በታዋቂው ደራሲ በክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ ስም የተሰየመው የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክና የምርምር ተቋም ሰሞኑን ተመሰረተ፡፡ በጐጃም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስር የተቋቋመው የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክና የምርምር ተቋም በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በስነ ፅሁፍ፣ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ፣ በፊልም፣ በባህልና በታሪክ ዘርፎች የተለያዩ ስራዎችን ያከናውናል፡፡ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቴዎድሮስ በካፋ በምስረታ ስነ ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በተለያዩ የኪነጥበብና የባህል ነክ ጉዳዮች ላይ የማሰልጠኛ ማንዋሎችን በማዘጋጀት ስልጠና የመስጠት፣ ምርጥ የፈጠራ ስራዎች ለህትመት የሚበቁበትን መንገድ የማመቻቸት፣ በኪነጥበባትና በባህል ዙሪያ ጥልቀት ያላቸው ጥናትና ምርምሮችን የማካሄድ ሥራዎችን በመስራት የጥበብ ሃብት ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ አላማ አለው፡፡ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁን ተቋም ለመመስረት ባለፈው ሰሞን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተከናወነው አውደ ጥናት ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተወካዮች የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን አቅርበው በተቋሙ አደረጃጀትና አሰራር ረቂቅ ማኑዋል ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