Saturday, 11 October 2014 12:50

መንግሥት “ይቅርታ” የጠየቀው ለእስከዛሬው ነው ወይስ ለወደፊቱ?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(5 votes)

የይቅርታ እዳችንን እንተሳሰብ እንዴ?

ትእግስት ኖሮን እድል መስጠት ከቻልን የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ ይኸው “አውራው ፓርቲ” ኢህአዴግ እንኳን ብዙዎች “አይለወጥም፤ ግትር ነው” እያሉ ሲያሙት ከርመው ድንገት ተለወጠና ኩም አደረጋቸው፡፡ እናንተ እኮ ቀልድ አታውቁም… ተለወጠ ስላችሁ… በርእዮተ ዓለም ምናምን መስሏችሁ አገር ልትቀውጡ ትችላላችሁ! ቆይ ግን “ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ” ወጥቶ ምን እንዲሆንላችሁ ነው የምትፈልጉት? (ኒዮሊበራል… እንዳትሉኝና እንዳንኮራረፍ!) ግን እኮ… ስምን መላዕክ ያወጣዋል የሚባለው ልክ ነው፡፡ ኢህአዴግ እኮ ሁለቱንም ነው - አብዮተኛም “ዲሞክራትም!” እናላችሁ… ኢህአዴግ ሥልጣን ከጨበጠ ከ20 ምናምን ዓመት በኋላ መጠነኛ የለውጥ ባህርይ በማምጣት ሰርፕራይዝ ያደርገን ጀምሯል፡፡ ለራሱ መለወጥ ብቻ ቢሆን ደሞ እምብዛም አይደንቅም ነበር፤ ኢህአዴግ ግን ራሱ ተለውጦ የእኛንም ባህል ሊለውጥ እየታተረ ነው፡፡ ትዝ ይላችኋል… የመዲናዋ ከንቲባ የትራንስፖርት ችግሩን በተመለከተ በፅናታችን ተደምመው ይቅርታ ሲጠይቁን! እኔ እኮ… በግላቸው እንጂ በፓርቲያቸው አልመሰለኝም ነበር፡፡

እናላችሁ… “Sorry” እና “Thank you” አያውቅም እየተባለ ለሚታማው ባህላችን፤ በተለይ ይቅርታ መጠየቅን (Sorry) እያለማመደልን ነው፡፡ ይሄን ደሞ ከወዴት አመጣኸው ብላችሁ ቱግ ለምትሉብኝ አንባቢያን፤ ቀስ ብዬ አስረዳለሁ እንጂ እኔው መልሼ ቱግ ልልባችሁ አይዳዳኝም፡፡ (ቱግ መባባል እኮ ነው ነገር ያበላሸው!) ለነገሩ ልብ ሳትሉ ቀርታችሁ እንጂ ኢህአዴግ “ይቅርታ” የማለት ባህልን በደንብ እያስለመደን እኮ ነው (ለነገሩ እሱም የ20 ዓመት የይቅርታ እዳ ከእነወለዱ አለበት!) የከንቲባው ሲገርመኝ ፕሬዚዳንቱም ሰሞኑን ይቅርታ ጠየቁን ተባለ (በይቅርታ ተንበሸበሽን እኮ!)፡፡ ባለፈው ሰኞ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ሲጀመር፣ የአገሪቱ ርእሰ ብሄር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ለማጠናከር የኢንቨስትመንትና የሥራ ማስኬጃ ፋይናንስና የማይዋዥቅ የኃይል አቅርቦት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ ሲሆን በኃይል አቅርቦት ረገድ ባለሃብቶችና የኢትዮጵያ ህዝብ መስተጓጐል እንደደረሰባቸው (መስተጓጐል ብቻ?!) በመግለፅ፤ “ለተፈጠረው መስተጓጐል በታላቅ አክብሮት ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል - መንግሥታቸውን በመወከል፡፡ አያችሁ… ይሄንን እኮ ነው ያልኳችሁ፡፡ እስቲ ሃቁን እንነጋገር… ኢህአዴግ በሉት በእሱ የሚመራው መንግሥት መቼ ነው እንዲህ በአደባባይ… እንዲህ በይፋ… እንዲህ በፓርላማ… በአክብሮት ይቅርታ ጠይቆን የሚያውቀው? (ከአገር ወጥቼ እኮ አላውቅም!) ይሄንን ነው እኮ የምላችሁ! እድል ከተሰጠው የማይለወጥ ነገር የለም… ማለት ይሄው ነው፡፡ እርግጥ ነው በይቅርታው ዙሪያም ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ እኔም ራሴ አንድ ሁለት ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ ከዚያ በፊት ግን እስቲ የመንግሥት “ይቅርታ” መጠየቅ ለአገርና ባህል ያለውን አዎንታዊ ተፅዕኖ እናጉላው፤ እናድምቀው፤ እናፍካው፡፡

