Print this page
Saturday, 11 October 2014 14:09

ሰሜን ኮሪያ የሞባይል አጠቃቀም ስነ-ምግባር መመሪያ አወጣች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

           የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በሚገኝባት ሰሜን ኮሪያ፣ በተጠቃሚዎች ላይ የሚታየውን የስነ-ምግባር ጉድለት ለመቅረፍ ሲባል አዲስ የአጠቃቀም መመሪያ መውጣቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ ዮንሃፕ የተባለውን የሰሜን ኮሪያ የዜና ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የሞባይል ተጠቃሚዎች ላይ ከሚታዩ የስነ-ምግባር ጉድለቶች መካከል፣ ሰው በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ጮክ ብሎ ማውራትና መጨቃጨቅ ይገኙባቸዋል፡፡ አዲሱ የአገሪቱ የሞባይል አጠቃቀም የስነ-ምግባር መመሪያ እንደሚለው፣ ተጠቃሚዎች ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው በትህትና መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ በሞባይል ስልክ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጭቅጭቆችን ለማስወገድ ሲባልም፣ የተደወለላቸው ሰዎች ጥሪያቸውን ሲመልሱ፣ ለደዋያቸው ማንነታቸውን ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የደዋያቸውን ማንነት እንዳወቁ መግለጽም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ደዋዩ ራሱን ለማስተዋወቅ ጊዜ እንዳይፈጅ ያግዘዋል ተብሏል፡፡እ.ኤ.አ በ2008 የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ በሆነችው ሰሜን ኮሪያ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ አለማቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ ክልክል ነው፡፡ የሞባይል ስልክ ባለቤት መሆን የሚችሉትም፣ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ (ባለፈው ሳምንት ለንባብ ባበቃነው በዚህ ዜና ላይ፣ ‘ደቡብ ኮርያ’ ተብሎ የቀረበው በስህተት በመሆኑ ከይቅርታ ጋር ዜናውን አስተካክለን አቅርበናል)

Read 2923 times
Administrator

Latest from Administrator