Print this page
Saturday, 11 October 2014 12:54

“አጠገብ ያለ ጠበል…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

           አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን ስሙኝማ…በአንድ የተክሊል ሠርግ ላይ ነው አሉ፡፡ ስነ ስርአቱ ከተገባደደ በኋላ የኃይማኖት አባቱ ሲያጠቃልሉ ቅርባችን ላለው ነገር ትኩረት መስጠት እንዳለብን ይናገሩና ምን አባባል ተጠቀሙ መሰላችሁ… “አጠገብ ያለ ጠበል የልብስ ማጠቢያ ይሆናል፡፡” አሪፍ አይደል! መቼም ለራሳችን ለሆነ ነገር ዋጋ ባለመስጠት እኛን የሚስተካካሉ አገሮች ይኖሩ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡ የአገሪቱ ልብስ መሸጫና ምግብ ቤት ሁሉ በውጪ ከተሞች ስም የሚሰየመው… አለ አይደል… “አጠገብ ያለ ጠበል…” ነገር እየሆነ ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ ለሆነ ነገር የአገርኛ መፍትሄ ይኖር አይኖር እንደሆነ በቅጡ ሳይጠና “ከእንትና አገር ተሞክሮ የወሰድነው…” ምናምን የሚባለው… “አጠገብ ያለ ጠበል…” ነገር ስለሆነ ነው፡፡ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እዚህ አገር በየመሥሪያ ቤቱ የ‘ፈረንጅ’ና፣ ‘ፈረንጅ ቀመስ’ ሰዎች መብዛት “አጠገብ ያለ ጠበል…” ነገር ይመስለኛል፡፡

የምር ግን…ዘንድሮ እኮ የራስ የሆነችው አሪፍ እንትናዬ እያለች የዚያኛው እንትናዬ ላይ ጆፌ መጣል የተለመደ ሆኗል፡፡ የራሱ ምን የመሰለች ሚስት ከቤት አስቀምጦ የሥራ ባልደረባውን ሚስት ላይ ‘ጥቁር ዶሮ’ ለማዞር የሚሞክር መአት ነው፡፡ (እኔ የምለው…ለምንድው ሰዉ ሁሉ ‘መነጣጠቅ’ ደስ የሚለው! ግራ ስለገባን ነው! ቅቤ ውስጥ ነክረው ያወጧቸው የሚመስሉት እነእንትና፣ ኩንታል የሹሮ ዱቄት ውስጥ አንከባለው ያወጡን የምንመስለው እነእንትና…ሁላችንም ነገራችን ሁሉ… አለ አይደል… “ከአንተ ተኝታ ሌላ ካማራት…” አይነት ሲሆን የምር ያሳስባል፡፡) በዚያ ሰሞን አንድ ወዳጃችን እንትንዬው ዘንድ ሲደውል የሆነ ሰፈር ዘመድ ቤት እንደሆነች ትነግረዋለች፡፡ ግንላችሁ… የእሱ ወዳጅ የሆነ ሌላ ሰው ደግሞ በዚያው ሰዓት የሆነ ‘ዘወር ተብሎ የሚገባበት’ ቦታ ጥግ ይዛ ከእንትናዬው የልብ ጓደኛ ጋር ያያታል፡፡ አላስችል ይለውና ለጓደኛው ደውሎ እንትንዬው ያለችበትን ቦታ ይነግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ምን አለፋችሁ…አገር ተቀወጠ፡፡

ደግሞላችሁ…በተለይ በእኛ ቀደም ያሉ መጽሐፍት ውስጥ ስንትና ስንት የሚጠቀሱ ነገሮች እያሉ እንኳን የሁል ጊዜ ጥቅሳችን…“በአንድ ወቅት ሼክስፒር እንዳለው…” “ይህን ነገር በአንድ ወቅት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ሲናገሩ…” ምናምን ነው ነገሩ፡፡ “አጠገብ ያለ ጠበልን…” የልብስ ማጠቢያ ማድረግ ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሰዉ ሁሉ ቀኑን ሙሉ የአሥራ ምናምን ብር ሻይና ማኪያቶ እንደ ልቡ እየደጋገመ ሲጠጣ የሚውለው ነገርዬው እንዴት ነው! የአሥር ብር ሻይ በቀን ሁለቴ መጠጣት ማለት እኮ በወር ስድስት መቶ ብር ነው! ስድስት መቶ ብር እኮ አምስት ሰው ያለበት ቤተሰብ የወር ቀለብ ነበር፡፡ የምር ግን የዚች የብር አቅም እንዲህ ይድከም! እኔ የምለው…እንግዲህ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ይባል የለ…ከዕለታት አንድ ቀን ሽልንግ ትሸጥ ነበር የምትባለው ክትፎ ብዙ መቶ ስድሳ ብር ደረሰች አሉ፡፡

