Monday, 06 October 2014 08:04

“በሱስ ብዛት የምዕተ ዓመቱ ግብ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንዴት ነው የአዲስ ዓመት ዕቅድ…‘ተጀመረ’ እንዴ!
እኔ የምለው…ሱስ ምናምን ነገርን በተመለከተ፣ በፊት እኮ አሪፍ ነበር፡፡ ወይ “መጠጥ አቆማለሁ…” ነው ወይ “ማጨስ አቆማለሁ…” አለቀ፡፡ አሁን ሱሶቻችን በአይነትና በብዛት ስለበዙ…አለ አይደል… እነ “መጠጥ አቆማለሁ…” “ማጨስ አቆማለሁ…” ኦልድ ‘ስቶሪ’ ነገር ሆነዋል፡፡ እኔ የምለው…ሰዋችን ይጠጣዋል! እንደምናየው ከሆነ ማጨስና መጠጣት…የሚያስተዛዘቡ መሆናቸው ቀርቷል፡፡
ደግሞላችሁ… ‘ሴሌብሪቲ’ የመሆን ሱስ አለላችሁ፡፡ …ብቻ እንደምንም ብለን ወይ ‘ሲንግል’ ለቀን ዘፍነን፣ ወይ የሆነ ፊልም ላይ እንደ ‘ዘብ’ ለመጫወት ‘ካስት ተደርገን’ (ቂ…ቂ…ቂ… ሊያመልጠኝ ሲል መለስኩት፣)  የሆነ ኤፍ.ኤም. ላይ… “የዛሬው እንግዳችን በቅርቡ የፈልም ዓለምን የተቀላቀለው አርቲስት….” መባል የሱስ ያህል ሆኖብናል፡፡
ልጄ ሆሊዉድ እኮ ገና ሰው ዓይን ለመግባት እንኳን ስንትና ስንት ዓመት መፍጋት አለ፡፡ እንደዛም ሆኖ ዕድሜ ልካቸውን ተውነው፣ አይደለም ተመልካች ሊሰለፍላቸው፣ ዳይሬክተሮች  የማያውቋቸው መአት ይኖራሉ፡፡ እኛ ዘንድ ግን እንደዚህ አይነት ችግር የለብንም፡፡ ‘ሴሌብሪቲ’ ለመሆን ‘ትሪለር’ በሚባል ዘፈን ዓለምን መቀወጥ፣ ‘ትዌልቭ ይርስ ኤ ስሌቭ’ የሚባል ፊልም ላይ ሠርቶ ዓለምን ቁጭ ብድግ ማሰኘት አያስፈልገንም፡፡ ‘ሲንግል’ ለቃቂና ሙሉ አልበም ያወጣ እኩል ታዋቂ የሚሆኑባት አገር ነች፡፡  
እናላችሁ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ለምሳሌ የሆነ የሰፈር ልጅ ምናምን አለ፣ ሲዞር ውሎ የምሳ ሰዓቱን በምንም አይነት የማያሳልፍ አለ፡፡ እናላችሁ… እናቱ ግራ ይገባቸውና ምን ይሉታል መሰላችሁ…“እንዲሁ ሰፈር ውስጥ ስትንገላወድ ከምትውል እንደ እኩዮችህ አንድ ነጠላ ዜማ እንኳን ማውጣት ያቅትሀል!” ይሉታል፡፡ በቃ…ሲንግል ያወጣል፡፡ ሲንግል ለመልቀቁ የምታውቁት ደሞ ወይ ጸጉር ‘ፍሪዝ’ ያደርጋል፣ ወይም ሱሪውን ‘ዝቅ’ ያደርጋል!
