Monday, 06 October 2014 08:27

በአዲስ አበባ በሚካሄደው የስራ አጥ ምዝገባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ
ምዝገባው የሚካሄደው የስራ አጡን ቁጥር ለማወቅ ነው ተብሏል

        በአዲስ አበባ  ቤት ለቤት የሚካሄደው የስራ አጦች ምዝገባ አላማ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለማወቅ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ ተብሏል፡፡ ወደ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተይዞለት ከመስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፤ በዋናነት በከተማዋ ምን ያህል ስራ አጥ አለ የሚለውን ለማወቅና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ፣ የስራ እድሎችን ለማመቻቸት የታቀደ ፕሮጀክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የሙያ ደህንነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ ስዩም ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ እንዲህ መሰሉ ምዝገባ ከዚህ ቀደምም በየጊዜው በከተማዋ እንደሚካሄድ አስታውሰው፣ የአለማቀፍ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ለአገራት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥነት ሁኔታ በተጠናከረ መረጃ የማደራጀት፣ የመተንተንና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተንተርሶ መፍትሄ የመስጠት አካል ነው ብለዋል፡፡ የስራ አጥነትን ሁኔታ አጥንቶ የስራ እድሎችን ማመቻቸት የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮው አንዱ ኃላፊነት እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ምዝገባው ከወር በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደታቀደ ጠቁመዋል፡፡ ቤት ለቤት እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፣ ተመዝጋቢዎች በምን አይነት የስራ መስክ ላይ ቢሰማሩ ይመርጣሉ የሚለውን ያካተተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳ፤ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ የተሰበሰበው መረጃ ተተንትኖ፣ ተመዝጋቢዎች በሚፈልጉት የስራ መስክ ስልጠና ወስደው የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
ቢሮው ስራና ሰራተኛን በነፃ የማገናኘት ኃላፊነቱን ለመወጣትም ራሱ ስራ አጦችንና ስራን ከማገናኘት ባለፈ ፍቃድ የተሰጣቸው ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስራ አጦችን ስራ በማስያዝ ተግባር እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ምዝገባው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት የሚያደርገው ጥናትን መሰረት አድርጎ የተለያዩ ማመላከቻዎችን መጠቀሙ እንደሆነ የገለፁት አቶ ካሣ፤ በከተማዋ ያሉ ስራ አጦች በየትኛው የስራ መስክ ነው የበለጠ መሰማራት የሚፈልጉት የሚለውን ለይቶ ለማወቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ መረጃውን በመጠቀምም የተለያዩ የመንግስት እና የግል የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና መስካቸውን እንዲፈትሹ አጋዥ ይሆናል ሲሉ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡
በምዝገባው ወቅት እድሜና የትምህርት ደረጃ የመሳሰሉትን ጨምሮ በትክክልም በአዲስ አበባ ነዋሪ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይሰበሰባሉ ተብሏል፡፡ በአለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት መስፈርት መሰረት እድሜያቸው ከ14-18 ዓመት ያሉት በወጣት ስራ ፈላጊነት ይመዘገባሉ ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ የእድሜ ክልል ላሉ በአቅማቸው ሊሰሩት የሚችሉት ስራ ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ በዚህ የምዝገባ ሂደት አይካተቱም ብለዋል - ኃላፊው፡፡ በየዓመቱ በርካታ የከተማዋ ስራ አጦች የስራ እድል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ካሣ፤ በ2006 ዓ.ም ከ230 ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ በዚህ የስራ አጦች ምዝገባ ፕሮጀክትም ከ350 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ይመዘገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ምዝገባው የቤት ሰራተኞችን ጨምሮ ማንኛውም ተቀጥሮ የሚሰራና ገቢ የሚያገኝ ግለሰብን አይመለከትም ተብሏል፡፡
ስራ አጦችን ለመመዝገብ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ እንደተገባ የተናገሩት ኃላፊው፤ 734 ሰራተኞች በኮንትራት ተቀጥረው በከፍተኛ አማካሪነት፣ በሱፐርቫይዘርነት፣ በአስተባባሪነት እና በመረጃ አሰባሰቢነት እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡ መረጃ ሰብሳቢዎችም በዲግሪ የተመረቁ እንደሆኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም የክልል ከተሞች በ2007 ዓ.ም በሃገሪቱ ምን ያህል ስራ አጦች አሉ የሚለውን በዘመናዊ መንገድ ለይቶ ለማወቅ ተመሳሳይ ምዝገባ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ቀደም በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ስራ አጦች እንዳሉ አመላካች የሆነ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መረጃ እንዳልነበረ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  

Read 2715 times