Monday, 13 October 2014 08:06

የጨርቃጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ 435 ሚ. ዶላር ለማግኘት አቅዷል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ያለፈው ዓመት ገቢ ከዕቅድ በታች ነው

           በኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የጨርቃጨርቅ ስፌት ኢንዱስትሪ በዘንድሮ  በጀት ዓመት ከተለያዩ የምርት ዓይነቶች የውጪ ንግድ 435 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ያለፈው ዓመት ገቢው ከዕቅድ በታች መሆኑንም ገልጿል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የዚህን ዓመት ዕቅድ ለባለድርሻ አካላት ባስተዋወቀበትና ያለፈውን ዓመት ዕቅድ በገመገመበት ወቅት፣ ይህ ዓመት፣ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ምዕራፍ የሚጠናቀቅበት ስለሆነ፣ ዕቅዱን ለማሳካት የሞት ሽረት ጥረት ይደረጋል ብሏል፡፡ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በዚህ ዓመት በጨርቃጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በግንባታ ላይ (18 አዳዲስና 7 በማስፋፊያ) የሚገኙት 25 ፕሮጀክቶች ወደ ምርት ይገባሉ ያለው ኢንስቲትዩቱ፤ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ጥጥ ልማት እንዲገቡ በማድረግ፣ የጥጥ ልማትና በዘርፉ የሚደረግ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የፋብሪካዎችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ የቴክኒክና የምክር አገልግሎት መስጠት፣ የገበያ ትስስር መፍጠርና የግብይት አቅምን ማጠናከር፣ … ዕቅዱን ለማሳካት የሚደረጉ ሌሎች ጥረቶች መሆናቸውን አብራርቷል፡፡ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮም 7 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም  ከ70 ሺህ በላይ የተደመጠ ጥጥ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለ10 ባለሀብቶችም ብድር ተፈቅዶ ወደ ጥጥ ልማት መግባታቸው ተገልጿል፡፡ የአምናው ክንውን ሁሉም ከዕቅድ በታች ከመሆኑን በላይ፣ አንዳንዱ ከ2005 ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው፡፡ ድርና ማግ (ክር) 77,147 ታቅዶ በክንውኑ የተገኘው 28,147 ነው፡፡ ብትን ጨርቅ 35,544 ታቅዶ 6,321፣ የስፌት ውጤቶች 230ሺ ታቅዶ፣ 72,148፣ የሽመና ውጤቶች 7,078 ታቅዶ፣ ክንውኑ 4,738 ሆኗል፡፡ ከካቻምናው 2005 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀሩ፣ ብትን ጨርቅ 9,399 የነበረው አምና ወደ (6,32) ወርዷል፣ 4,916 የነበረው የሽመና ውጤቶች ወደ 4,738 ዝቅ ብሏል፡፡በአጠቃላይ ከወጪ ንግድ 350 ሺህ ዶላር ለማግኘት አቅዶ የተገኘው ግን 111.4 ሺህ ዶላር ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ፣ ከኤክስፖርተር ኩባንያዎች ጋር ባደረገው ውይይት፣ ባለሀብቶቹ የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተው የመፍትሄ ሀሳብ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ዋንኛ ችግር ከፍተኛ ሰው ኃይል በመሆኑ መፍትሔ ካልተፈለገለት ዘርፉን እንደሚያሽመደምደው ተገልጿል፡፡ ሰራተኞች፣ በትንሽ የደሞዝ ለውጥ ከአንዱ ድርጅት ለቀው ወደ ሌላ እንደሚገቡ፣ አንዳንድ የውጭ አማካሪዎች ሰራተኞችን እንደሚያስኮበልሉ፣ … ተገልጿል፡፡ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት ሌላው ችግር ነው፡፡ ባንክ ደግሞ በቀላሉ ብድር አይሰጥም፡፡ የአራት ዓመት የኮንትራት ስምምነት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የትራንስፎርሜሽኑንም ዕቅድ እንዳይሳካ ያደርጋል ተብሎ የተሰጋው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋትና መቆራረጥ ነው፡፡ ስለዚህ በሙሉ አቅማቸው እንደማያመርቱ ገልፀዋል፡፡ አንድ 10.5 ሺህ ሜጋ ዋት የሚያስፈልገው ፋብሪካ የሚያገኘው የኃይል መጠን 4ሺህ ሜጋ ዋት ነው፡፡ የኤክስፖርት ምርቱ ተሞክሮ በማያውቅ ሁኔታ በስዊድን ተቀባይነት አግኝቶ ኮንትራት ቢፈራረምም በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋትና መቆራረጥ ኃላፊነትና ግዴታውን መወጣት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ የጥሬ ዕቃ (ጥጥ) የክር እጥረት፣ የመንገድ ያለመስፋፋት፣ የባለስልጣኖችና ኃላፊዎች ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት፣ … በኤክስፖርተሮቹ ከተነሱት ችግሮች ጥቂቱ ናቸው፡፡

Read 2106 times