Monday, 20 October 2014 07:57

“እንደ ሰዉ አላውቅበት ብለህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…‘ቻልኩበት’ የምትለው ዘፈን አትመቻችሁም! የምር እኮ…የዘመናችንን ነገር ቁልጭ አድርጋ የምታሳይ ነች፡፡ ልጄ… አልችልበት ብሎ የዱቄት ጆንያው የተራገፈና የበይ ተመልካች የሆነ ስንትና ስንት አለ አይደል! የቻሉበት ደግሞ…የጠፈር መንኮራኩርን በሚያስንቅ ፍጥነት… አለ አይደል…ግድግዳው ላይ ያለው የቀን መቁጠሪያ ገና ሳይጋመስ… ‘ሁሉ ሙሉ፣ ሁሉ ዝግጁ’ ሲሆንላቸው ነገርዬው የእጣ ፈንታ ሳይሆን ‘የመቻል’ና ‘ያለመቻል’ ይሆናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዲት የተለመደች አባባል አለች፡፡ አለ አይደል…ነገር አልሳካ ሲል፣ ኑሮና ብልሀቱ አልሆን፣ አልሆን ሲል….ምን ይባላል መሰላችሁ… “እንደ ሰዉ አላውቅበት ብለህ…” ይባላል፡፡ አሪፍ አባባል አይደል!
እናላችሁ… ሰዉ አጨብጭቦ የሚቀረው ‘እንደ ሰዉ አላውቅበት…’ እያለ ነው፡፡
ታዲያላችሁ…‘እንደ ሰዉ ያወቀበት…’ ምን አይነቱ መሰላችሁ… በሁሉም ነገር የነፋሱን አቅጣጫ እያየ ነገረ ሥራውን የሚያስተካክል፡፡ ልክ ነዋ!…የሚናገረው ንግግር እንደሚሰማው ሰው ማንነት ይለያያል…ለአንዱ …ያለውን ሌላው….
እናማ… ‘እንደ ሰዉ ማወቅ’ አስፈላጊ የሆነበት ዘመን ሆኗል፡፡ በ‘ፕሪንሲፕል’ ምናምን መመራት የሚባለው ነገር “ያረጀና፣ ያፈጀ…” ነገር እየሆነ ነው፡፡ “እንደ ሰዉ ማወቅ ምን ማለት ነው?” የሚል ሰው ገና የጨዋታው ህግ አልገባውም ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ በቦተሊካ አንዱ ‘ማወቅ’ ምን መሰላችሁ…ቋንቋውን መለማማድ፡፡ እናማ…በምኑም በምናምኑም የዘመኑን ቃላት እያመጡ መክተት፡፡ የሆነ ስብሰባ ላይ “በሠፈራችን አንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ለማስቀመጥ የህዝቡን የለውጥ ስሜት ባገናዘበ መልኩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሥራዎች እየተሠሩ ነው…” አሁን አንድ ገንዳ ይቀመጣል ተብሎ ሌኒን እንኳን ሊያልመው የማይችል አይነት ንግግር ጉዳዩ የገንዳው ሳይሆን…አለ አይደል… እንደ ‘ሰዉ የማወቅ’ ነው፡፡
ወይም ደግሞ የሆነ ስብሰባ አለ እንበል፡፡ እናማ… ሥራ አስኪያጁ “በተከታዩ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሠራተኛው ሁሉ ሊረባረብ ይገባል…” ይላሉ፡፡ ይሄኔ ያላወቀበት ሁሉ አጨብጭቦ ዝም ሲል ያወቀበት ደግሞ እጁን ያወጣል፡፡ “በእውነቱ አሁን ሥራ አሥኪያጁ በተናገሩት ንግግር ላይ የምጨምረው የለኝም፡፡
