Monday, 06 October 2014 07:32

ክስ ከቀረበባቸው መፅሔቶች ሶስቱ ጥፋተኛ ተባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ማክሰኞ የቅጣት ውሳኔ ይሰጣል
         ሃሰተኛ ወሬዎችን አሳትሞ በማሰራጨት፣ ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል ክስ የቀረበባቸው “ሎሚ”፣ “አዲስ ጉዳይ” እና “ፋክት” መፅሄቶች አሳታሚዎች እና ሥራ አስኪያጆች ጥፋተኛ ናቸው ተባሉ፡፡ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው  የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት፣ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ብይን፣ የ“አዲስ ጉዳይ” መፅሄት አሳታሚ ሮዝ የህትመት ስራዎች ኃ/የተ የግል ማህበር እና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ፣ የ“ሎሚ” መፅሄት አሳታሚ ዳዴሞስ የህትመትና የፕሬስ ሥራዎችና ሰራተኛና ሥራ አስኪያጁ አቶ ግዛው ታዬ እንዲሁም የ “ፋክት” መፅሄት አሳታሚ ዮፋ ኢንተርቴይመንትና የፕሬስ ስራዎች እና ስራ አስኪያጇ ፋጡማ ኑርዬ በአቃቤ ህግ በቀረበባቸው ክሶች ጥፋተኞች ናቸው ብሏል፡፡ ቀደም ሲል ሁሉም ተከሳሾች በጋዜጣ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ባለመቅረባቸው በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ብይን የተሰጠ ሲሆን አቃቢ ህግም ኦርጂናል መፅሄቶችን በማስረጃነት እንዲያቀርብ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡
 በዚህም መሰረት ረቡዕ እለት ፍ/ቤቱ የአቃቢ ህግን ማስረጃዎች መርምሮ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ብይን ከሰጠ በኋላ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለፊታችን ማክሰኞ መስከረም 27 ቀጥሯል፡፡ መፅሄቶቹ በተለያዩ ጊዜያት ለህትመት ያበቋቸውን ፅሁፎች በማስረጃነት በመጥቀስ መንግስት በአሳታሚዎቹና ሥራ አስኪያጆቹ ላይ ክስ መመስረቱን በሚዲያ ያስታወቀው በነሐሴ ወር 2006 ዓ.ም እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል በፌደራል የመጀመሪ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እየታ የሚገነው የጃኖ መፅሔት እና አፍቶ ታይምስ ጋዜጣ አሳታሚዎች እና ስራ አስኪያጆች ክስ እንዴት ይቀጥል የሚለው ላይ ፍ/ቤቱ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 3 ቀን 2007 ኣ.ም ቀተሮ ሰጠ ሲሆን በእንቁ መፅሄት አሳታሚና ስራ አስኪያጅ ጉዳይ ደግሞ የመፅሄቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ህግ ጠበቃው ድርጅቱን ወክለው መከራከር ይችላሉ አይችሉም በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል፡፡  

Read 2895 times