Saturday, 11 October 2014 12:30

የአረብ አገራት የሥራ ጉዞ ለመጀመር አዋጅ እስኪፀድቅ እየተጠበቀ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

           ለስድስት ወር ብቻ ታግዶ የነበረው ወደ አረብ ሃገራት የሚደረግ የሥራ ጉዞ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ጉዞውን እንደ አዲስ ለመጀመር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ የቀረበው አዋጅ እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ለስራ ወደ ውጭ ሃገር በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ ጉዞ ለ6 ወራት እንዲታገድ የተወሰነው ለስራ ብለው ወደ አረብ ሃገራት የሚጓዙ ዜጎችን በህጋዊ ማዕቀፍ አጠቃላይ ከለላ ለመስጠት የሚያስችልና በተጠናከረ ህግ የተደገፈ አሰራር ለማስፈን ነው ያሉት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ፤ እገዳው ሳይነሳ እስከ ዛሬ የዘገየው አዲስ የህግ ረቂቅ በማዘጋጀትና አጠቃላይ ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ ታስቦ ነው ብለዋል፡፡

ከሰራተኛና ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ ከሰራተኞች መብት፣ ደህንነትና ክብር፣ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሁም ከስልጠና ጋር የተያያዘ የህግ አንቀፆችን አካቷል የተባለው ረቂቅ አዋጁ፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎ እንዲፀድቅ መቅረቡንና ሰሞኑን መደበኛ ስራውን የጀመረው ምክር ቤቱ ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት አቶ ግርማ፤ አዋጁ እንደፀደቀ ታግቶ የነበረው የአረብ ሃገራት ስራ ስምሪት ይጀመራል ብለዋል፡፡

አዋጁን የማሻሻል ስራ ሰፊ ጊዜ እንደወሰደ የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ የህግ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በማሻሻል ሂደቱ እንዲሳተፉ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ረቂቅ አዋጁ ለስራ የሚሄዱ ግለሰቦች ተገቢውን ስልጠና ማግኘት እንዳለባቸው የሚገልፁ አንቀፆች እንደተካተተበት የተናገሩት አቶ ግርማ፤ ሰራተኞች ሰልጥነው መሄዳቸው የተሻለ ደሞዝ ተከፋይ ያደርጋቸዋል ይላሉ፡፡ ያልተማሩ ሰዎች እንዴት ይስተናገዳሉ የሚለው ጉዳይም በአዋጁ መካተቱን የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ዝርዝሩን ለመግለፅ አልችልም ብለዋል፡፡ወደ 40 የሚጠጉ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተመርጠውና ስርአተ ትምህርት ተቀርፆ፣ በቤት አያያዝና አጠቃላይ እንክብካቤ (care giving) ላይ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ከአረብ አገሩ የሥራ ጉዞ እገዳ በፊት ዜጎችን ወደ ተለያዩ የአረብ ሃገራት ይልኩ የነበሩ ኤጀንሲዎች ሰራተኞችን መላክ የተከለከሉ ቢሆንም ቀደም ሲል የላኳቸው ዜጎች የኮንትራት ስራቸውን ጨርሰው እስኪመለሱ ድረስ ደህንነትና መብታቸውን የማስከበርና የመከታተል ግዴታ አለባቸው ያሉት ኃላፊው፤ ኤጄንሲዎቹም ይሄን ግዴታቸውን እየተወጡ ነው፤ ችግሮች ሲያጋጥሙም ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እያነጋገረ ችግሩ እንዲፈቱ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ የላኳቸውን ሰራተኞች መብት ሁለት ዓመት ከአራት ወር ድረስ የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው አቶ ግርማ ጠቁመዋል፡፡ ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው አዋጅ ላይም ኃላፊነትና ግዴታቸውን በማይወጡ ኤጀንሲዎች ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች እንደተካተቱ ገልፀዋል፡፡ የእገዳው መዘግየት ህገ ወጥ ፍልሰትን አባብሷል የሚል ቅሬታ እንዳለ ያነሳንላቸው አቶ ግርማ፤ ህገወጥ ፍልሰት ህጋዊ ጉዞው ከመታገዱ በፊትም የነበረ መሆኑን ጠቅሰው በአሁን ሰዓት የሚመለከታቸው የህግ አካላት በድንበር አካባቢዎች እንዲሁም በአየር መንገድ አካባቢ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ በመሆናቸው የፍልሰት መጠኑ እየቀነሰ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

Read 5279 times