Saturday, 11 October 2014 12:33

የጠቅ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፓትርያርኩን ተቃወሙ

Written by 
Rate this item
(38 votes)

               በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ተጠርቶ የተካሔደው ስብሰባ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ወቅታዊ ኹኔታ የማይገልጽ፣ መዋቅሩን ያልጠበቀ እና ጽ/ቤታቸው የማያውቀው መኾኑን በመግለጽ ተቃወሙ፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልጸግ›› በሚል ርእስ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያርኩ አዳራሽ የግማሽ ቀን ስብሰባ በተደረገበት ወቅት፣ የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን የመግቢያ ንግግር ተከትለው የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷ ‹‹አኹን ወደ ስብሰባው ስገባ ነው መልእክቱን የሰማኹት፤ አጀንዳውም ከመቅረቡ በፊት ከቋሚ ሲኖዶሱ ወይም ከእኔ ጋራ ምክክር አልተደረገበትም፤›› በማለት ስብሰባው ከመዋቅሩና ከዕውቅናቸው ውጭ የተጠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ባስተላለፈው የቃል ትእዛዝ መጠራቱ በተገለጸው በዚኹ ስብሰባ÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመምሪያዎች ዋናና ምክትል ሓላፊዎች፣ የድርጅቶች ዋናና ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ የዋና ክፍሎችና የክፍሎች ሓላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋናና ምክትል ሥራ አስኪያጆች መሳተፋቸው ተገልጧል፡፡

በ2001 ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ መጠናከሩን ተከትሎ የቀድሞው ፓትርያርክ መዋቅሩን ሳይከተሉና ከቅ/ሲኖዶሱ ጋራ ሳይመክሩ ወስደዋቸው ነበር ያሏቸውን ርምጃዎች በመቃወም በወቅቱ የአሜሪካ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የአኹኑ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በብዙኃን መገናኛ የሰጡት መግለጫ በማስረጃነት ተይዞ እንደሚገኝ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ቅዱስነትዎም በምትካቸው ሲቀመጡ መዋቅሩን ሊጠብቁ ይገባል፤ መዋቅሩን ሳይከተሉና ከሚመለከተው አካል ጋራ ሳይመክሩ የሚሠሩት ሥራ ቤተ ክርስቲያኒቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤›› እንዳሏቸው ተመልክቷል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹ውድቀት እንዳይደረስብዎ አማካሪዎችዎ ሊያዝንልዎ ይገባል፤›› ማለታቸውን የገለጹት የስብሰባው ተሳታፊዎች አያይዘውም ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአማካሪዎቻቸው ምክንያት ከዕድሜያቸው ዐሥር ዓመት አሳጥረዋል፤ እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሣ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት፤›› ሲሉ መምከራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ውይይቱን በሰብሳቢነት የመሩት ፓትርያርኩ በበኩላቸው፤ በሥራ የሚያግዛቸው ባለማግኘታቸውና ብቻቸውን በመኾናቸው›› ስብሰባውን ወደ ታች ወርደው ለመጥራት እንደተገደዱ አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ባቀረቡት በጽሑፍ የተደገፈ ገለጻ÷ በቤተ ክህነቱ የመልካም አስተዳደር ዕጦቶች እንዳሉ፣ በሙሰኝነት፣ በዘረኝነትና በአድሏዊነት የሚገለጹ የብልሹ አሠራር ሒደቶች እንደሚታዩ ዘርዝረዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራትና ግለሰቦች፣ ሕግና ደንብ እየጣሱ መዋቅሯን እየተፈታተኗት እንደሆነና ከመዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት እያካበቱ በመኾኑ አካሔዳቸው ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥንካሬና ህልውና ፍጹም አደጋ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡

መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር ኹሉም የሥራ ሓላፊዎች ራሳቸውን በመፈተሽና በማጽዳት ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ፓትርያርኩ፤ የማኅበራት አካሔድ ሥርዓት መያዝ እንዳለበት ጠቁመው ተገቢ ያልሆነውን አካሄድ ኹሉም ሊቃወመው ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹አማካሪዎቼ ዓላማዬን የሚጋሩና የሚያስፈፅሙልኝ ሰዎች ናቸው፤›› ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹አኹንም የምቀጥልበት መኾኑን አሳውቃለኹ›› ብለዋል፡፡ ‹‹ብቻዬን ነኝ፤ በሥራም አልታገዝኹም›› ለሚለው የፓትርያርኩ ንግግር ‹‹ቅዱስነትዎ አዝዘው ምን ያልተፈጸመ ነገር አለ?›› በሚል ምላሽ የሰጡት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ያልተፈጸመ ነገር ካለ ለጉባኤው በይፋ ይገለጽ›› ሲሉ ጠይቀዋቸዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግርና የችግሩ መገለጫዎች በርግጥም እንዳሉ ያልሸሸጉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ መምሪያዎችና ድርጅቶች የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በማውጣት፣ የክንውን ሪፖርት በአስተዳደር ጉባኤ በወቅቱ እንዲያቀርቡ፣ ድክመቶች እንዲስተካከሉና ጠንካራ ጎኖች ታቅበው እንዲቀጥሉ መደረጉን በመግለጽ በፓትርያርኩ ጽሑፍ የቀረቡትን መረጃዎች ወቅታዊነት ሞግተዋል፡፡

በልማት ተግባራትና በሠራተኛ አያያዝ ባለፈው በጀት ዓመት የተፈጸሙ ተግባራትን የዘረዘሩት የጽ/ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ በበኩላቸው፤ ቀጣይነት ባላቸውና በጥናት በተደገፉ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችና የተጉላሉ ባለጉዳዮች አለመኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የፋይናንስ ሥርዐት ዘመናዊው ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጠቁመው የፓትርያርኩን መረጃዎች አግባብነት እንደጠየቁ ታውቋል፡፡ አንድ የስብሰባው ተሳታፊ “አንድ ጣታችንን ወደሌላው ስንጠቁም ሦስቱ ወደኛ እንደሚያመለክት አንዘንጋ” በማለት ፓትርያርኩ ከሙስናና ብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ በዙሪያቸው ስላሉ አማካሪዎችም እንዲያስቡበት ጠቁመዋቸዋል፡፡መንግሥት የሲቪል ማኅበራትን የሚከታተለው ሕግ አውጥቶና ተቋም መሥርቶ መኾኑን፣ በሕጉ የሚተዳደር አብሮ እንደሚጓዝና አልፈልግም ያለ እንደሚወጣ የተናገሩት አቡነ ማቴዎስ፤ ቤተ ክርስቲያን ግን መንፈሳውያን ማኅበራት የሚቋቋሙበት ሕግ እንዳላወጣችና የምታቅፍበት መዋቅር እንዳልዘረጋች ገልጸዋል፡፡

በአገልግሎት ላይ ያሉትን መንፈሳውያን ማኅበራት በሕገ ወጥነትና በመዋቅር ባለመታዘዝ ለመጠየቅ በቅድሚያ ሕጉ ወጥቶ በሥራ ላይ ማዋሉ መቅደም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ “ለኢትዮጵያ በረሓ ወርደው፣ ብረት አንሥተው የታገሉትና ዋጋ የከፈሉት ኹሉም ሕዝቦች ናቸው፤ ሕገ መንግሥት ለኹሉም እኩል ነው፤ ለእገሌ ሚኒስትር እናገራለኹ፤ ለእገሌ ደኅንነት እደውላለኹ እያሉ አያስፈራሩን፤›› በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፓትርያርኩን እንዳሳሰቧቸው የስብሰባው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ አቡነ ማትያስ ቀደም ሲል ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ ሳይመክሩ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራትና ገዳማት አለቆች ጋራ ባደረጉት ስብሰባ፤ ሊቃነ ጳጳሳቱን ማዘለፋቸውን የጠቀሱት አቡነ ማቴዎስ በዚኽም ኹሉም አባቶች ቅሬታ እንደተሰማቸውና እንዳዘኑባቸው ተናግረዋል፡፡ ፓትርያርኩ ዓመቱን በሙሉ በየደረጃው እቀጥልበታለኹ ባሉት ስብሰባ÷ አጀንዳዎች መዋቅር ሳይጠብቁ፣ ጥናት ሳይደረግባቸውና ሳይብላሉ ውይይቱ ለሚዲያዎች ክፍት መደረጉ ቤተ ክርስቲያኒቷን ለአጉል ትችት ያጋልጣታል ሲሉ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

Read 10036 times