Saturday, 11 October 2014 13:04

የጉራጌ አገር የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(7 votes)

ዘሙቴ ማሪያም


ለመሆኑ ስለጉራጌ የምናውቀው ዋና ዋና ነገር ምንድን ነው?
ፍቅር?
ሥራ?
ዕምነት?
ገንዘብ? ለእነዚህ መልስ መፈለግ የዛሬ ጉዞዬ ስንቅ ነው፡፡
ዛሬም መጓዝ ማወቅ ነው!
ገጣሚ ከአገር አገር ካልዞረ አገር ያለው ይመስለዋል፡፡ ከአገር አገር ከዞረና ባየው ካልተገረመ፣ እንዲሁም ብዕሩን
ካላነቃ፤ አገር የሌለው ይመስለዋል፡፡ ከአገር አገር ዞሮ ያየውን በልቡናው ጽፎ ከተደሰተ ራሱ አገር ሆነ፤ ብዬ
አምናለሁ፡፡
ሁሌ ስጓዝ ፖል ቴሩ (Paul Theroux) የተባለ አሜሪካዊ የጉዞ ፀሐፊ! (ተጓዥ ፀሐፊ) (Travel writer) ትዝ
ይለኛል፡፡ “ካስፃፈኝ የጉዞ ትንሽ የለውም” ይላል ፖል፡፡ እኛ “የድግስ ትንሽ የለውም” ብለን ነው የምናስበው፡፡
እርግጥ ጉዞው እንደድግስ ከታየ የጉዞ ትንሽ የለውም ማለትም ያስኬዳል፡፡ ፖል አንድ ዓመት ሙሉ ከአንድ
የዓለም ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ጫካ ጫካውን፤ ቆላ ቆላውን፣ ውሃ ውሃውን ይጓዝና፤ በዓመቱ መጨረሻ ቤቱ
ገብቶ በሩን ከርችሞ ሊፅፍ ይቀመጣል፡፡ ከቤቱ ብቅ ሲል አንድ ደጓሣ መጽሐፍ ይዞልን ከተፍ ይላል፡፡ በዚህ
ዓይነት እኔ ሳውቀው 13ኛ መፅሐፉን ለመፃፍ እየተጓዘ የነበረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመጣ ጊዜ በአሜሪካን ኤምባሲ
ጋባዥነት ለምሳ ተገናኝተን ተጨዋውተን ነበር፡፡ ከዛ መፅሐፉን ጽፎ ከች አለ፡፡ ላከልኝ፡፡ በመጽሀፉ ውስጥ
ከእኔም ጋር የተገናኘንበትን ቅፅበት ከትቦታል፡፡ ልብወለድም፣ የጉዞ መጽሐፍም፣ ወደፊልም የተቀየሩ
መጽሐፍትም (ለምሳሌ saint jack፣ the mosquito coast ወዘተ) አሉት፡፡ የፖል የፅሁፍ ጥበብ ምን
መሰላችሁ? ለምሳሌ ወደ አፍሪካ ሲመጣ ምክኑን እንዲህ ይገልፀዋል፡-
“… ከችጋርና ከሽብር ባሻገር አፍሪካ የተነገሩ ተረቶች፣ የተወሰነ ተስፋ፣ ኮሜዲና ጣፋጭነት የያዘች ሰፊ አህጉር
ናት፡፡ ያችን ዕምብርት የሆነች የላንቲካ ዕምቅ - አገር አይቼ፤ ጎብኝቼ፤ እንድትሰማኝ እፈልጋለሁ”
“… እያንዳንዱ ጉዞ ራስን በራስ የመጠበቅ ትምህርት ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ዓለም በአፍጢሙ ተደፍቷል ብለው
