Monday, 20 October 2014 07:39

ሣሙኤል ዘሚካኤል በሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ራሱን “ኢንጅነር ዶክተር ነኝ” እያለ ግለሰቦችን በማታለል አጭበርብሯል በሚል የተከሰሰው ሳሙኤል ዘሚካኤል፤ ሁለቱን ክሶች ራሱ በማመኑ ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን በቀሪው ክስ ላይ ማስረጃ እንዲሰማ ፍ/ቤት አዟል፡፡
ከትናንት በስቲያ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ጉዳዩ የታየው ሳሙኤል ዘሚካኤል፤ ቀደም ሲል ከአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት 58ሺህ ብር አታሎ ወስዷል በሚል የቀረበበትን ክስ ክዶ የተከራከረ ሲሆን ደረቅ ቼክ በማዘዝና ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የማጭበርበር ወንጀል ፈፅሟል በሚል የቀረቡበትን ሁለት ክሶች አምኗል፡፡ ፍ/ቤቱም ጥፋተኛነቱን ባመነባቸው ሁለቱ ክሶች ወዲያውኑ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ክዶ በተከራከረበት ክስ፣ አቃቤ ህግ ማስረጃውን አቅርቦ እንዲያሰማ አዝዟል፡፡ የአቃቤ ህግን ማስረጃ ለመስማትም ፍ/ቤቱ ለጥቅምት 25 ቀጥሯል፡፡
ተከሳሹ፤ የትላልቅ ሰዎችን የህይወት ታሪክ የሚዘክር መፅሃፍ ላሳትም ነው፤ የእርስዎን ድርጅት በመፅሀፉ ላይ አስተዋውቃለሁ በማለት ከአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት 58ሺህ ብር አታሎ ተቀብሏል በሚል የተመሰረተበትን ክስ ነው አልፈፀምኩም ብሎ የተከራከረው፡፡
ድርጊቱን መፈፀሙን በማመኑ ጥፋተኛ ከተባለባቸው ክሶች አንዱ የአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት የሆኑትን አቶ ሰኢድ መሃመድን “ያሰለጠንኳቸውን ተማሪዎች ላስመርቅ ስለሆነ” በሚል 6ሺህ ብር ዋጋ ያላቸውን አራት ሙሉ ልብሶች በዱቤ ከወሰደ በኋላ ለማስተማመኛ ወጋገን ባንክ ቦሌ ቅርንጫፍ የሚከፈል ደረቅ ቼክ ሰጥቷል ተብሎ የቀረበበት ክስ ሲሆን ሌላው ደግሞ ያልታደሰን ንግድ ፍቃድ በሃሰተኛ መንገድ የታደሰ ለማስመሰል ማህተምና ፊርማ በማስቀመጥ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አፍሪካ - ቻይና ጎዳና ቅርንጫፍ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ለማስከፈት በመሞከሩ የቀረበበት በሃሰተኛ ሰነድ የመገልገል ወንጀል ክስ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3181 times Last modified on Monday, 20 October 2014 10:42