Monday, 06 October 2014 08:20

ሚስት ደስተኛ ስትሆን ቤቱ ሰላም ይሆናል!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

               በሩትገርስ ዩኒቨርሲቲና በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ ጥናት፤ በትዳር ህይወት ውስጥ ከባልየው ይልቅ የሚስትየው ደስታ ለግንኙነታቸው ህልውና የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ተረጋገጠ፡፡ ተመራማሪዎቹ በአማካይ ለ39 ዓመታት በትዳር የዘለቁ ጥንዶች ላይ ጥናት እንዳደረጉ ታውቋል፡፡ ጥንዶቹ የትዳር አጋሮቻቸው ያደንቋቸው፣ ይሞግቷቸው ወይም ያበሽቋቸው እንደሆነ የተጠየቁ ሲሆን በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በሚያከናውኗቸው የተወሰኑ ተግባራት - ለምሳሌ አስቤዛ መሸመት ወይም ቴሌቪዥን መመልከት … ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ተጠይቀዋል፡፡ አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊዎችም በትዳር ህይወታቸው ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡ ሴቲቱ በባሏ ደስተኛ ከሆነች እሱም በአጠቃላይ ህይወቱ የበለጠ ደስተኛ ይሆናል - ስለትዳሩ የሚሰማው ስሜት ምንም ይሁን ምንም፤ ብሏል ጥናቱ፡፡
ከጥናት ፀሃፊዎቹ አንዷ የሆኑት ዲቦራህ ካር ለሩትገርስ እንደተናገሩት፤ “ሚስቲቱ በትዳሯ ስትረካ፣ ለባሏ የማታደርገው ነገር የለም፤ ይሄ ደግሞ በህይወቱ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ወንዶች ስለትዳር ግንኙነታቸው ብዙም አያወሩም፤ ስለዚህም በትዳር ህይወታቸው ደስተኛ አለመሆናቸው ወደሚስቶቻቸው ላይጋባ ይችላል”
ሰውየው በትዳሩ ደስተኛ ካልሆነ፣ ሚስቱ ህይወቱን ብሩህ ለማድረግ የምታከናውናቸው ትናንሽ ነገሮች የደስታ እጦቱን ሊሸፍነው ይችላል፡፡ ወንዶች የጥናቱ ተሳታፊዎች ከሚስቶቻቸው ይልቅ ትዳራቸው መልካም ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን ትዳራቸው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንደሆነ የሚያስቡ ተሳታፊዎች በሙሉ ግን በአብዛኛው የህይወት እርካታን የተጎናፀፉ ሆነው ተገኝተዋል - ያለምንም የፆታ ልዩነት፡፡

ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ያገኙት ሌላ ነገር ደግሞ ባሎች ሲታመሙ የሚስቶቻቸው ደስታ መጨመሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ለባሎቻቸው እንክብካቤ የሚያደርጉት እነሱ በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ሚስቶች ሲታመሙ ብዙ ጊዜ ለእርዳታ ፊታቸውን የሚያዞሩት ወደ ሴት ልጆቻቸው ነው፡፡ እናም የባሎች የደስታ መጠን ሳይለወጥ ባለበት ይቆያል፡፡ የትዳር ህይወት የጥራት ሁኔታና የደስታ መጠን ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ በጤናቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በዴቦራህ የጥናት ፅሁፍ  መሰረት፤ “ጥራት ያለው ትዳር አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በኋላ ዘመን ውጥረት ፈጣሪ ከሆኑ ጤና የሚያላሽቁ ተፅዕኖዎች መከላከያ ጋሻ ያጎናፅፋል፤ እንዲሁም ጥንዶች ጤናና ህክምናን የተመለከቱ አስቸጋሪ ውሳኔዎችን በቅጡ ለመወሰን ያግዛቸዋል፡፡”
በእናንተ የትዳር ግንኙነት በጥናቱ የተመለከተው ዓይነት ውጤት ገጥሟችኋል? ቢያንስ በግል ካስተዋልኩት፤ በትዳር ግንኙነታቸው ደስተኛ የሆኑ ሴቶች ለትዳር አጋሮቻቸው ተጨማሪ በጎ ነገር ለማድረግ ከመንገዳቸው እንደሚወጡ ተገንዝቤአለሁ፡፡ ይሄ ማለት ግን ወንዶች እንዲህ መሰሉን ነገር አያደርጉም ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ጥናት የምንረዳው አንድ ዋና ቁም ነገር፣ ሚስት ደስተኛ ስትሆን የትዳር ህይወት የሰመረ እንደሚሆን ነው፡፡ ንግስቲቷ ደስተኛ ስትሆን፣ መላው ቤተሰብ ደስተኛ ይሆናል እንደማለት!!

Read 7523 times