የከፋቸው ሰዎች ቢነግሩኝ እንኳን…
… አፍሪካ ይብስ ተራበች፣ ይብስ ደኸየች፣ ይብስ መኸየመች፣ ይብስ ተስፋ ቆረጠች፣ ይብስ ሞሰነች፣ ደሞም
ፖለቲከኛውን ከጠንቋዩ ለመለየት የማይቻልበት ደረጃ ደረሰች ቢሉኝም እንኳን …
… መሪው ሌባ፣ ወንጌላዊው የአገሬውን የዋህነት ዘራፊ፣ የዕርዳታ ድራጅቱ ራሱን ጠቃሚና የሀሰት ተስፋ ሰጪ፤
ነው ቢሉኝም ቅሉ …
ዋናው አለመሰልቸቴ፣ አለመታከቴ፣ ጥሩ ነገር ለማየት ተስፋ ማድረጌ ነው እላቸዋለሁ፡፡ በእርግጥም ጉዞዬ ደስታና
አስተራዕዮ (revelation) የተሞላበት ነው! ይሄ መጨረሻ የገለጽኩት ነገር ማብራሪያ ይፈልጋል፡፡ ያውም ይሄንን
መፅሐፍ የሚያክል፡፡ ይሄው አንድ መፅሐፍ ወጣው” ይላል፡፡
የፖል የመጨረሻ ጥበብ፣ “በሥራና ቤት በመቀመጥ የተሰላቸ ህይወታችሁን ለመስበር መጓዝ ፍፁም የሆነ
መድኃኒት ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ቁጭ ብለው ለውጥ ይጠብቁ፡፡ እኔ ግን እጓዛለሁ፡፡ በየጫካው፣ በማይደረስ ቦታ
መጓዝ፤ በሞባይል፣ በፋክስ፣ በመስመር ስልክና በየዕለቱ ጋዜጣ ላይ ማመፅና ማምለጥ ይመስለኛል” የሚለው
ነው፡፡ “እንዲህ አድርጋችሁ ከግሎባላይዜሽን ካመለጣችሁ በአሸናፊነት መፃፍ ትችላላችሁ፡፡ ተፈጥሮ ይክሳችኋል”
ይላል ፖል ቴሩ፡፡
ፖል ቴሩን ያለነገር አልወደድኩትም፡፡ ያላዩትን ማየት፣ ያልሰሙትን መስማት፣… በተፈጥሮ ታቅፎ… ስለተፈጥሮ
መፃፍ፡፡ ስለገጠሩ ሰው ህይወት፣ ስለአድባራት፣ ስለበዓላቱ መፃፍ…
* * *
የዛሬ ጉዞዬ ወደዘሙቴ ማሪያም ነው፡፡ ጉራጌ አገር - ሶዶ፡፡ እኔም እንዳቅሜ ስልክ የሌለበት፣ ፋክስ የሌለበት፣
የፖስታ አገልግሎት የማይገኝበት ቦታ ሄድኩ ማለት ነው፡፡ በጆሮ - ርቀት ወሬ ከሚራወጥባት አዲሳባ ለጥቂት
ቀናት አመለጥኩ፡፡ ኸክ የተባለው ጸሐፊ እንደሚለው “ወደ ሩቅ ግዛት እያበሩ መውጣት” አደረግሁ፡፡ እንግዲህ
በዘመናዊው አገላለፅ የሚቀጥለው ድረ - ገፅ “የዘሙቴ ማሪያም የፀጥታ ድባብ፣ የአረንጓዴው ተራራ ግርማ -
ሞገስ” ሆነ ማለት ነው፡፡
መስከረም 20 2007 ዓ.ም ነው የጉዞ ጅማሬያችን፡፡ የምሄደው፤
ከ19 ዓመት በፊት ከተቋቋመው “የዘሙቴ ማህበር የሐሙስ ቡድን” ከሚባል የጓደኛሞች ማህበር ጋር ነው፡፡
(ስለዚህ ማህበር ማንነት በሚቀጥለው ሳምንት እተርካለሁ፡፡ ነጋዴም፣ የመንግስት ሰራተኛም፣ የቴሌቪዥንና
ሬዲዮ ጠጋኝም፣ የህክምና ዶክተርም፣ መሀንዲስም፣ ፋርማሲስትም… አባላት ያለው ነውና በሰፊው ብተርከው
