Monday, 06 October 2014 08:24

ፓትርያርኩ ለመቄዶንያ 100 ሺህ ብር ለገሱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

            መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በማዕከሉ ባዘጋጀው የመስቀል በአል አከባበር ስነስርአት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገች፡፡ በእለቱ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ከማዕከሉ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ በመስቀል አከባበር ስነስርአት ላይ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የመንግስት አካላት የተገኙ ሲሆን ዝግጅቱን በንግግር የጀመሩት የመቄዶንያ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ብርሀኔ ጸጋዬ እና የድርጅቱ መስራችን ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ ማዕከሉ በአራት ማዕከላት 650 በላይ ለሚሆኑ ተረጂ ወገኖች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልፀው ከመንግስት የጠየቀውን 30.000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሰጠው፣ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ የተረጂውን ቁጥር ወደ 10,000 /አስር ሺህ/ ለማሳደግ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉም የጎበኙትና 100.000 ብር የለገሱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ፓትሪያርክ ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብጹሃን ጳጳስ፣ ይህንን እርዳታ እንዲያደርጉ የረዳቸውን እግዚአብሔርን አመስግነው ማዕከሉ እያከናወነ ያለው ተግባር እግዚአብሔር የሚወደው መሆኑን የገለፁ ሲሆን እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ወደፊት በማስተባበርም ሆነ በገንዘብ እግዚአብሔር በሰጠን፣ አቅማችን በፈቀደ እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ይህ ተቋም ከሌሎች የተለየ እውቅናና ክብር እንድንሰጠው ያደረጉ ተግባሮችን እየሰራ ያለ ማዕከል ነው፡፡ ከማዕከሉ ጋር አብረን ለመስራት ፈቃደኛ መሆናችንን ማረጋገጥ እንወዳለን ያሉ ሲሆን፤ የወረዳ 9 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ በፈቃዱ በበኩላቸው፤ የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን እየተደረገ ያለውን ድጋፍና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እናደንቀዋለን፤ ከዚህም ባሻገር እንደ አስተዳደር ልንተጋገዝ የሚገባ ጉዳይ ሲገኝ ተጋግዘን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

Read 2973 times