እሷዬዋ ደግሞ ምን አለፋችሁ እየተኳኳለች፣ እየተበጣጣረች…ስትወጣና ስትገባ እናት የሰፈር ወሬ አላስቀምጥ ይላቸዋል፡፡ “ኸረ ልጄ እኔንም የቡና መጠጫ አታድርጊኝ…ምን አለ እንደ ጓደኞችሽ አንዱ ፊልም ላይ ሌላው ቢቀር ቡና ስትቀጂ እንኳን ታይተሽ የአርቲስት እናት ብታሰኚኝ!” ይሏታል፡፡ በወር ውስጥ የሆነ ፊልም ላይ ብቅ ትላለች፡፡ ‘ብቅ’ ማለቷን የምታውቁት እንዴት መሰላችሁ… ከእኛ ፀጉር ብዙም የማይበልጠው ፀጓሯ… አለ አይደል… “ወገቧ ላይ የተዘናፈለው ዞማ ፀጉሯ…” ምናምን አይነት ሆኖ ቁጭ፡፡ (በቀደም የሰማናት… “በተገዛ ፀጉር በተገዛ ቅንድብ…” የሚል ስንኝ ያለባት ግጥም በጣም ተመችታናለች፡፡)
እናላችሁ…አንዲት ፊልም ላይ ‘ብቅ’ በማለትና አንድ ነጠላ ዜማ በመልቀቅ ‘ሴሌብሪቲ’ የሚኮንባት የእኛዋ አዲስ ነገር መፍጠር የማይገዳት ይቺው ጦቢያችን ነች፡፡
በነገራችን ላይ ሰሞኑን የተለያዩ የቲቪ ጣቢያዎች ላይ ያየናቸው የመዝናኛ ዝግጅቶች አንዳንዶቹ ደህና ነበሩ፣ ምንም እንኳን ብዙም “ብራቮ!” የምንልባቸው የፈጠራ ነገሮች ባናይም፡፡ አንዳንዶቹ ዝግጅቶች ግን የበዓል ልዩ ዝግጅት መባላቸው…ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል አሰኝቶናል፡፡ አብዛኞቹ ዝግጅቶች ላይ ግን ይቺ የ‘ሴሌብሪቲ’ ባህል ውስጣችን ምን ያህል እየሰረጸች እነንደሆነ የሚያሳዩ ነገሮች ነበሩባቸው፡ አሀ…ዝግጅት አዘጋጆቹ እኮ ‘አርቲስቶቹን’...አለ አይደል…“ሲሻሟቸው ከርመው ነበር እንዴ!” የሚያሰኝ ነው፡፡ አርቲስቶቻችን…ሁሉም ላይ መታየት መሰላቸት እንዳያመጣ  አስቡበትማ! ልክ ነዋ!… በማስታወቂያዎቹ እንኳን አብዛኞቹ ፊቶች ‘የለመድናቸው’ እየሆኑብን ነው!)  
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ደግሞላችሁ ‘የወንበር ሱስ’ ያለባቸው አሉላችሁ፡፡ የምር…አይደለም ሦስት መንግሥት፣ አሥራ ሦስት መንግሥትም ቢለዋወጥ የሆነ ‘ወንበር’ ላይ አይጠፉም! እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… እንዲህ አይነት ሰዎች ዓለምን ሲሰናበቱ ምን ብለው ሊናዘዙ ይችላሉ መሰላችሁ… “አደራ እንደሌላው ሰዉ ሳጥን ውስጥ እንዳትከቱኝ! የሆነ ወንበር ላይ አስቀምጣችሁ ቅበሩኝ…” ሊሉ ይችላሉ፡፡
እናላችሁ…እንዲህ አይነት ሰዎች አንድ ጊዜ የሆነ መሥሪያ ቤት አለቃ ይሆናሉ፣ ሌላ ጊዜ የሆነ የምናምን ኮሚቴ ሰብሳቢ ይሆናሉ፣ ሁሉም ቢጠፋ እንኳን እንደምንም ብለው የዕድር ዳኛ ይሆናሉ…ይህም ካልሆነ ደግሞ ጓደኞቻቸውን ሰብስበው ሰባት ሰው ያሉባት ዕቁብ ይመሠርቱና የዕቁብ ጸሀፊ ይሆናሉ፡፡
ከወንበር ሱስ ይሰውራችሁማ!
ደግሞላችሁ… እንዲሁ የሰማዩንም የምድሩንም ሁሉንም ነገር የማጣጣል፣ የመወንጀል ሱስ ያለባቸው አሉ፡፡ የምር…መድረክ ላይ ሲወጡ የሆነ ክፍልን ወይ ቡድንን ‘ወጋ’ ሳያደርጉ መውረድ አይፈልጉም፡፡ ልክ ነዋ…በየስብስባው “የራሳቸው ድብቅ ዓላማ ያላቸው…” አይጠፉማ! (እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ አገር… አለ አይደል… ስብሰባው ላይ የተገኙት ሁለት ሰዎች ብቻ ቢሆኑ እንኳን አንደኛው ‘የራሱ ድብቅ ዓላማ ያለው መሆኑን’ አትጠራጠሩ፡፡ እንደውም…ማመልከቻ የሚያስገባልን አጥተን ነው እንጂ…‘በነፍስ ወከፍ የድብቅ ዓላማ’ ብዛት ጊነስ ቡክ ውስጥ ባንገባ ነው!)
እናላችሁ…ሁሉንም የማጣጣል ሱስ ያለባቸው ሰዎች የሚሉት ቢያልቅባቸው እንኳን… እንደምንም ብለው “በዓጼ ልብነ ድንግል ዘመን ህዝቡ ኢንተርኔት እንዲጠቀም አይበረታታም ነበር…” ምናምን ከማለት ወደኋላ አይሉም፡፡
ከመወንጀል ሱስ ይሰውራችሁማ!