ይሻላል ብዬ ነው፡፡)
ጉራጌ አገር ስሄድ በእርግጥ ይሄ የመጀመሪያዬ አይደለም፡፤
ጉራጌ አገርን ያወቅሁት (ዕድሜ ለደርግ) “በዕድገት በህብረት የዕውቀትና የስራ ዘመቻ” ጊዜ ነው፡፡ በ1967 -
የዛሬ 40 ዓመት ግድም! ጊዜው እንዴት ይሮጣል ማለት ፋሽን ሆኗል መቼም፡፡ እኔም አልኩ፡፡ በምድብ ወሊሶ
በእነሞር፣ ጉንችሬ ወረዳ ዘምቼ ነው፡፡
ወዳጄ አሰፋ ጫቦ፤ ሰለመጀመሪያው የግጥም መፅሀፌ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና ስለእኔ ሲጽፍ፤ “ነቢይ
ሁለት ግጥሞች አሉት፡፡ ለየት ያሉ፡፡ አንደኛው “ገለታ ሉላሼ” (ገጽ 24) እና “አያ ልበ-ጥኑ” (ገፅ 30)፡፡ “ገለታ
ሉላሼ” የደቡብ ህዝቦች መወድስ ነው፡፡ የሐዲያ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ ጉራጌ፣ ዳውሮ…
“… ከሲዳሞ እስከ ከፊቾ፣ ከከምባታ እስከ ኦሞ፣
እንዳምሳ - እግር፣ ባምሳ ቋንቋ፣ ሲሳብ ሲሰባሰብ ከርሞ …” (ገፅ 25) ይለዋል፡፡
“አያ ልበ - ጥኑ” ደግሞ ስለቆጮና ጉራጌ ነው፡፡ ይህ ግጥም የተፃፈው ዛሬ ነው፡፡ ትላንት ኮሙኒስቶች፣
ኢንተርናሽናሊስቶች ነን ያልን፤ ዛሬ፣ እንኳን ለዓለም ለኢትዮጵያ አልበቃ ብለን የየመንደሩ ነገር ፈጅ ሆነናል፡፡
በዚህ ዘመን እንዲህ መፃፍ ለእኔ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ነቢይ አማራ ነው፡፡ ናዝሬት ተወልዶና አድጎ፤ ጉራጌ ዘመተ፡፡
አዲስ አበባ ተማረ፡፡ ታሰረ፡፡ ኖረ፡፡ ከራስ መንደር አልፎ በዚች “በጋራ ቤታችን” ዐይን ማየት ብርቱ ማየትን
ይጠይቃል፡፡ ከድንኳኗ ውጪ የሚያይ አይነ - ልቦና ይፈልጋል” እንዳለው ነው፡፡
ከዚያ ወዲያ አልፎ አልፎ ወደ ጅማ ስዘልቅ ዋና ዋናዎቹን ቱሉቦሎን፤ ወሊሶን፣ ወልቂጤን በረገጥኩ ቁጥር ጉራጌ
- ጉራጌ የሚለውን ስሜት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ከወደ ሻሸመኔ በኩል ወደቡታጅራ በሚያስገባው መስመር፣
ባለፈው የእየሩሳሌም ድርጅት የገለፅኩት ጉብኝቴና የቡታጂራ እንቅስቃሴዬ ከማውቃቸው ባሻገር የወላይታ፣
ሆሳዕና ወዘተ ጉዞ ለደቡብ ዕውቀቴ የተወሰነ እገዛ ሳያደርግ አልቀረም!
ሰበታ፣ ቱሉ ቦሎ፣ ተጂ፣ ተፍኪ፣ ወሊሶ፣ ወልቂጤ … እንድብር፣ ጉብሬ፣ እገዜ ገበያ ከዚያ ጉንችሬ፣ ማፌድ፣
ኤነር (… ዋቤ) ጃጉራ ዚዞ፣ አብሬት ሼህ ወዘተ…. ዛሬም ትዝታዬ ላይ ይንጣለላሉ!