መቶ ስድሳ ብር! ልጄ…መቶ ስድሳ ብር እኮ ምን የመሰለ ሙሉ ልብስ የሚሰፋበት ነበር፡፡ እናላችሁ…ኮሚክ ነገር ነው፡፡ የመቶ ስድሳ ብር ታሪክ ይታወስልንማ! ለምሳሌ ምሳውን ክትፎ በልቶ የመጣ ሰው ምን እንደተመገበ ሲጠየቅ “ክትፎ…” የሚለውን ይለውጥልንማ! ሌላ ‘ምስል ከሳች’ (ቂ…ቂ…ቂ…) አባባል ይኖራላ! “ምሳ ምን በላህ?” “ሙሉ ልብስ፡፡” ልክ ነዋ! እናላችሁ… አንድ ሺህ ብር ማግኘት እንደ ጉድ የሚወራበት ዘመን ነበር፡፡ “የወ/ሮ እከሊት ልጅ ስንት ደሞዝ እንደሚበላ ሰምተሻል! “ኧረ እኔ’ቴ!!” “ሺህ ብር! በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ…ምንድነው ያልሽኝ?” “በየወሩ ሺህ ብር ይዝቃል! ጆሮሽ አይሰማም እንዴ!” “እንደው እኔ የምለው… በዚያ ሁሉ ብር ምን ይገዛበታል?” ምናምን የሚባልበት ዘመን ነበር፡፡ እናላችሁ…ሺህ ብር ማግኘት ዘንድሮ “የሆነች ሺህ ብር እየቆነጠሩ ይሰጡታል መሰለኝ…” እያልን ልናሾፍባት በጊዜዋ ‘የምትዛቅ’ ነበረች፡፡ ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ለምሳሌ ሺህ ብር የሚበላው ሰው መሥሪያ ቤቱ ‘የጥሬ ብር እጥረት’ ገጥሞት “የዚሀ ወር ደሞዝ በአይነት ይሰጥ ቢባል…” ቤቱ ምን ይዞ ቢገባ ጥሩ ነው…ግማሽ ኪሎ ጤፍ! ሚስት ሆዬ እልልታዋን ታቀልጥና ምንድነው ስትል….. “የወር ደሞዜ ነው…” “ጤፉ?” “አዎ ጥሬ ብር ስለሌለ በአይነት ይሰጥ ተብሎ ግማሽ ኩንታል ጤፍ ሰጡኝ፡፡

” ሚስት ሆዬ የደላቸው ሰንጋ በሬ እያስጎተቱ ይመጣሉ፤ አጅሬ ዱቄት አምጥተህ ታቦንብኛለህ!” እንዲህ ነዋ! የሺህ ብር ‘ዝና’ ከወረደ ቆይቷላ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሚሊዮን ብር ምናምን የምትባለው ነገር ብዙዎች ዘንድ ተለመደችሳ! ልጄ… እኛ እንኳንስ ሚሊዮን ብር ልንቆጥር 1,000,000 የሚል ቁጥር የተጻፈበት ወረቀት እንኳን ኪሳችን የሚገኘው ከስንት አንዴ ነው!እናላችሁ…የብር አቅም ነገር የምር ያሳስባል፡፡ አሀ…በፊት እኮ ለእንትናዬ አሥራ አምስት ብር ከሰጠን ጸጉሯን፣ ተሠርታ፣ መደገም ትችል ነበር፡፡ “ለምን አይመርባት! ምን ታድርግ፣ ሰውዬዋ እንደሁ ገንዘቡን ከጓሮ ከዛፍ ላይ የሚሸመጥጠው ነው የሚመስለው፣” ተብላ የሚቀናባት ትሆናለች፡፡ እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ከስንት መቶ ዓመት በፊት የነበረው፣ የእኛ ነን ብለን ‘የምንጣላበት’ ፑሽኪን አደባባይ አለው፣ ቻርለስ ደጎል አደባባይ አላቸው፣ ቸርችል ምን የሚያክል ጎዳና አላቸው (ምን አለፋችሁ…እንግሊዞቹ መንገዱንም ት/ቤቱንም ይዘውታል)፣ እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ‘አደባባይ’ ነገር አለው…እናላችሁ ስንትና ስንት የእኛ የሆኑ አደባባይ፣ መንገድ ምናምን ሊሰየምላቸው የሚገቡ የሉም? ሞልተው! ግን…አለ አይደል… ነገርዬው “አጠገብ ያለ ጠበል…” ነገር ስለሆነ ነው፡፡

እናማ…በዚህ ዘመን እንኳን በየአገሮቹ የምንሰማቸው ‘መጤዎች’ ላይ የመዝመት ነገር እየተባባሰ ባለበት፣ ያልሆነውን እንሁን ብንል እንኳን ኦፊሴላዊ እውቅና የሚሰጠን በሌለበት ዘመን…ለምን ወደ ራሳችን እሴቶች እንደማንመለስ፣ ለምን የራሳችን የሆኑትን ማክበር እንዳቃተን ግርም ይላል፡፡ የራሳችን ለሆኑት ነገሮች ክብር እንድንሰጥ ልቦናችንን ክፍት ያድርግልንማ! እናላችሁ….‘አጠገባችን ያለ ጠበልን’ ያለማየት ወይም ለማየት ፈቃደኛ አለመሆን ብዙ ሥራ የሠሩ ወገኖቻችን ስማቸው ጭርሱን እንዲረሳ እያደረጋቸው ነው፡፡ፍቅር ከዚህ ቀደም ብዙ አንገላቶኛል ዛሬም እኔው ላይ ነው ምንድን ይሻለኛል፣ ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡ እናም የውጪ ነገር የማምለክ ፍቅር አልለቅ ብሎ ተጣብቆብናል፡፡ “…ምንድን ይሻለኛል…” ብለን የምናንጎራጉርበት ጊዜ እንኳን ልናጣ ነው፡፡ “አጠገብ ያለ ጠበል…” መለየት ካልቻልን ትንሽ ቆይቶ ራሳችንን መለየት አቅቶን የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳንገባ አንድዬ ይጠብቀንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3189 times