Monday, 20 October 2014 07:49

“በጋምቤላው ግጭት በተሳተፉት ላይ እርምጃ አልተወሰደም” መኢአድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

“አስፈላጊው እርምጃ ተወስዷል፤ ወደፊትም ይወሰዳል” መንግስት
   በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ጎደሬ ወረዳ፣ በዜጎች መፈናቀልና ግድያ ላይ ተሳትፈዋል በተባሉ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ላይ መንግሥት ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱን የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የገለፀ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ ድርጊቱን በፈፀሙት ግለሰቦች ላይ የማጣራት ስራ ተከናውኖ አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱንና ወደፊትም እንደሚወሰድ አስታውቋል፡፡
መኢአድ ሰሞኑን በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ በጋምቤላ ክልል በተከሰተው የዜጎች መፈናቀልና ግጭት ከ540 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ጠቁሞ፤ በድርጊቱ የመንግስት ባለስልጣናት መሳተፋቸው ሁኔታውን በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ያደርገዋል ብሏል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎችን ማፈናቀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም በተደጋጋሚ ሲጠይቅና ሲያሳስብ መቆየቱን ያመለከተው ፓርቲው፤ በመንግስት በኩል ተገቢ እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ እየሰፋ መሄዱን ገልጿል፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀሙትን ካድሬዎች መንግሥት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሲገልፅ እንደነበር ፓርቲው አስታውሶ፤ ነገር ግን የፖለቲካ ፍጆታ ከማድረግ ባለፈ እርምጃ ሲወስድ አለመታየቱንና አሁንም በጋምቤላው ድርጊት በተጠረጠሩት ላይ እርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ባለፈው ሰኞ በክልሉ ቴፒ እና ጎደሬ ወረዳ ባገረሸው ግጭት የ5 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የጠቆሙት ምንጮች በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ ከረቡዕ ጀምሮም አካባቢው በፌደራል የመከላከያ ኃይል አባላት ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየተደረገበት መሆኑን ምንጮች ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዜጎችን ከመኖርያ ቀዬአቸው ማፈናቀልን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በአገሪቱ ያለው ስርአት የግለሰቦችንና የቡድን መብትን በእኩል የሚያከብርና የሚያስከብር መሆኑን ጠቁመው በጋምቤላ በተፈፀመው ማፈናቀል ላይ መንግስታቸው ጉዳዩን መርምሮ ድርጊቱን ፈጽመዋል በተባሉት ላይ እርምጃ መውሰዱንና ለወደፊትም እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡
ከመንግስት በኩልም ሆነ ከተቃዋሚዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ብሔረሰቦችን ለማጋጨት የሚጥሩ እንዳሉ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ድርጊት በሚሳተፉት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ህጋዊ መስመር እንደሚያሲዟቸው፣ ጥላቻን የሚዘሩ ኃይሎችንም ሆነ በጠባብነትና በትምክህት የተለከፉ አካላትን አደብ ለማስገዛትም መንግስት ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

Read 3247 times