Monday, 20 October 2014 07:38

“በግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁት በግፊት መውረድ አልፈልግም” - ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈውራ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ላለፉት 10 ወራት ያገለገሉት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፤ ከተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፊ ሰጪ አመራሮችና የካቢኔ አባላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው እንደለቀቁ ተናገሩ፡፡
ለዳያስፖራዎች ክብር እንዳላቸው የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ የተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፍ ሰጪ አባላት አገር ውስጥ ባለው አመራር ጣልቃ በመግባት ማዘዝ እንደሚፈልጉ ጠቁመው ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ስለሚያደርጉ ብቻ ፓርቲውን የእነሱ ወኪል ለማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
“መውረድ አለብህ ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አልቃወምም፤ ነገር ግን ተቃውሞዋቸውን በተቋማዊ መንገድ ማቅረብ አለባቸው” የሚሉት ኢንጂነር ግዛቸው፤ “እዚህ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርግ፣ እዚያ ቦታ ህዝባዊ ስብሰባ ጥራ እያሉ የሚያዙትን አልቀበልም” ብለዋል፡፡ “የሚሰጡትን ገንዘብ እንደ በጎ አድራጎት ማየት የለባቸውም፤ እንደ ግዴታ መውሰድ አለባቸው፤ እኔ ለእስርም ሆነ ለሞት ቅርብ እንደሆንኩት ሁሉ እነሱም ገንዘብ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው እንጂ በገንዘብ እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር የለባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል - ኢንጂነሩ፡፡
“ግንኙነታቸውም ግለሰባዊ በመሆኑ ይህንን እቃወማለሁ” የሚሉት ኢንጂነሩ፤ እኔን ከስልጣን የማውረድ መብት ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ቢሆንም አተካሮ ውስጥ ገብቼ ፓርቲውን ላለመጉዳት ስል በገዛ ፈቃዴ መልቀቁን መርጫለሁ ብለዋል፡፡ አክለውም “አንዷለም አራጌ ታስሮ አንተ እቤት ቁጭ የማለት ሞራል አለህ ወይ? በሚል ግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁ በግፊት መውረድ አልፈልግም” ብለዋል፡፡
ከተወሰኑ የካቢኔ አባላት ጋር ያለመግባባት የተፈጠረው ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ በተደረገው ሙከራ መሆኑንም ኢ/ር ግዛቸው ገልፀዋል፡፡ ውህደቱ መኢአድ ውስጥ ባለ ችግር ምክንያት ሊሳካ አልቻለም ብለዋል፡፡
ለውጥ በህዝባዊ አመፅም ሆነ በትጥቅ ትግል ይመጣል ብለው እንደማያምኑ የገለፁት ኢንጅነሩ፤ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደርም ሆነ ላለመወዳደር ገና እንዳልወሰኑ ተናግረዋል፡፡

Read 2479 times