ስለዚህ የዚህኛው ወገን ጉራጌ ከዕውቀቴ ሩቅ አደለም! ከክስታኔ ልጆች (በተለይ ከአሰፋ ጎሣዬ፣ አሰፋ ገዳ፣
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ወዘተ) ጋር ወገራምን መሄዴና ማየቴ እንደተጠበቀ ሆኖ ከስራ ባልደረባዬ ከገነት ጎሣዬ
ጋር አማውቴ ሄደን የነበረውም በጉራጌ አገር ሬከርዴ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ማረቆ ያለው አጎቴ ነብሱን ይማር (ጋሽ
ከበደ ወ/ሰማያት) አገሩን ሳያሳየኝ ተለያየን፡፡ አልፎ አልፎ አዲሳባም ናዝሬትም (እናቴን እና ሌሎች ዘመዶቹን
ሊጠይቅ ሲመጣ) ከሚነግረኝ የጉራጌ ታሪክ በተቀር ያንን አገር አላየሁትም፡፡ ዞሮ ዞሮ ብዙ ጉራጌ ጎን አለኝ
ማለት ነው የዛሬውን ጨምሮ!
ዛሬ ከወዳጄ ከኪዳኔ ቤት ነው መነሻችን ቀድሞ ወደ እሱ ቤት ሊወስደኝ ወደ እኔ ቤት መጥቷል፡፡ ወደ ቡታጅራ
ልናመራ ነው - በዓለም ገና በኩል፡፡ የጉዞው መጀመሪያ ይሄ ነው፡፡ ዕቃ እየተጫነ ለመንገድ የሚዘገጃጁ አብሮ
ተጓዦች ሁሉ እየተደራጁ ነው! በቱታ፣ በባርሜጣ፣ በዥንጉርጉር ቱታ ውር ውር እያሉ ነው፡፡ እኔ አልፎ አልፎ
ኪዳኔጋ ያገኘሁዋቸው ወዳጆቼ ቢሆኑም ብዙ ቀርቤ አላገኘሁዋቸውም፡፡ ሆኖም እንደዥጉርጉር ቱታቸው
ጠባያቸው እንደማይዥጎረጎር በሆዴ ተስፋ አደረግሁ! መንገድ ላይ ኢንተርቪው ማድረጌ የማይቀር ነውና የበለጠ
እንተዋወቃለን!
እግረ - መንገዴን በሌሎች ቦታዎች ለምሳሌ በሰባት ቤት እንዴት እንደሚከበር ካወያየሁዋቸው ወዳጆቼ
ያገኘሁትን ታሪክ እተርክላችኋለሁ፡፡ ዋናው ጉዳዬ ግን የዘሙቴ ጉዞዬ ነው፡፡ “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች”
እንዳይሆን ነዋ! ስለትግራይ ኢሮብ መስቀልም እንደዚሁ አያይዤ እተርክላችኋለሁ፡፡ (ኢሮብ በትግራይ መስቀል
ደምቆ ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ ነው፡፡) ስለጉራጌ አካባቢ አንዳንድ መጣጥፎችን ሳገላብት ባገኘሁዋቸው
ጠቅላይ መረጂያዎች መሰረት፡- “ጉራጌ” የሚለው መጠሪያ ስም የሚያጠቃልለው፡-
“በደቡብ ኢትዮጵያ በሰሜን - በአዋሽ ወንዝ፣ በደቡብ ምዕራብ በግቤ ወንዝና በምስራቅ በዝዋይ ሃይቅ መካከል
የሚኖሩትን ህዝቦች ነው” የሚለውን ታሪካዊ ጂኦግራፊ እንደጠቅላላ ዕውቀት ይዤ ነው የምነሳው፡፡ እዚህ ውስጥ
እንግዲህ ከነቋንቋ ዘዬአቸው - ሶዶ፣ ጎጎት፣ ሙህር፣ መስቃን፣ እዣ፣ ቸሃ፣ ጎመር፣ ጉራ፣ ኤነር፣ እንዳጋኝ፣
እነሞር፣ ጌቾ… እንደብጤታቸው እንደሚካተቱ ሁሉ፤ ስልጤ፣ ወለኔ፣ እነቆር፣ ኡርባረግና ዝዋይም የዚያኑ ያህል
ቦታ አላቸው፡፡ ግን ዘሙቴ የት ናት? ለምንስ ሄድኩ?
ይቀጥላል

 

Read 8638 times