Saturday, 11 October 2014 12:27

የሶስትዮሽ ውይይት ሃሙስ በካይሮ ይቀጥላል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

             የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮችና ባለሙያዎች የሚሳተፉበትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚመክረው ሁለተኛው ዙር የሶስትዮሽ የቴክኒክ ውይይት፣ በመጪው ሃሙስና አርብ በካይሮ እንደሚቀጥል የግብጹ አሃራም ድረገጽ ዘገበ፡፡የግብጹን የውሃና የመስኖ ሚኒስትር ሆሳም አልሞሃዚን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በውይይቱ ላይ የሚሳተፉት 12 የአገራቱ ባለሙያዎች፣ ግድቡ በግብጽና በሱዳን ላይ የሚያደርሰውን ማህበራዊ፣ አካባቢያዊና የውሃ ተጽእኖዎች በተመለከተ ተጨማሪ ጥናት የሚያደርግ አለማቀፍ አማካሪ ኩባንያ ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ውይይት ሶስቱ አገራት የግድቡን ተጽዕኖ በተመለከተ ያገኟቸውን አዳዲስ የጥናት ውጤቶች አቅርበው ይወያዩባቸዋል፡፡አገራቱ ባለፈው ነሃሴ በግድቡ ተጽዕኖዎች ዙሪያ የሚሰሩ ተጨማሪ ጥናቶችን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንና የመጀመሪያው ዙር የሶስትዮሽ ውይይት ባለፈው መስከረም 10 ቀን በአዲስ አበባ መካሄዱ ያስታወሰው ዘገባው፣ በውይይቱ የተገኘው ውጤትም በአገራቱ መካከል የተጀመረው ድርድር ወደተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1913 times