትልቅ ብስራት ነው” ያለው ነዋይ ደበበ፤ አርቲስቱም ሆነ ህዝቡ ያደረገው ትብብር ሊዘነጋ የማይችል እንደሆነ ተናግሯል፡፡
የኮሚቴው አባላት አክለው እንደገለፁት፣ አበበ መለሰ ከህክምናው ሙሉ በሙሉ ሲያገግም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሙያ አጋሮቹንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማመስገን እንደጓጓ፣ እስከዚያው ግን ደስታውን የአገሩ ህዝብ እንዲጋራው በድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው በኩል መልእክት ማስተላለፉ በመግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡
“ለመሆኑ ለህክምናው ምን ያህል ወጪ ተደረገ?” በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ የኮሚቴው አባላት በሰጡት ምላሽ፤“ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው የተሰበሰበውን ብር በቀጥታ ለአበበ ከመስጠት ባለፈ ለሆስፒታሉ ክፍያ ባለመፈፀሙ ምን ያህል እንደወጣ መረጃ የለንም፤ ይህንን የጉዳዩ ባለቤት ወደፊት የሚገልፀው ይሆናል” ብለዋል፡፡
ከኮንሰርቱ ምን ያህል ገቢ እንደተገኘና ለአበበ መለሰ ስንት እንደደረሰው የተጠየቁት የኮሚቴው አባላት “ራሱ አበበ መለሰ ይናገር” በማለት ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ምሽት በሸገር 102.1 ኤፍኤም በሚተላለፈው የ“ታዲያስ አዲስ” ፕሮግራም ላይ ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ አበበ መለሰን በተመለከተ በሰጠው ተገቢ ያልሆነ መግለጫ የኮሚቴው አባላትም ሆነ ራሱ አበበ መለሰ ማዘኑን ከኮሚቴው አባላት አንዱ የሆነው የአርቲስቱ የቅርብ ጓደኛ አቶ ፍሰሃ ዘውዴ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
 “አረጋኸኝ በእርግጥ የገንዘብ መዋጮ አድርጓል፤ ነገር ግን ላፍቶ ሞል በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርትም ሆነ በእስራኤሉ ጉዞ ላይ እንዲሳተፍ ሲጋበዝ አይመቸኝም በማለት አልተገኘም” ያለው አቶ ፍሰሃ፤ በ“ታዲያስ አዲስ” ፕሮግራም ራሱን የድጋፍ ማሰባሰቡ ዋና የአርቲስቶች አስተባባሪና የሁነቱ መሪ አድርጐ ማቅረቡ በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው፣ በሙያቸውና በጊዜያቸው ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈሉ አርቲስቶችን ሞራል የሚነካ በመሆኑ የኮሚቴ አባላቱም ሆኑ ራሱ አበበ መለሰም እጅግ ማዘናቸውን ጨምሮ ገልጿል፡፡
ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ በበኩሉ፤“እኔ የወንድሜን የአበበ መለሰን የህክምና ስኬት በደስታ ከመግለፅ ውጭ ስለኮሚቴው ስራ ያልኩት ነገር የለም” ብሏል፡፡ “መጀመሪያውኑም መታመሙን ሃይልዬ ለሰይፉ ነግሮት የድጋፍ ማሰባሰቡን ስራ ያቀጣጠለው ሰይፉ በመሆኑ ደስታውን ነግሬው ለህዝቡ ቢገልፅ ምን ክፋት አለው፤ የኮሚቴ አባላቱን የሚያበሳጭስ ምን ጉዳይ አለ?” ሲል ጠይቋል፤ አረጋኸኝ፡፡ “ከሁለት ዓመት በፊት አበበን ሳገኘው ኩላሊቱን እንደታመመና ዲያሊስስ እንደሚያደርግ አልነገረኝም፡፡ ሃይልዬም የሰማው ከራሱ ከአበበ ሳይሆን ከወንድሙ ከዘመነ መለሰ ነው” ያለው አረጋኸኝ፣ ሰይፉ የአበበን መታመም በሚዲያ ከገለጸ በኋላ ብዙ እንቅስቃሴ ተደርጓል ብሏል፡፡
ሆኖም ኮንሰርቱ ጁን 1 ቀን ይደረጋል ሲሉ እኔም አሜሪካን አገር ጁን 1 ቀን ስራ ነበረኝ ያለው ድምፃዊው፤ ጁን 1 ቀን በሚደረገው የአበበ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት ላይ ለመገኘት የአሜሪካ ስራውን ወደ ጁን 15 ቢያዛውርም ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ኮንሰርቱን ወደ ጁን 15 በማዛወራቸው ፕሮግራሙ እንደተቃወሰበትና ጁን 9 ቀን ወደ አሜሪካ ስራው እንደበረረ አክሎ ገልጿል፡፡ በእስራኤሉ ስራ ላይም ያልተሳተፈው ገና የአሜሪካ ስራው ባለመጠናቀቁ እንደነበር አብራርቷል፡፡
“አበበን እስራኤል አገር አግኝቼው ህክምናው በስኬት መጠናቀቁን ሰለነገረኝና ያለበትን ሁኔታ በማየቴ ከደስታዬ ብዛት መጥቼ ለሰይፉ ነገርኩት እንጂ ኮንሰርቱ ላይ ተሳትፌያለሁ፣ ኮሚቴው ይህን ሰርቷል፣ ይህን ያህል ገንዘብ ተሰብስቧል የሚል ኮሚቴውን የሚመለከት ነገር አላነሳሁም” ያለው አረጋኸኝ፤ የማይመለከተኝን እስካልተናገርኩና ከዜናው ጀርባ የማገኘው ጥቅም እስከሌለ ድረስ የቅርብ ጓደኛዬንና የወንድሜን ደስታ ለሰይፉ መንገሬ ሌሎችን የሚያበሳጭበት ምክንያት አልገባኝም ብሏል፡፡
“እኔ፣ አበበ መለሰና ይልማ ገ/አብ የተለየ ቅርበትና ቤተሰባዊ ግንኙነት ያለን ሰዎች ነን” ያለው አረጋኸኝ፤ አርቲስት አበበ በሃዋሳ የእርሱን ስራ ሲሰራ ቤተሰቦቹ ወደ እስራኤል ጥለውት እንደሄዱና ይህን ያህል መስዋዕት እንደከፈለለት አስታውሶ “እኔና አበበን ለማጋጨትና በመሃል ጣልቃ ለመግባት ከመጀመሪያ ጀምሮ ሲያገሉኝ ነበር”፤ ነገር ግን ኮንሰርቱ ላይ ባልሳተፍም የአቅሜን ያህል አድርጌያለሁ” ብሏል፡፡ “እኔ ለሰይፉ በነገርኩት ዜና የተበሳጩት የሙዚቃ ሙያተኞች ሳይሆኑ ጉዳዩ የማይመለከታቸው አንዳንድ ግለሰቦች ናቸው” በማለትም የቀረበበት ቅሬታ ትርጉም የለሽ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

Read 5077 times