Monday, 20 October 2014 07:46

የጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ የቀብር ሥነ-ስርዓት ዛሬ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   በኬንያ በስደት ላይ ሳለ በጥቂት ቀናት ህመም ህይወቱ ያለፈው የጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በትውልድ ሀገሩ ይርጋጨፌ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተለያዩ የግል የህትመት ውጤቶች ላይ ለረጅም አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሰራ የቆየውና “ማራኪ” የተሰኘ መፅሄት አሳታሚ የነበረው ጋዜጠኛ ሚሊዮን፤ ባደረበት ድንገተኛ ህመም ባለፈው ሰኞ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ትላንትና ምሽት አስከሬኑ አዲስ አበባ እንደሚገባና ይርጋጨፌ ወደሚገኙት ቤተሰቦቹ ተልኮ በዛሬው እለት የቀብር ሥነ ስርአቱ ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው ናይሮቢ ኬንያታ ሆስፒታል ለ15 ቀናት በህክምና ሲረዳ መቆየቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ ሃኪሞች ታይፎይድና ከሆድ ውስጥ ደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ህመም አጋጥሞት እንደነበር መግለፃቸውን አመልክተዋል፡፡
የጋዜጠኛው ህይወት ካለፈ በኋላ በገንዘብ እጥረት ለ4 ቀናት በኬንያታ ሆስፒታል የአስክሬን ማቆያ ውስጥ መቀመጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አንተነህ አብርሃም፤ ሟች ሚሊዮን የማህበራቸው ግንባር ቀደም አባል ስለነበር በኃላፊነት ስሜት አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት በተደረገው ጥረት ውስጥ መሳተፋቸውን፤ አስከሬኑን እንድታመጣም የሟችን እህት ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር ሆነው ገንዘብ በማዋጣት ወደ ኬንያ መላካቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አስከሬኑን ለማስመጣት በተደረገው ጥረት የገንዘብ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አንተነህ፤ ለሆስፒታል መከፈል የነበረበትን 1600 ዶላር የምስራቅ አፍሪካ የጋዜጠኞች ህብረት እና አርቲክል 19 ተባብረው መክፈላቸውንና አስፈላጊውን የመጓጓዣ ሰነድ በማስፈፀምም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ ለረጅም አመታት ከቀድሞ “ኢትዮጵ” ጋዜጣ ጀምሮ በተለያዩ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አገር ጥሎ እስከወጣበት ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ”ማራኪ” የተሰኘች በማህበራዊና በኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር መፅሄት ያሳትም እንደነበር ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛው በ2005 ዓ.ም “ወሲባዊ ውስልትና (ዘ አዲስ አበባ)” የተሰኘ መፅሃፍ ፅፎ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡
የ30 አመቱ ጋዜጠኛ ሚሊዮን፤ ከሀገር ከመሰደዱ በፊት ማተሚያ ቤቶች “ማራኪ” መፅሄትን አናትምም እንዳሉትና ገቢ ያገኝበት የነበረ ስራው በመቋረጡ በችግር ላይ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፆ ነበር፡፡     ጋዜጠኛ ሚሊዮን የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡

Read 3600 times