አያችሁ… የአገሪቱ ትልቁ የሥልጣን ባለቤት፣ መንግሥት ለጥፋቱ እንዲህ እየደጋገመ ይቅርታ ሲጠይቅ፤ ተቃዋሚዎችም፣ ህዝቡም፣ ማህበረሰቡም፣ ቤተሰብም፣ ግለሰቦችም… ምንም ሳይመስላቸው ለጥፋታቸው ይቅርታ መጠየቅ ይጀምራሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ መሰረት ይይዝና ባህላችን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሄ ታዲያ ግሩም እሴት አይደለም? (በጣም ሸጋ እንጂ!) በግርግር አንድ በጐ እሴት አጐለበትን ማለት ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆነውን (ለይቅርታው ማለቴ ነው!) የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን እንዳትዘነጉብኝ አደራ እላችኋለሁ፡፡ እሱን ከረሳነው ውለታ ቢስ መሆን ነው፡፡ ከምሬ እኮ ነው… ይሄ ተቋም ባለው አቅም ተታትሮ ላለፉት ጥቂት ዓመታት አንዴ ትራንስፎርመር ተቃጠለ እያለ፣ አንዴ ምን እያለ… ኃይል ባያስተጓጉል ኖሮ እኮ መንግሥትም ሆነ ኢህአዴግ ይቅርታ ለመጠየቅ አይዳዳቸውም ነበር፡፡ (የሃይል አቅርቦት ካለ የይቅርታ አቅርቦት አያስፈልግማ!) እናላችሁ… የኢህአዴግ “ይቅርታ” ትዝ ባላችሁ ቁጥር መብራት ሃይል ይታወሳችሁ፡፡ ኤልፓ ባይኖር የ“ይቅርታ” ወግ አይደርሰንም ነበር፡፡ (ዕድሜ ለአልፓ!) ኢህአዴግና መንግሥት ሳይወዱ በግድ (እጅ መጠምዘዝ በሉት!) ለይቅርታ እጅ እንዲሰጡ ያደረጋቸው እሱ ነው - ኤልፓችን! አንዴ… “የስርጭት እንጂ የሃይል አቅርቦት ችግር የለብንም”… ሌላ ጊዜ “የኪራይ ሰብሳቢዎች ሴራ ነው”…. ቀጥሎ “የህዝብ ቁጥር ጨምሯል” እያለ ሲያዘናጋ ቆየና ድንገት ሰበቦች አለቁበት፡፡

ሆኖም እጅ አልሰጠም፡፡ ኤልፓ ነፍሴ አይበገሬ ነው! ብርሃን ሊሰጠን ምሎ ተገዝቶ የተቋቋመው ኤልፓ፤ ዋና ስራው ብርሃን መንፈግ፣ በጨለማ ማዳፈን ሆነና አረፈው (ያልተቋቋመበትን እኮ ነው የሚሰራው!) በእዚህ ሁሉ መሃል መከራችንን የበላነው፣ አሳራችንን ያየነው… እኛ ነን - ድምፅ ሰጪዎቹ ምእመን!! ግን ፈረንጆቹ A blessing in disguise እንደሚሉት ሆነና በጨለማ ተዳፍነን ከርመን “በይቅርታ ብርሃን” ነፃ ወጣን፡፡ በኤሌክትሪክ ብርሃን ፋንታ “የይቅርታ ብርሃን” ተጐናፀፍን!! (አሁንም እድሜ ለኤልፓ!) በእርግጥ ይሄ “የይቅርታ ብርሃን” የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የጠቀሷቸውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚያንቀሳቅስ አይደለም፡፡ (እንኳንስ ለኢንዱስትሪ ለባለ ዜሮ ሻማ አምፑልም ብርሃን አያመነጭም!) እንግዲህ ምን ይደረግ… ይቅርታና ኤሌክትሪክ ለየቅል ናቸው፡፡ (አንዱ መንፈሳዊ፣ ሌላኛው ቁሳዊ! አንዱ ታንጅብል፣ ሌላኛው ኢንታጀብል!) እናላችሁ… መብራት አጥተን… ቢዝነሳችን ለኪሳራ ተዳርጐ… ኑሮአችን ተቃውሶ… በሻማ ተጨናብሰን… ከፕሮግራም ውጭ ሆነን… ከህልቆ መሳፍርት እንግልትና ስቃይ በኋላ አጨብጭበን አልቀረንም፡፡ ብቸኛ መፅናኛችን ምን መሰላችሁ? በ”ይቅርታ ብርሃን” መካሳችን ነው፡፡ ይቅርታ መጠየቃችን እኮ ሻማ አይገዛልንም፡፡ ለኪሳችንም አንዲት ድንቡሎም አይጨምርልንም፤ ግን ነፍሳችን በሃሴት ጮቤ ትረግጣለች፡፡ በይቅርታ ፀዳል ትደምቃለች፡፡ በነገራችሁ ላይ መብራትና ይቅርታ ሰምን ወርቅ ይመስሉኛል፡፡ (መሰሉኛ በቃ!) አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ምን መሰላችሁ? ለይቅርታው ዋና ሰበብ ኤልፓ ቢሆንም፣ ይቅርታውን የጠየቀው ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ቢሆንም አምጠን የወለድነው ግን እኛ ነን - በቻይነታችን፣ በፅናታችን፣ በጨዋነታችን!! ከጨለማ ውስጥ ብርሃን አምጦ መውለድ ይሏል ይሄ ነው፡፡ (በጨለማ ውስጥ እያደርን ብርሃን ወለድን!!) የ”ይቅርታ ብርሃን” የኤሌክትሪክ ብርሃንን ፈፅሞ ሊተካው እንደማይችል ለእናንተ ሳይሆን ለመንግሥት ላስታውሰው እወዳለሁ፡፡ (መንግሥት እኮ አንዳንዴ የዋህ ነው!) በእርግጥ ”ይቅርታው” እንደ ህመም ማስታገሻ… እንደ ማደንዘዣ…. እንደ ፔይን ኪለር… እንደ ጊዜ መግዣ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ሁነኛ ሃኪም ጋ እስክንደርስ ማለት ነው፡፡