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ ይሄ ‘ኒኦ ሊበራሊዝም’ የሚሉት ‘ጭራቅ’ ነገር…እንኳንም ‘ክላስሜቴ’ ምናምን አልሆነ! አሀ…ሰሞኑን ሲወርድበት እንደከረመው ውግዘት ለሌላውም መትረፉ አይቀርማ! ወይ ደግሞ…መቼም ‘ክላስሜት’ ስለነበር እናዝንና… “እንደው እንደዛ እንትን የነካው እንጨት ሲያደርጉት ሆዴን ቦጭ፣ ቦጭ አደረገው…” እንልና…‘ራዳር’ ውስጥ ልንገባ እንችላለና!)
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሆነ አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ…ዘንድሮ የባህል መድኃኒት አዋቂውም፣ ዘመናዊ ክሊኒኩም፣ ሆነ ኮከብ ቆጣሪውም ምናምኑም “...ስንፈተ እንትን ካለባችሁ ወደ እኛ ኑ…” እያሉን ነው፡፡ እኔ የምለው…ይሄን ያህል ደክመናል እንዴ! የተጠና ነገረ ካለ ይነገረና! አሀ…እኛ የምናየው ነገር ሁሉ… ‘ስንፈተ ምናምን…’ ሳይሆን…አለ አይደል…አሥራ ሦስቱም ወር የሀበሻ ልጆች ‘ሜቲንግ ሲዝን’ ምናምን የሆነ ነው የሚመስለዋ! ቂ…ቂ…ቂ…
ይልቅስ፣ ምን መሰላችሁ… አቅማችን ለደከመው ብቻ ሳይሆን ኸረ ለበዛብንም መፍትሄ ይፈለግልን! ልክ ነዋ… የእንትን ሱስ ያለብን መአት ነና! ልጄ…በቀን ስንት ጊዜ የሚያንደረድረን እኮ ብንሰባሰብ በህዝብ ቁጥር ከዓለም አራተኛ የሆነ ‘ኪንግደም’ መመስረት የምንችል ይመስላል፡፡ (ወዳጄ… ያ በቀን አምስት ጊዜ ምናምን የሚያሯሩጠው ሰውዬ… ቀለለለት ወይስ ጭራሽ ተቆለለበት! የእሱ እኮ የሚገርም ነው…እንኳንም የመርካቶ ነጋዴ ሆነ፡፡ የዓለም የነዳጅ ‘ኰስት’ እንኳን በየቀኑ ይሄን ያህል አይወነጨፍም! ቂ…ቂ…ቂ… በነገራችን ላይ የሚያሯሩጠው ሰውዬ ነገር ‘እውነተኛ ታሪክ’ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ “ሰው እንዲህ ይቀጠናል!” የሚለውን ጥያቄ የምትተዉት ‘ሱሱ’ን ስታውቁለት ነው፡፡)
እናማ ከንእትን ሱስ የሚያላቅቅ የባህልም ሆነ ዘመናዊ መፍትሄ ይፈለግልንማ!
ከእንትን ሱስ ይሰውራችሁማ!
ደግሞላችሁ…የ‘ቦተሊካ’ ሱሰ ያለብን አለን፡ እንክት! አሁንም እንደግመዋለን የ‘ቦተሊካ’ ሱስ ያለብን አለን፡፡ አለ አይደል…እንደ ነፋሱ አነፋፈስ የምንወዛወዝ፡፡ ከፍ ብለን እንዳልነው የሦስት መንግሥታት ዓይነ ውሀ ‘ተስማምቷቸው’ የሚኖሩ ‘ቦተሊከኞች አሉ፡፡ ይሄ እኮ እንዴት አይነት ከእንትኑ የተጣላ ‘ኦፖዚሽን’ ምናምን መሰለህ…“ሲባል የምንጠይቀው ጥያቄ “በዛ ሰሞን የዘመኑ ሰው ነው፣ ምናምን ስትሉ አልነበረም እንዴ!” ምናምን የሚል ነው፡፡ የ‘ቦተሊካ’ ጂምናስቲክ ዓለም አቀፍ ውድድር ይዘጋጅልን፡፡ እኔ የምለው… እኛ አሪፍ፣ አሪፍ በሆንንባቸው ነገሮች ውድድር የማይዘጋጅሳ! ልጄ በ‘ቦተሊካ አጥር ዘለላ’ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ማንም አይደርስብንም፡፡በእግር ኳስ እንኳን ከአንድ ክለብ ወደሌላ ለመዘዋወር ስንትና ስንት ጣጣ አለበት፡፡ በኛዋ ጦቢያ ‘ቦተሊካ’ ግን ከአንዱ ካምፕ ወደሌላ ካምፕ መዝለልን የመሰለ የሚያፈጥን ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ደግሞላችሁ… ‘ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ’ ነገር የሚሆኑት እነኚህ የቦተሊካ አጥር ዘላዮች ናቸው፡፡ከ‘ቦተሊካ’ አጥር ዘለላ ሱስ ይሰውራችሁማ!
“በሱስ ብዛት የምዕተ ዓመቱ ግብ…” ምናምን የሚል ነገር ያለ እያስመሰለብን ነው፡፡
አንድዬ ከሱስ ሱናሚ ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3317 times