ያደረጉልን ንግግር የድርጅቱን ሠራተኞች የሥራ ፍላጎት የሚጨምርና ምርታማነትን የሚያሳድግ ነው፡፡ በእውነቱ ሥራ አስኪያጃችን ከተሾሙ በኋላ መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ለውጥ በማስመዘገብ ላይ ነው…” ምናምን አይነት ‘እንደ ሰዉ የማወቅ’ ንግግሮች ይናገራል፡፡ (ከዓመት እቅዱ ያሳካው እኮ 51% ነው፡፡ ያውም ከ50% በታች ምን ይባላል ተብሎ አሥራ ዘጠኟ ባልተጻፈ ስምምነት የገባች ነች!)  በዚህ ቢበቃው ጥሩ! “የምጨምረው ነገር የለም…” ያለው ሰው… አለ አይደል…“ባለፈው በሰው በላው ስርአት ጊዜ…”  ምናምን አይነት ነገር ይጨምርላችኋል፡፡
እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰሞኑን ‘ሰው በላው ስርአት’ ትንሽ ከውግዘት ቀለል አለለት መሰለኝ፡፡ ልክ ነዋ…“‘ከሀንድረድ ይርስ’ ምናምን ወዲህ ያለ ውግዘት ሁሉ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል…” የተባለ ነው የሚመስለው! ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞላችሁ…የአለቆች ቢሮ አካባቢ ሹክ፣ ሹክ፡… ‘እንደ ሰዉ ማወቅ’ አለ፡፡ እናላችሁ… አንዳንዱ በስብሰባ ምናምን ላይ ‘እንደ ሰዉ ሲያውቅበት’…ሌላው ደግሞ በመረጃ አቀባይነት ‘ያውቅበታል’፡፡ “ጌታዬ እኔ ይሄ የአስተዳዳርና ፋይናንስ ሥራ እስኪያጁ አካሄድ ደስ አላለኝም፡፡ አዲስ የቀጠራት ፀሀፊ የአገሩ ልጅ ነች አሉ…” ምናምን አይነት ‘እንደ ሰዉ ማወቅ’ አለላችሁ፡፡
እናላችሁ… ይቺ ሹክ በተባለች ሁለተኛው ሳምንት ገደማ…ወይ የአስተዳዳርና ፋይናንስ ሥራ አስኪያጁ “የተዳከመ የክልል ቢሮ ለማጠናከር…” በሚል  ሁለት ቀን በሊዎንቺና ሰባት ሰዓት በእግር ወደሚያስኬድበት ቢሮ ይዘዋወራል፣ ወይ ደግሞ ሥራ እስኪያጁ ‘ከጤንነት ጋር በተያያዘ’ ከቦታው ይነሳና የአስተዳዳር ሥራ አስኪያጅ ሆዬ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ጉብ ነው፡፡ ልክ ነዋ! ‘የዘንድሮ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው’ ምናምን ተብሎ የለ!
እኔ የምለው…ካነሳነው አይቀር… ይሄ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየማህበሩ፣ በየኮሚቴው ምናምን ‘የአገር ልጅ’ መሰብሰብ… አለ አይደል… ‘በጋራ የምንግባባበት’ ብቸኛው ነገር ሊሆን ነው ማለት ነው! አሀ፣ ያስብላላ!…ሰብሰብ ተብሎ ሻይ በሚጠጣባቸው ስፍራዎች እንኳን በአገር ልጅ መፈላለግ ነገር ታያላችሁ፡፡ (ስሙኝማ…በየቦታው ለሻይ ቡና ስትገቡ የሰዉ ዓይን አልሰለቻችሁም! ከየት የመጣ ልማድ እንደሆነ ግርም አይላችሁም! ድሮ እኮ… “ምን እንትናዬ ላይ ያፈጣሉ!” ምናምን ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ እንትናዬ የለ፣ እንትና የለ… ልክ “የሚገባው ሰው ላይ ሁሉ ማፍጠጥ የቤቱ ግዴታ ነው…” ምናምን የተባለ ይመስል ሁሉ ያፈጥባችኋል፣ እንኳንስ አፍጥጠውብን እንደውም ቅፍፍ፣ ቅፍፍ ስለሚለን… አፍጣጮች ሆይ ስትራቴጂያችሁን ለውጡልንማ! እናላችሁ…አንዳንድ ተቋም ስትሄዱ…ከላይ እስከታች ሠራተኛው ‘የአገር ልጅ’ ነገር ይሆንባችሁና… አለ አይደል… የሆነ የዘመድ ጉባኤ፣ ወይም የአካባቢ ልማት ማህበር የመጣችሁ ይመስላችኋል፡፡ ሀሳብ አለን…የሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ…‘ለተጠቀሱት የሥራ ቦታዎች ማመልከት የሚችሉት የእንትን አካባቢ ተወላጆች ብቻ ናቸው…’ ምናምን የሚል ማሳሰቢያ ይካተትልን፡፡)
ታዲያላችሁ…እኔ እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ይሄ የቺስታ ጓዳ የሚያካክለው የቆዳ ወንበር ሁሉ ‘ከስሩ ተስቦ’ ተቀማጩ ዘጭ ሲል እንጂ… ‘የሳቡት እጆች’ የትኞቹ እንደሆኑ የማይታዩ ይመስለኛል፡፡
 ልጄ… አለ አይደል… ጠዋት እንቁላል ፍርፍሩንና የጀበና ቡናውን ግጥም ካደረገ በኋላ ቢሮው ሲደርስ ‘ታሽጓል’ ተብሎ ኩም!
ታዲያማ…ህዝቤ ደግሞ ገና ወንበር ‘ሲሰጠው’ አብሮ የይዞታ ማረጋገጫ ምናምን ነገር አብሮ የተሰጠው ይመስል ሲንጋለል…‘ምን ጉድ እንደወረደበት’ ሳያውቀው ራሱን መሬት ላይ ሲንከባለል ያገኘዋል፡፡ እናማ…ባለ ትላልቅ ወንበሮች ስሙንማ…የወንበሩ ‘ከስሩ መሳብ’ የጊዜ ጉዳይ ነገር ሆኖ ናፖሊዮን ምናምን ነገር አያድርጋችሁማ! ደግሞላችሁ…እንደ የተጨባጩ ሁኔታ ማወቅ አለ…ልክ ነዋ! ባለፉት ሁለት ‘ዴኬዶች’ (በፈረንጅ አፍ ‘ክብደት’ ይኖረዋል ብዬ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…) ስንትና ስንት ጊዜ ማልያ የለዋወጠ ሞልቶ የለ እንዴ! እናማ… ትናንትና “ኸረ አንድዬ አፈር ድሜ ያስግጣቸው…” ይላቸው የነበሩትን ዛሬ ሁሉ በእጃቸው፣ ሁሉ በደጃቸው ሲሆን… “ዕድሜያቸውን እንደ ማቱሳላ ያርዝመው…” ሲል… ‘እንደ ሰዉ አወቀበት’ ማለት ነው፡፡ ነገርዬውማ…አለ አይደል…
ካንድም ሁለት ሦስቴ ፍቅር ደርሶብኛል
ግን ዛሬ አዲስ ሆኖ ይጫወትብኛል፣
አይነት ነው፡፡ ነገሮች በተለዋወጡ ወይም የተለወዋወጡ በመሰለን ጊዜ ሁሉ ‘ፍቅር እንደ አዲስ’ የሚጫወትብን መአት ነን፡፡
በል ልቤ በርታ ብለህ ይህን ችግር እለፈው
ስለ መጪው አስብ እንጂ አትጨነቅ ስላለፈው፣
ሰው ቢሄድ ሰው ይመጣል ሆዴ በዚህ ተጽናና
እንደ ሰዉ እወቅበት፣ አንተም ወስን ጨክንና፣
ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡ እናማ… ዘንድሮም ነገርዬው “እንደ ሰዉ እወቅበት…” ነው፡፡
 እናላችሁ… አብዛኛውን ጊዜ ‘ከጳጳሱ በላይ ቅዱስ’ የሚሆኑት ‘ኦሪጅናሌዎቹ’ ሳይሆኑ “እንደ ሰዉ እወቅበት…” በሚለው የአቋራጭ መንገድ ሰብረውም ሰርስረውም የገቡት ናቸው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 5560 times