ህመም ማስታገሻዋን እንደ ዋነኛ ፈውስ (መድሃኒት) ቆጥረናት እንዳንዘነጋ ነው ፍርሃቴ! ለምን መሰላችሁ? እኛ ጋ መዘናጋት በሽ ነዋ፡፡ እንግዲህ እስካሁን ድረስ የመብራት ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ ከሻማ ዘመን መቼ እንደምንወጣ አፉን ሞልቶ ለመናገር የደፈረ አንድም የመንግሥት ባለስልጣን አልገጠመኝም፡፡ ስለዚህ ፔይን ኪለሯ እንደዘላቂ ፈውስ ልትቆጠር የምትችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ እናም… የፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ “የተከበረ ይቅርታ” ለእስካሁኑ የሃይል መስተጓጐል ነው ወይስ የወደፊቱንም ይጨምራል? (ግልፅ አይደለማ!) ለመሆኑ ይቅርታው የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ (expiry date እንደማለት) አለው ወይስ ጊዜ አያልፍበትም? እኔ የምላችሁ ግን… ወደፊት ለምበድልህ ተብሎ ይቅርታ ይጠየቃል እንዴ? (የ21ኛው ክ/ዘመን ይቅርታ እኮ መላው አይታወቅም!) በይቅርታው ዙሪያ ጥያቄዎችን ማንሳቴ ካልቀረ በአእምሮዬ የሚመላለሱትንና ሰዎች ሲያነሷቸው የሰማኋቸውን ሃሳቦች ይፋ ባደርጋቸው ሸክሜ ቀለል እንደሚልልኝ አሰብኩ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ጥያቄ (ቅሬታ ቢባል ይሻላል!) ምን መሰላችሁ? እንግልታችንና ይቅርታው አይመጣጠንም የሚል ነው፡፡ እንዴት የሚለውን ከሰማሁት እያጣቀስኩ ላብራራ፡፡ ላለፉት ዓመታት እየተንገላታን ያለው በሃይል መስተጓጐል ብቻ ሳይሆን በኢንተርኔትና ኔትዎርክ መቋረጥና መጓተት፣ በትራንስፖርት እጥረት ሰልፍና ግፊያ፣ በውሃ መጥፋት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት… ጭምር መሆኑ እየታወቀ ይቅርታው ግን የኃይል መስተጓጐሉ ላይ ለምን አነጣጠረ ይላሉ - ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡ አይገርማችሁም… ችግሮቹን በጣም ከመላመዳችን የተነሳ፣ እነሱን ትተን ይቅርታው ተመጣጣኝ አይደለም ወደሚል ቅሬታ እየገባን ነው፡፡

እኔ ምን እንደፈራሁ ታውቃላችሁ? ይቅርታሁ ተመጣጣኝ አይደለም የሚለው ቅሬታ ቀስ እያለ “ይቅርታው ተጭበርብሯል” ወደሚል እንዳያመራ ነው፡፡ (ይቅርታ ደሞ እንደ ምርጫ አይደገምም…) ምን ትዝ እንዳለኝ ልንገራችሁ? የኢህአዴግ እዳዎች! ብዙ የይቅርታ እዳዎች እኮ አሉበት፡፡ አሁን አንዴ ዓይኑ ተገልጧልና እዳውን ቢከፍለን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ሂሳብ መተሳሰብ ሳያስፈልገን ያመነበትን ብቻ ይቅርታ ይበለን!! (ያለወለድ እኮ ነው!) እኛም ያስቀየምነው ነገር ካለ ይቅርታ እንጠይቀዋለን (የ97 ምርጫ ለምን ትዝ አለኝ?!)

Read 3168 times